IMG_4372

ዋዜማ ራዲዮ-የኢትዮጵያ ፖለቲካ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት እና ሌሎች ጉዳዮች በሚል በ10 ምዕራፎች የተከፈለው እና 288 ገጾችን የያዘው የአቶ ገለታው ዘለቀ መፅሀፍ ባሳለፍነው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ሳንኮፋ መፅሐፍት መደብር ተመርቋል::
በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ምን አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ቅርፅ ያስፈልገናል ለሚለው ከራሳቸው የጥናት ግኝት በመነሳት ያዘጋጁት መፅሀፍ ነው::
የዋለልኝን የብሄሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ : ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ተግዳሮቶችን በመፅሀፉ ሲያካትት: በዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳቦችን በመተንተን በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ አንድነት መፍጠር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ያትታል::
ሀገሪቱ ውስጥ ላለው ችግር አሁን ያለው ስርዓት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሆነ የዴሞክራሲ እና የነጻነት ጥያቄን የያዘ በመሆኑ ልሂቃን በትግል ስልት እና በፖለቲካ አስተሳሰብ ከመለያየት ይልቅ ኢትዮጵያ በሽግግር ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ መግባት አለባት በሚለው ሀሳብ መግባባት አለባቸው ብለው ያምናሉ አቶ ገለታው:: ለዚህ ሽግግርም የኢትዮጵያን  ባህላዊ አንድነትን ማዕከል ካደረጉ ሀገሪቱ ወደተሻለ የፖለቲካ ምዕራፍ ትሻገራለች ይላሉ::
በዓለም ላይ ያሉ የተለያየ የሶሺዮ ፖለቲካ ንድፈ ሀሳቦችን በመተንተን በህገ መንግስት ቀናኢነት እና በስምምነት ላይ የተመሰተ ባህላዊ አንድነት መገንባት ስለሚቻልባቸው ስልቶች ጸሀፊው አትተዋል::
በቀጣይ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሀገርነት ትሻገራለች ለሚሉ ሀይላት በጥቅሉ የትኛውን ዴሞክራሲ ትከተል በሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ይመክራሉ:: ከወዲሁም ከለውጡ በኃላ ሊመጣ የሚችለውን ስርዓት ሁሉንም የሚያስማማ ያሉትን ባህላዊ አንድነት መገንባት ላይ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ በመጽሀፍቸው አስረድተዋል::