President Biden and His Sec of State Anthony Blinken – ABC

ዋዜማ ራዲዮ- የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ቢሊንከን ለመገናኛ ብዙሀን ባሰራጩት መግለጫ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት፣ በወታደራዊና የደህንነት ሹማምንት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ መዋቅር መሪዎች እንዲሁም በወንጀል የተሳተፉ የሕወሓት መሪዎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ ጣለች።

እሁድ ማምሻውን ይፋ በተደረገው መግለጫ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ማበረታቻና የፀጥታ ድጋፍ ታቋርጣለች። የስብዓዊ ዕርዳታ እንዲሁል ለትምህርት፣ ግብርናና ጤና ለመሳሰሉት የሚደረገው የልማት ዕርዳታ ግን ይቀጥላል።

አሜሪካ ማዕቀቡን ለመጣል የወሰነችው የትግራዩ ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያቀረብኩት ሀሳብ ተቀባይነት አላገኘም በሚል ነው።

የጉዞ ማዕቀቡ የትኞቹን ባለስልጣናት እንደሚመለከት መግለጫው አልዘረዘረም። አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ባለስልጣናትና በሕወሓት አንዳንድ አባላት ላይ የተጣለው እገዳ የጠቀሰው ደንብ ቁጥር (Section 212a) ሲሆን በዚህ ደንብ መሰረት የማዕቀቡ ዒላማ የሆኑት ባለስልጣናትን ስም ለህዝብ ይፋ ማድረግን አይጠይቅም።

በተለምዶ ለከፋ የስብዓዊ መብት ረገጣና ሙስና ጉዳዮች ስራ ላይ የሚውለው የማዕቀብ አይነት (Section 7031c) ሲሆን ማዕቀቡ የሚመለከታቸው ባለስልጣናትና ግለሰቦች ስም ዝርዝር በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ያዛል።

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ግድያና መሰል ወንጀሎች የተሳተፉ ወገኖችን ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ለፍርድ እንዲያቀርቡ የአሜሪካ መግለጫ ይጠይቃል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት በትግራይ ጦርነት የሚሳተፉ ወገኖች ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲደረግ የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]