Abate Mekuriaዋዜማ ራዲዮ-በህመም ላይ የሰነበተው ዕውቁ የትያትር አዘጋጅ አባተ መኩሪያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በ”ፕሮስቴት እጢ” በጠና ታምሞ ህክምናውን ይከታተል በነበረበት “አዲስ ህይወት” ሆስፒታል ረቡዕ ምሽቱን ያረፈው አባተ ላለፉት 50 ዓመታት ለኢትዮጵያ ትያትር የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆየ ባለሙያ ነበር። በሙዚቃዊ ትያትር ዘርፍም ፈር ቀዳጅ ስራዎች ወደ መድረክ እንዳመጣ ይነገርለታል።

የፀሀፊ ተውኔት ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን ወጥ እና የሼክስፒርን ትርጉም ስራዎች እስትንፋስ ዘርተው፣ በመድረክ ተወዳጅ እንዲሆኑ በማድረግ የአባተ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ እንደነበር ባለሙያዎች ይመሰክሩለታል። በ1966 ዓ.ም ካዘጋጀው “ሀሁ በስድስት ወር” ጀምሮ “አቦጊዳ ቀይሶ” እና “መልዕክተ ወዛደር” ይጠቀሳሉ።

አባተ ታሪካዊ ትያትሮችን የሚገባቸውን ደረጃ ሰጥቶ በመስራትም ይታወቃል። በ1973 ዓ.ም ያዘጋጀው “ቴዎድሮስ” እና ከስድስት ዓመት በሁዋላ ለመድረክ ያበቃው “አሉላ አባ ነጋ” ከእነዚህ መካከል ይመደባሉ። አባተ ከሚታወስባቸው ዝግጅቶቹ አንዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት፣ የ”አድዋ”ን የክተት ዘመቻ የሚያሳይ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ያቀረበው ትርኢት ነበር።

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ያገለገለው አባተ በግሉ የቴአትር ስቱዲዮ  አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በ1988 ከመደረከው “ኤዲፐስ ንጉስ” በሁዋላ እምብዛም ወደ መድረክ ያልመጣው አባተ ዳግም ወደ መድረክ የመመለስ ፅኑ ምኞት ነበረው። በዚህ ዓመት ለእርሱ ክብር የተዘጋጀ መሰናዶን ተከትሎ በኤፍ.ኤም 97.1 ከሚተላለፈው “አዲስ ዜማ” ጋር በነበረው ቆይታ ይህንኑ ፍላጎቱን አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሮ ነበር። “መድረክ እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ” የሚል ቅሬታውንም አሰምቶ ነበር።