ዋዜማ- መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅጥር ሲፈጽሙ ሀሰተኛ የትምህርት ሰነድን ያቀረቡ 220 ሰራተኞቹን ማበረሩን ዋዜማ ከባንኩ ምንጮች ሰምታለች።
ባንኩ ከሰሞኑ ሀሰተኛ የትምህርት ሰነድ አቅርበዋል በሚል ከስራ ያባረራቸው ሰራተኞቹ ባለፈው አመት ንግድ ባንኩ ባወጣው የስራ ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ በስራ ላይ የነበሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አመት በአንድ ቅጥር ክብረ ወሰን በተባለ ሁኔታ ወደ 12 ሺህ ሰራተኞችን መቅጠሩ ይታወሳል።ሆኖም ባንኩ እነዚህ ተቀጣሪዎች ፈተና አልፈው የስራ ቅጥር ውል ፈጽመው ወደ ስራ ከገቡ በሁዋላ ተመርቀንበታል በሚል ያስገቡትን የከፍተኛ ትምህርት ሰነድ ፣ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በመላክ በጀመረው የማጣራት ስራ ከ200 ዋዜማ በላይ ሰራተኞች ያቀረቡት የትምህርት ሰነድ ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ተቀጣሪዎች የፈጸሙት የሰነድ ማጭበርበር ሁለት አይነት መልክ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ፣ የተወሰኑት ተቀጣሪዎቹ እንዳስገቡት ሰነድ የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ቢሆንም ፣ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ በማሰብ በትክክል ካመጡት የመመረቂያ ውጤት ላይ ከፍተኛ የሆነ የነጥብ ጭማሬ እንዳላቸው በማስመሰል ሀሰተኛ የትምህርት ሰነድ ማሰራታቸው ተረጋግጦባቸዋል።
ሌሎቹ ደግሞ ለባንኩ ለቅጥር ያስገቡት የከፍተኛ ትምህርት ሰነድ ፍጹም ሀሰተኛ መሆኑ በመረጋገጡ ከስራ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል።ንግድ ባንኩ ጉዳዩን ወደ ህግ ይውሰደው አይውሰደው ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ሆኖም ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀጠራቸው ሰራተኞች ላይ የጀመረው የትምህርት ሰነድ ማጣራት እስካሁን አለመጠናቀቁን ፤ ይህ የትምህርት ሰነድ ከአምና ተቀጣሪዎች ባለፈ ቀድሞ ተቋሙን በተቀላቀሉ ባልደረቦችም ላይ የትምህርት ሰነዶች ትክክለኝነትን በስፋት ወደ ማጣራት እንደሚገባም ሰምተናል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተጭበረበረና ሀሰተኛ ሰነድ ተቀጥረው በስራ ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የፀረ ሙስና ኮምሽን ከዚህ ቀደም ፍንጭ ቢሰጥም በጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ አላቀረበም። ዋዜማ በቅርብ ወራት ያነጋገረቻችውና ወንጀሉን ለማጋለጥ ተቋም መስርተው በምስጢር እየተንቀሳቀሱ ያሉ ባለሙያዎችን በጠየቀችበት ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር በርካታ ሰዎች ያለ ሙያቸውና ብቃታቸው እየሰሩ እንደሚገኙ መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል። አንዳንዶች ከውጪ ሀገር በግዥ የተገኘ የትምህርት ማስረጃ አቅርበው በመንግስት ሀላፊነት እስከመቀመጥ የደረሱ ሲሆን በርከት ያሉ የክልል ባለስልጣናትም ህጋዊ ያልሆነ የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው ተቋሙ ማረጋገጡን ነግሮናል። ተቋሙ የምርመራ ግኝቱን ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቅ ቅ ለፀረ ሙስና ኮምሽን እና ለህዝብ ይፋ የማድረግ ዕቅድ አለው። [ዋዜማ]