ዋዜማ- የሸኘነው ወር፣ ያ ታላቅ ማኅበራዊ አብዮት የተቀሰቀሰበት የኅምሳኛ ዓመት ዝክር  ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን በዝምታ ልታልፈው መርጣለች። የጽሕፈት ተውስዖዏን እና የውይይት አደባባዮቿን ለዚህ እንድታውል ቢጠበቅባትም፣ ምንም ያልተፈጠረ ያህል ክስተቱ በለሆሳስ እንኳን ሳይነሳ ታልፏል። ምን አልባትስ ገዢዎች፣ ‘የማን አብዮት?’ ብለውት ይሆን? የሚለውን መናፍቃዊነትም ወረድ ስንል እናነሳዋለን። እንዲያም ቢሆን፣ ከምንግዴለሽነቱ ጋር ላለማበር፣ እጅግ ጥቂት ማሰላሰያ ነጥቦችን እናገኝ ዘንድ፣ በአንድ ድርሳን በኩል ጥቂት እናጨንቁር።

    ያን አብዮት አስመልክቶ፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እና ከሚፃረሩ ጥጎች አንድ ቤተ መጻሕፍት የሚሆኑ ድርሳናት ተጽፈዋል። ይህኛው ፓርቲ ትክክል ነበር ባዮቹም፣ ዛሬም ከልቦለዱ እስከ የግል ትውስታዎቻቸው እየጻፉ ነው። ከሞት ፍርድ የተረፉትም፣ የመጨረሻዎቹን ወሮቻቸውን ያባከኑት፣ የኢሕአፓን እና የመኢሶንን ኅጢአት ሲያወሱልን እንጂ፣ በይቅርታም፣ በፀፀትም የወረደውን መከራ ሲያብሱ አልነበረም። የመኢሶኑን አዛውንት፣ የደረጄ አለማየሁን “ታዝቤ ዝም ከምል”ን ገፋ ብናደርጋት፣ የአብዮቱን መቀልበስ የሚነግረን፣ ስለ ትውልዱ መባከን የሚንገበገብ የትውልዱን ሰው እንዳጣን መኖራችንን አሌ አንልም። በተለይም በ40ኛው እና በ50ኛው ዓመት መካከል ባሉት ጊዜያት አብዮቱን አስመልክቶ የወጡትን መጸሐፍት ስንመለከት፣ የግል ትውስታዎች እና ፓርቲ ተኮር የሆኑት ይበዛሉ። በእርግጥ ያም ሆኖ፣ ከተለመዱት ፓርቲያችን ትናንትም፣ ዛሬም ትክክል ነው ከሚሉ አታካች እሪታዎች ባለፈ፤ እንደ መሃመድ ይማም፣ ‘Wore Negari: A Memoir of an Ethiopian Youth in the Turbulent ’70s’መሰል፣ እንደ ቤተ መቅደስ ይታይ የነበረውን የኢሕአፓን ቅፅር “ያረከሱም” ሕትመቱን ተቀላቅለዋል። በዚህ ዐሥርት መካከል ግን፣ ጠበቅ ያሉ ምሁራዊ ሥራዎችን ተነፍገናል ሰንብተናል ማለት እንችላለን። 

  ለዛሬው ጥቂት ሐሳባዊ መነሾችን ይሰጠን ዘንድ የመረጥነው ግዙፍ ድርሳን የወጣው በአብዮቱ 40ኛ ዓመት ክብረ-በዓል ዋዜማ ነበር። “IDEOLOGY AND ELITE CONFLICTS: AUTOPSY OF THE ETHIOPIAN REVOLUTION” በሚል እንግዳ መሰል ርዕስ፣ መጽሐፉን ያቀበለን የአብዮቱ ተሳታፊና የፍልስፍና መምህሩ መሳይ ከበደ፤ በኢትዮጵያ ልሂቃን ተነቃይነት፣ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ግድፈት እና በአገር በቀሉ ምዕራብ ተገዳዳሪ ዕውቀቶች ላይ ያዋጣቸው ጹሑፎች እና መጻሕፍት፣ የኢትዮጵያ የጥናት መስክን ማበልፀጋቸውን አለመመስከር ንፉግነት ይመስላል።

ይህኛው የፕሮፌሰሩ ጥናት፣ ከዚህ ቀደም ብሎ የወጣውን “Radicalism and Cultural Dislocation” በተሰኘው እጅጉ የበዛ ምሁራዊ ሙገሳ ያገኘውን፣ የተማሪዎቹ ንቅናቄን ላዕላይ መዋቅር የፈተሸበት ሥራ ቅጣይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ያም ሆኖ፣ እስከዛሬ አብዮቱን አስመልክቶ ከተጻፉ ጥናታዊ ሥራዎች ፈንገጥ ያሉ የክርክር ነጥቦችን መጽሐፉ ቢያነሳም፣ በሌሎቹ ምሁራኖቻችን ዘንድ ምላሽ ለመነፈጉ አንድ ዋንኛ ነጥብን ማንሳት የሚቻል ይመስለናል። ይኸውም፣ ተለምዷዊውን የአብዮቱን መነሾ ተረኮች ወደ ጎን ብሎ፣ የዚያ ክስተት ዕውን መሆን፣ ሥልጣን የሚያመጣቸውን ጥቅሞች ያሰሉ ልሂቃን ግብግብ እና የርዕዮተ ዓለም(በእኛ ጉዳይ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምን) ሚናን ከፊት ማስቀደሙ ይመስላል። ራሱም እንደሚለው፣ “የልሂቃንን ግድድር ማዕከላዊ ሚና መስጠት፣ የኢትዮጵያን አገረ-መንግሥት መውደቅ ያብራራልናል”፤  አብዮቱ የሰፊው ሕዝብ ነው የሚለውን ተለምዷዊ ተረክን በዚህ መንገድ ማጠየቁም፣ ለመጸሐፉ ገሸሽ መደረግ ገፊው ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፤(ምንም አልተፈጠረም ብለን ምናልባት እንዳንደመድም የሚያደርገን፣ በኖርዝ ኢስት አፍሪካን ስተዲስ የጥናት መጽሔት ላይ፣ በእርሱ ሸንቋጭነት ከባህሩ ዘውዴ ያደረጓቸው መሳጭ ምልልሶች ናቸው)።

አፄውን የጣሉትን ልሂቃን እና ንቅናቄዎችን የፖለቲካ ታሪክ በቅጡ እና በብዙ አቅጣጫዎች የተነተነበት ይህ ሥራ፣ ግዛተ-አፄው የቆመባቸውን መሠረቶችንም አዳዲስ ዕይታ እያከለ ማብራራቱ ዋንኛው አበርክቶውም ነው። ከእነዚህ ጭብጦች መካከልም፣ ጃንሆይ መንበራቸውን ለማፅናት ከተጠቀሟቸው ስልቶች አንዱ የፖለቲካዊ ሹመት ዕቅፋት ስልትን (ኮኦፕትሽን) መሆኑን ሲነግረን፣ ኋላ የኢሕአዴግን አገዛዝ ለመገምገም በብዙ ጥናቶች ላይ ጠቀሜታ ላይ የዋለውን የመንፈቀ-ጥቅማዊ ግንኙነት ኀልዮት(ኒዮፓትሪሞናሊዝም)፣ ለአገዛዝ መሠረት ሰጪነት የቀደመ የባህል ድልዳል እንደነበረንም ማሳያ ይሆነናል። ደግመን ደጋግመን ብናነሳው፣ አብዮቱን ጭምር በቅጡ  ለመረዳት ዋጋ ያለው ሃሳብ ሊሰጠን የሚችለውን፣ በእርግጥ በቅድመ-አብዮቷ ኢትዮጵያ ‘ፊውዳሊዝም ነበር’ የሚለውም ብርቱ ጥያቄ ከተነሳባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች አንዱ ነው።

የተማረው ክፍል ሥር-ነቅልተኝነትም ሆነ የደርግ ድንገታዊ ክስተት፣ ማኅበራዊ መሰላሉን የዘጋ ማኅበረሰብ ውጤት ነው የሚለን መሳይ፣ መዘጋት አዝግማዊ ሁሉን ዓቀፍ ዕድገትን መግታት ነውና፣ ይሄን ዕግዳት ማኅበረሰቡ ከመንገዱ ገለል ለማደረግ ከአብዮት፣ ሊያውም ከማኅበራዊ አብዮት ውጪ አንዳችም አማራጭ አይኖረውም የሚለውም የመጸሐፉ የክርክር ልብ ነው። [ፅሁፉ ከታች ይቀጥላል]

“የማን አብዮት?”¡

   ያን አብዮት፣ በአብዮት ሃቲቶች አስደግፈው የተነተኑ በዛ ያሉ ተጠቃሽ ጥናቶች አሉን ብሎ ለመናገር የሚያስችል ድፍረት ብዙም የለንም። የዚህ መጸሐፍ አንዱ ዋጋም ያለው እዚሁ ነጥብ ላይ ነው። ፕሮፌሰር መሳይ፣ እስከዚህ ዘመን ድረስ ያሉ የተለያዩ የአብዮት ኅልዮቶችን በሚገባ ያብራረበት እና ከእነዚህ ኅልዮቶች አኳያም የኢትዮጵያው ቦታው የት እንደሆነ ለማስረዳት የሄደበት ርቀት፣ ምሁራዊ ኅሰሳውን አድካሚ ያደረገው መስሏል። መሳይ፣ በዚህ አራት መቶ ገፅ ሥራው ሰብሰብ አድርጎ ከተቸባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ አብዮቱን አስመልክቶ ሲሰጡ የነበሩ ስያሜዎችን እና ተያያዥ ሐሳባዊ መቆሚያቸውን በጠንካራ ጉልበት እያነፀረ የዳሰሰባቸው ገፆች ናቸው። የዘመናዊ ኢትዮጵያም ሆነ በውስን መልኩ የአብዮቱ አጥኚዎች በዚያ አብዮት ስያሜም ሆነ ዋንኛ ባህሪያት ላይ ስሙም አይደሉም። ለማሳያነት ጠርዝ እና ጠርዝ የሚተያዩትን ሁለቱን ብቻ አንስተን እንሻገር።   

አብዮቱ በምዕራባውያኑ ግራ ዘመም ምሁራን ጭምር ቸል ተብሏል የሚሉ ብስጭቶቻቸውን የሚያሰሙን እንደ ክርስቶፈር ክላፋም መሰሎቹ ነባሮቹ የኢትዮጵያ ጥናት ተማሪዎች፣ አብዮቱ በወታደራዊው ደርግ ስር የተካሄደ እውነተኛ ሶሻሊስት አብዮት ነው ሲሉት ብዙም አልተቸገሩም። እውነተኛ ነው ለማለትም፣ አፄያዊው ሥርዓት ከእነ ባለመሬቱ ገዢ መደብ ጋር ወደ ታሪክ ቅርጫት መወርወሩ፤ አልፎም፣ የምርት ግንኙነቱ እና ስልተ ምርቱ በሶሻሊስት ርዕዮት ሙሉ ለሙሉ በማዕከላዊ መንግሥቱ መዳፍ ተጠቅልሎ መያዙ እንዲህ እንዲደመድሙ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው። በእርግጥ ያ አብዮት በደም አፋሳሽነቱ ጭምር፣ ከፈረንሳይም ሆነ ከሩሲያ አብዮቶች አይተናነስም ባይነታቸውም የስያሜያቸው ማናጠቂያ ነው። 

ከዚህ በተፃራሪ የሚቆሙት ዘውጌ ብሄረተኞቹ ሲሆኑ፣ በተለይም ለኦሮሞ ብሄረተኞቹ፣ አብዮት ተካሄደ ይሉት ቀልድ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደ አሰፋ ጃለታ እና ቦኔ ሆልኮምብ እና ሲሳይ ኢቢሳ መሰል የ“The Invention of Ethiopia” ጸሓፍት፣ ግዛተ-አፄው “በቅኝ ግዛት ሥርዓት የተዋቀረ ነውና”፣ አብዮቱ እና ቀጥሎ የመጣው ደርግ፣ በሶሻሊዝም ስም አማራዋዊነትን ቅኝ በተገዙት ሕዝቦች ላይ ከመጫን ያለፈ አንዳችም ያመጡት ፋይዳ የለም።

ዘግናኝ ጭሰኝነት የነበረበት የመሬት ሥሪቱ ከኦሮሚያ ሰማይ ላይ በኖ መጥፋቱም ሆነ፤ በእንድሪያስ እሸቴ አነጋገር፣ ከብሄር ጭቆና ይልቅ ወደ ባርነት ይቀርብ የነበረው የምዕራብ ኢትዮጵያ ግፉዓን መዓት በአብዮተኞቹ ደም ተሠርዮ፣ ወደ አደባባዩ ከእነ ማንነቶቻቸው መምጣት የልጆች ተረት እንጂ፣ የ50 ዓመት ዝክሩን የምናወድስለት በደም የተፃፈ ታሪክ አልሆን ብሏቸዋል። ምናልባትም፣ አገሪቷ ያን ታላቅ ማኅበራዊ አብዮት ያያች ሳትመሰል እንዲህ በዝምታ ሥርዓተ-ክብሩን ማሳለፏ፣ ይህን “የማን አብዮት?” ባይነት የሚጋሩ ልሂቃን ለመንበሩ ከመቅረባቸው ይነሳ ይሆን ለሚል ጠርጣራ ማን ደህና ምላሽ ሊሰጥ ይችላል?!   

 አብዮቱ ከሽፏል?

    በግብታዊ አነሳሱ እና ጉዞው ላይ ክርክር የማይሰማበትን ያን አብዮት፣ ያሳካቸውን እና ረግጦ ያለፋቸውን የቀደሙ ማኀበራዊ ጥያቄዎች በማንሳት፣ እንደከሸፈ የሚናገሩ ድርሳናት በርከት ያሉ ናቸው፡፡ ተሳክቷል ከሚሉት ይበልጥ በውድቀቱ ልክ ላይ የሚነታረኩ ጸሓፊያን ይበዛሉ፡፡ የሁለቱንም ክርክሮች ስንፈትሽ የምናገኘው አንድ በጥምዝም የሚቀርብ መነሻዊ መላምት አለ፡፡ ይኸውም፤ ክስተቱን እንደ ፖለቲካዊ አብዮት ወይስ እንደ ማኀበራዊ አብዮት ይመለከቱታል የሚለው ነው፡፡ ይህ ድርሳን፣ በተለይም በማኅበራዊ አብዮት እና በፖለቲካዊ አብዮት መካከል ያሉትን መሠረታዊ ልዩነቶች በቅጡ አብራርቶ ማስቀመጡ፣ አብዮቱ ከሽፏል አልከሸፈም ለሚለው ሰሞናዊው ክርክር ዋጋ ያላቸውን ነጥቦች ያቀብለናል። 

ከተለምዷዊው ግራ ዘመም ሐሳባዊ ማዕቀፍ አብዮቱን የሚገመግሙ፣ በክሽፈቱ ላይ ክርክር አያነሱም፡፡ ነገር ግን፣ ከቀዛቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ወዲህ የተሻለ የአብዮት ማጥኛ ዘዬ ሆኖ የወጣውን ሊበራሉን ሃቲት ስንተራንስ፣ የኢትዮጵያ አብዮት ከገጠመው አልያም ከሆነው የተለየ እንዲሆን መጠበቅ የሚቻል አይመስልም፡፡ “አብዮት ያለ ደም” እንደማይከወን ኀልዬቶችም ሆኑ የታሪክ መዝገቦች ከመመስከራቸው ባሻገር፤ ያ አብዮት በብሉይ ማኀበራዊ አብዮትነት ከተለካ፤ ከአቻዎቹ የፈረንሳይ፣ የሩሲያ እና የቻይና አብዮቶች የተለየ መንሸራተት እንዳልገጠመው ይነሳል፡፡

አቻቻይ ፖለቲካዊ ሥርዓት ያለመፈጠርን እና የሕዝባዊ መንግሥትን አለመምጣት መሰል ነጥቦችም ለዚሁ አብዮቱ ከሽፏል ለሚለው ክርክር በማሳያነት ይነሳሉ፡፡ ነገር ግን፣ የትኞቹም ማኀበራዊ አብዮቶች፣ በቀዳሚው እንቅስቃሴያቸው (መሰል አብዮቶች ቢያንስ ቀጣይ አብዮት እንደሚያዋልዱ ልብ ይሏል) እነዚህን የተጠቀሱ ጭብጦች አላዋለዱም እና የኢትዮጵያውኑንም የተለየ የሚያደርገው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ በቻይና ማኦ፣ በሩሲያ ሌኒን፣ በፈረንሳይ ናፖሊዮን እንደመጡት፤ በኢትዮጵያም መንግስቱ ኃይለማርያም መውጣቱ፤ እንደ ማኀበራዊ አብዮት ተጠባቂነት ስለሚኖረው፣ አብዮቱ አልተሳካም የሚለውን መከራከሪያ ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡ 

   የእነዚህ ሦስት ማኀበራዊ አብዮቶች አጥኚዎች በስፋት እንደሚከራከሩት፤ ማንኛውም ወደ ማኀበራዊ አብዮት የሚያዘግም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሁለት እርከኖች አሉት፡፡ የመጀመሪያው፤ የሥርዓቱን ምሶሶዎች የሚነቀንቀው እና ተቋማቱን ወደ ሁሉን አቻቻይነት ለመቀየር የማሻሻያ አማራጭን የሚከተለው ፖለቲካዊ አብዮት ነው፡፡ በዚህ ስያሜ እንደሚጠሩት የእንግሊዝ እና የአሜሪካ አብዮቶች እንዲሁም የቅርቡ የአረቡ ፀደይ ሁሉ፤ የዚህ መሰሉ አብዮት ግብ ገዢውን መደብ በሌላ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ወደሚያከብር ሥርዓት መቀየር እንደሆነ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ አውድም፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ፖለቲካዊ እና ሲቪል መሰል መብቶችን ወደሚያከብር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመቀየር ብቻ የተነሳሳ ንቅናቄ ቢሆን፤ እንደ ፖለቲካዊ አብዮትነቱ እነዚህን የሚያከብር ሥርዓት አላነበረምና በክሹፍነቱ ሊነቀስ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የአብዮቱ ሁለቱ መሠረታዊ ጥያቄዎች፣ እንቅስቃሴውን ከ የፖለቲካ አብዮትነት በላይ እንዲሻገር የሚያስገድዱ ነበሩ፡፡

የመሬት ላራሹ እና የብሄር እኩልነት ጥያቄዎች፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን ዲሞክራሲያዊ በማድረግ ብቻ የሚመለሱ አልነበሩም፡፡ በጭሰኝነት ፖለቲከ-ማኀበራዊ አወቃቀር ላይ የቆመውን ባላባታዊ ሥርዓት እና በአንድ ቋንቋ፣ ሰሜናዊ ባህላዊ ዕሴት እና በአንድ ሃይማኖት የበላይነት የተዋቀረችውን አገር፣ በሥር-ነቀልተኛ አመፅ ዳግም ማዋቀርን ግድ ማለቱ፤ እንቅስቃሴውን ከፖለቲካ አብዮትነት በላይ አሻግሮታል፡፡

ይሄ ነባራዊ እውነትም፣ የሂደቱን ሁለተኛ ዕርከን ወልዷል፡፡ ማኀበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አወቃቀሩን አፍርሰው በመገንባት የተሻለች ኢትዮጵያን እንደሚያዋልዱ ያመኑ ግራ-ዘመም  ምሁራን፣ ተማሪዎች እና የቢሮክራሲው አባላት፤ እንቅስቃሴውን ወደ ብሉይ አብዮትነት መርተውታል፡፡ እንደሌሎች አገራት አብዮቶች ሁሉ፣ ይኽኛው ሁለተኛው እርከን፤ የግራ-ቀኝ ልሂቃንን ደም አፋሳሽ ትንቅንቆችን መቀስቀሱ ነባራዊ ግዴታ ሆኗል፡፡ በትንቅንቁ ሂደትም፣ ሥር-ነቀልተኛ ልሂቃን የአብዮቱን የመጨረሻ ማኀተም ያሳርፋሉ፡፡ የኢትዮጵያው አብዮትም፣ የተነሳበትን ሁለቱን ዋንኛ ጥያቄዎች በሚገባ መልኩ ሥርዓታዊ ተካታችነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ማኀበራዊ አብዮቶች ግድ የሚሉትን ሂደቶች መጓዙን ተከትሎ የታዩትን ሁነቶች በመጥቀስ በክሽፈትነት ማንሳት ብዙም ረብ እንደሌለውም ይጠቅሳል፡፡ 

አብዮቱን ስናስታውስ፣ ደም ማፋሰሱን ብቻ እንዳንዘክር ሊያስጠነቅቀን የሚችለው፣ ራሱን ለማደስ ያልቻለ እና በተለይም በእኛ ሁኔታ በደቡብ እንደነበረው፣ የሰብዓዊነት መንጠፍ መለዮው የነበረው የመሬት ሥሪት እንዳይሻሻል አንቆ የያዘ ባላባታዊ ስብስብ፣ ይህንንም ለማስረገጥ ሌሎቹን የአገሪቷን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘ ገዢ ቡድን ባለበት፣ ‘ካለደም ስርየት የለም’ መንገድ ውጪ በምን መልኩ ሥርዓቱን መናድ ይቻል ነበር የሚለውን በካር ጥያቄ አውጋዦቹ አይመልሱም። አብዮቱ እስከዛሬ በሚተነተንበት ማርክሳዊ መነፅርም እንየው ካልን፣ ያየናቸው ጥቅል ውድመቶች አይቀሬ መሆናቸውን እንረዳለን።

እንደ ማርክስ ሙግት፣ አብዮቶች ታሪክ አዋላጅ እንደመሆናቸው ደም አፋሳሽነታቸው አይቀሬ ነው። ዘመኑን ባልዋጀ ሥልተ ምርት ላይ የቆመ ሥርዓት ወደ ጎን ተደርጎ፣ አዲስ ሥልተ ምርት እንዲበጅ እና ይህንንም የሚገሩ የፖለቲካ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዲቆሙ በሚደረገው ከባድ መደባዊ ትግል ውስጥ፣ በአብዮቱ ቀስቃሾች ያልታሰቡ አውዳሚ ሁነቶች የሚፈጥሩበት ዕድል እጅጉን ብዙ ነው።

አምስቱን የአብዮት መተንተኛ ኅልዮቶች አስመልክቶ መሳይ ከበደ በስፋት በሄደባቸው ገፆች እንደሚሟገተውም፣ ማኅበራዊ አብዮቶች መነሿቸው እጅጉን ውስብስብ፣ መገለጫዎቻቸውም የተለያዩ ከመሆናቸው አኳያም ነው፣ እስከአሁንም የአብዮቶችን መምጣት አስቀድሞ ይነግረን ዘንድ ኅልዮት ያጣነው። የትኞቹም ብሉይ አብዮቶች ርዕታዊ ማኅበረሰብ ሲፈጥሩ አልታየምና፣ የኢትዮጵያውም የተለየነት እንዲኖረው መጠበቅ፣ በዚህም ታላቁን ንቅናቄ ለማውገዝ መጣደፍ ሲያንስ ስለ ማኅበራዊ አብዮቶች አለመረዳት ነው የሚለውም የፈላስፋው የዙርዮሽ መከራከሪያ ነው። መሳይም እዚህች ወሳኝ ነጥብ ላይ ጠበቅ አድርጎ ሲናገር፣ ፖለቲካዊ አብዮትን ወደ ማኅበራዊ አብዮትነት የሚያሻገረው ርዕዮተ ዓለም ነው ይለናል። ነገር ግን ይላል መሳይ፣ ይሄ የርዕዮተ ዓለም ሚና ብቻውን ሳይሆን፣ ያልተለመዱ ጠባያት ያሏቸው እና ከሚሊነሪያን ባህል ውስጥ የመጡ ልሂቃን ንፅረተ-ዓለም ላይ ማረፍ አለበት ሲልም አበክሮ ፅፏል። [ፅሁፉ ከታች ይቀጥላል]

ሚሊነሪያን/ሚሊኒየማዊነት ግን ምንድን ነው?

የፕሮፌሰር መሳይ ከበደን መጸሐፍት እና ጹሑፎች በቅጡ የሚከታተል፣ ይሄ ንባበ-ቃል እጅጉን መደጋገሙን ያስተውላል። በተለይም፣ ርዕሰ-ጉዳያችን በሆነው አብዮቱ እና ቅደመ-አብዮቱ የተማሪዎቹ ንቅናቄ ትንታኔ ላይ፣ ፈላስፋው አብዝቶ ሲጠቀመው እናስተውላለንና፣ ጥቂት ማፍታቻ ሰጥተን እንለፈው።  

 ምንም እንኳን ማኅበራዊ አብዮቶች በቂ የማኅበረ-ፖለቲካዊ ጭቆናዎች እና ዓመፅ ቀስቃሽ ስር የሰደዱ ቁጣዎችን የግድ ቢሉም፣ ሁሉም ወደ አብዮት ያዘግም ዘንድ እጅጉን እንግዳ እና ከነባሩ ማኅበረ-ሥነ ልቦናዊ ውቅር አፈንግጠው የሄዱ ልሂቃንን ግድ ማለቱ እውነት ነው። እኒህ መሰሎቹ ልሂቃን ደግሞ፣ ወርዝቷል ያሉትን ሥርዓት ጥለው፣ እንገነባለን ያሉትን ተምኔታዊውን ዓለም ለሰፊው ሕዝብ አሳምነው ከኋላቸው ያሰልፉት ዘንድ፣ የመሲኅ ጥበቃ የገነገነበት ባህል መሠረታዊ ነው፤ ሚሊኒየማዊነት ይሉት ሐሳብም የሚመጣው እዚህ ሁነት ላይ ነው።  

በዚህ ሥራው መሳይ ባይጠቅሰውም፣ ከ20ኛው ክፈለ-ዘመን ስመ ጥሩ የማርክስ ተማሪዎች ከነበሩት አንዱ የሆነው ኤሪክ ሆብስባም፣ ”Primitive Rebels” በሚል ርዕስ፣ ስለ 19ኛው እና 20ኛው ክፈለ ዘመናት የአውሮፓ ማኅበራዊ ንቅናቄ መለዮዎች ባተተባት አነስ ያለች መጸሐፉ ንባበ-ቃሉን ለአማፂዎቹ መተንተኛ ጫፍ አድርጎታል። እንደ ነባሩ ማርክሲስት ገለፃ፣ ሚሊኒየናዊነት ንፅረተ-ዓለማቸው ላይ አሻራ ያለባቸው ልሂቃን፣ ሰይጣናዊ ብለው የጠሩትን አሁናዊዉን ዓለም ሙሉ ለሙሉ በመካድ፣ የተሻለ ዓለምን መናፈቅ መለዯቸው ነው።

ዘመናዊዎቹ ዓለማዊ አብዮታዊነቶች ሳይከሰቱ በፊት፣ ይህን መሰሉን ዓለማዊ ምልከታ የምናገኘው በጁዶ-ክርስትና ብቻ ሳይሆን አልቀረም የሚለን ሆብስባም፣ ብሉይ አብዮቶችም የሚቀሰቀሱት፣ በእነዚህ የሃይማኖት ስብከቶች በተነኩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ብቻ ነውም ሲል እስከመደምደም ሄዷል። ሐሳቡን መለስ ቀለስ እያለ ባብራራባት ይህች ኪስ ገብ መጸሐፉ፣ አሁን የምናየው ዓለም አንድ ቀን ያበቃል፤ በቦታውም ፍፁም ሰላም የሰፈነበት ሥነ-ዓለም ይተካል የሚለው፣ አጠር ያለው የታሪከ-ማርክሲዚም መምህሩ መደምደሚያ ሊሆንን ይችላል።

 መሳይም በዚህ መጸሐፉ፣ የታሪክ መምህሩን መርዕድ ወልደ አረጋይን ተንተርሶ እንደሚጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ሁሉ ድል አድርጋ በመጨረሻ የብቻ አሸናፊ እንደምትሆን የሚያውጀው ክብረ ነገሥት፣ ይህን ሚሊነሪያዊ ዕይታ በተለይም በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ስር ያደጉትን የወቅቱን አብዮተኞች ኅሊና በመሞረድ ግዙፍ አስተዋፅዖ አድርጓል። በዚያ የተገሩት አብዮተኞችም፣ የክርስትና መሲኅ ጥበቃን ወደ ዓለማዊ ገፁ ከመቀየር ባለፈ፣ ሰማያዊውን ዓለም ወደምድር እንደሚያወርዱት ለመስበክ፣ ለራሳቸውም፣ ለተከታዮቻቸውም ምቹ ሥነ-ልቦናዊ ድልዳል አግኝተዋል፤(አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ‘ትውልድ አይደናገር፣ እኛም እንናገር’ በሚለው ሥራው፣ ስለ ኢሕአፓው መሪ ተስፋዬ ደበሳይ ታላቅነት ሲያወሳ የተጠቀመው ርዕስ ‘ለካ! መሲሁ ሰው ነበረ’ የሚል መሆኑ ያፍታ ማሳያ ይሆነናል)።            

ስለመጨረሻው ቀን ፍርድ፣ የሰው ልጅ ዕጣ መደምደሚያ ስለሆኑት ገሃነም እና ገነት ቀን ተሌት የተሰበከበት ምኩራብ፣ ማርክሲዝም እዚሁ አበጃታለሁ የሚላትን ተምኔታዊዏን ዓለማዊ ሥርዓት ዛሬ እንደምትገነባ ለመቀበል የተመቸ መሆኑን ልብ ይሏል። በሌላ አነጋገር፣ የራሱ መሲኅ(ማርክስ)፣ የራሱ ዓማኞች(ላብ ዓደሮች) እና የራሱ ገነት(የላብ ዓደሩ አምባገነንነት የሰፈነበት አገረ-መንግሥት) አለው የተባለው ማርክሲዚም፣ ይህን መሰሉን በመሲኅ ጥበቃ የተቃኘ የወል ልቦና ሲያገኝ፣ ተደላድሎ ማረፉ ብዙም አስገራሚ አይሆንም። 

               አብዮት “መንቻፊው” ደርግ እና ሊቀመንበር መንግሥቱ

የኢትዮጵያን አብዮት እንግዳ የሚል ስያሜ ካሰጡት መገለጫዎቹ አንዱ፣ የደርግ ጉዳይ ነው። የደርግን ሚና እንዴት እንረዳው?፣ ስብስቡንስ ምን ብለን እንጥራው? የሚሉት እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ አብዮት አጥኚዎች ዘንድ ብዙ ሲያወዛግቡ ቆይተዋል። ደርጎቹ በበኩላቸው፣ አብዮቱን በፀረ-ኢትዮጵያ ኅይሎች ከመጠለፍ አዳንነው ባዮች ስለመሆናቸው የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን “እኛ እና አብዮቱ”፣ አልያም የጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ “ትግላችን”ን ገረፍ ገረፍ ማደረግ ብቻ ይበቃል። አብዮቱን “አዝጋሚው ሥዒረ-መንግሥት”፣ ደርግንም “መንበር መንቻፊው” የሚሉ ጸሓፍት መኖራቸውም፣ ከዚሁ ምሁራዊ ግራ ገብነት የሚነሳ ነው። እኒህን ጉዳዮች በቅጡ የተመለከታቸው መሳይ፣ “አብዮታዊው ተጨባጭ ሁነት ደርግን ከመፍጠር ይልቅ፣ ደርግ አብዮታዊ ሁኔታውን ፈጠረው” ሲል ከበድ የሚል ድምዳሜውን ያስነብበናል። ይህ መከራከሪያው ግን፣ በምላሹ ብዙ ክርክሮችን ሊቀሰቅስ የሚገባ የነበረ ቢሆንም፣ እንዲያው ሳይነሳ ማለፉ አስገራሚ ይመስላል። 

ደርግ እንዴት በአንድ ጀንበር ሶሻሊስት ሊሆን ቻለ? ለሚለው የብዙዎች ጥያቄም መሳይ በምላሹ ሲከራከር፣ በውስጥም በውጪም የገጠሙትን ተገዳዳሪ ኅይሎች እንደሚያስወግድለት እና በሂደቱም ፍጹም ሥልጣንን እንደሚሰጠው ማመኑ፣ ለአንድ አዳር ሶሻሊስትነቱ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ይነግረናል። በዚህ ሙግቱ በኩልም፣ አንድ የልሂቅ ስብስብ፣ እንዴት ከነባር ፍላጎቶቹ እና ከቆመበት ማኅበራዊ ቦታው በተቃረነ መልኩ ለሥር ነቀልተኛ ርዕዮቶች ሊገዛ የሚችልበትን እንቆቅልሽ ያፍታታልናል።

በአብዮቱ ዙሪያ ከተጻፉ መጻሕፍት ይህኛውን በሆነ መንገድ ለየት እንዲል የሚያደርገው ሌላይኛው ነጥብ፣ ‘አብዮቱን ጠለፈው’፣ ‘አበለሻሸው’ ወይም ጨከን ባለ አገላለፅ ‘የአብዮቱ የእንጀራ ልጅ’ እየተባለ በብዙ መጣጥፎች እና በተለይም ፓርቲ ተኮር መጻሕፍት ላይ ስም ሲሰጠው የቆየውን መንግሥቱ ኅይለ ማሪያምን ለመረዳት፣ ሳይኮባዮግራፊ የተሰኘውን የመተንተኛ መንገድ ለመጠቀም ያደረጋቸው ተወዳሽ ጥረቶች ናቸው።

በተለይም ራስ-አምላኪ (ናርስሲቲክ) ነው ላለው መንግሥቱ አምባገነንት፣ ጭካኔ እና ተጣጣፊነት ለማብራራት ሐሳቡ ጥሩ ጠቅሞታል። ግና፣ እርሱም እንደ ኅይለ ሥላሴ ለሥልጣኑ ማጠናከሪያ ሊጠቀምባቸው የፈለጋቸው መንገዶች በእርስ በእርስ ጦርነት አዳክመው ጣሉት። “ከዚህ ባለፈም” ይላል መሳይ ይህን ርዕሰ-ጉዳይ ባተተባቸው ገጾች፣ “መንግሥቱ በሶሻሊዝም ውስጥ የራሱን ትልቅነት የሚያበጅበት እና ለወደደው የጭካኔ ሂደት መንገድ አገኘ” ሲል ጠንከር ብሎ ፅፏል።

በዚህም እንዴት በታሪክ አጋጣሚ ከፊት የሚቆም የአንድ ሰው ባህሪያት፣ አብዮት መሰል ታላቅ የሰው ልጅ ክስተትን እጅጉን ሊወስን እንደሚችል በቂ ሐሳባዊ መተከዢያዎች ይሰጠናል። ለማሳያነት የታዋቂውን የማኅበረሰብ ጥናት ሊቅ ማክስ ዌበርን የቻሪዝማ ሃቲት ዕሴት አልባ መሆኑን ደህና አድርጎ ካብራራልን በኋላ፣ መንግሥቱንም በዚህ በኩል ሊመለከተው ጥሯል። የመንግሥቱን ቅጥ ያጣ የራስ-አፍቅሮት ስብዕና ሳንመረምር፣ የደርግንም ሆነ የራሱን የመንግሥቱን ውድቀት በምልዓት ማጥናት አንችልም የሚለው፣ ለተገባደደው ዝክር ቁዘማችን የተወረወረልን መላምት ነው።

“ጥልቅ የሥልጣን ፍቅር፣ አምባገነናዊነት፣ ከራስ ውጪ አለመመልከት እና ሌሎችን ለራስ የማይጠረቃ ፍላጎት መበዝበዝ” በሚል መልኩ ሚዛን ያጣ የራስ-አምልኮን ባፍታታበት አፍታ፣ በእርግጥም እኒህ ባህሪያት የኢሕድሪውን ፕሬዝደንት፣ የኢሠፓውን ዋና ጸሓፊ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጦር አዛዡን፣ የአብዮቱን የበላይ ጠባቂ፣ ጓድ ኮለኔል መንግሥቱ ኀይለ ማርያምን በሚገባ ይገልፁታል ይለናል። 

 A luta continua!

በዚያም በዚህም ብለን መለስ ስንል፣ ስለ አብዮቱ ከተስተዋሉ ጉድለቶች ሁለት ጉዳዮችን ማንሳት ግን ርዕታዊነት ነው፡፡ የመጀመሪያው እና ብዙውን ጊዜ ሰፋ ያለ ቦታ የማይሰጠው ጭብጥ፣ የአብዮቱ ከተማ እና ከተሜ ተኮር የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በዋጋ ንረት ግብታዊ ጅማሮውን ሲያገኝ፣ የተደረጉት ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎችም የተደራጁት በከተሜው ሠራተኛው እና የቢሮክራሲው መደብ ነበር፡፡

በቀጣይ ሲከወኑ የነበሩት ከፊል ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችም በዋናነት በዋና ከተማዋ ብቻ የተቀነበቡ መሆናቸው፣ ሰፋ ያለ ሕዝባዊ መሠረት እና አሳታፊነት ሳይኖረው እንዲካሄድ መደረጉ፣ ሊገኙ ይችሉ የነበሩ አገራዊ ጥቅሞችን አጉድሏል፡፡ በተለይም፣ አብዮቱ የተጠነጠነባቸው ጥያቄዎች ከከተሜው የማኀበረሰብ ክፍል ይልቅ የሰፊውን ገበሬ እና አርብቶ አደር ህልውና የሚመለከቱ ቢሆኑም፣ ያን ገበሬ የአብዮቱ ማኀበራዊ መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ አለመቻሉ ሁነቶችን በፍጥነት ወደ አሉታዊነት ቀይሯቸዋል፡፡

ይሄን የአብዮቱን መልክ፣ የአብዮቱ የተለየ ገጹ ሲል በትኅትና የሚጠቅሰው መሳይ፣ ተጠቃሿ የአብዮቶች አጥኚ ቲኄዳ ስኮፕኩል እንደምትለው፣ “በተለይም ገበሬውን ይዞ የታችኛው መደብን ማካተት ዋንኛው የአብዮት መልክ ነው” ከሚለው ሃቲት ማፍንገጡን በማስታወስ፣ ያ የኢትዮጵያ አብዮት በዋናነት ከተማዊ አብዮት አይኖርም የሚለውን መላምት በአፍጢሙ የደፋ ብሎታል። 

   ሌላኛው ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ጉድለት፣ አስቀድሞ የተደራጁ ስብስቦች አለመኖር ነው፡፡ ድርጅቶቹ ዘግይተው ለመምጣታቸው የአብዮቱ ግብታዊነት በምክነያትነት ቢነሳም፤ ዋንኛው ክፍተት ግን፣ አብዮተኞቹ ቅድመ-አብዮታዊ ነባራዊ ሁነቶቹ አብዮቱን እንደፀነሱ በሚገባ ካለመረዳታቸውም እንደሆነ መረዳት ይቻላል፤(በኢሕአፓ እና በመኢሶን መሪዎች መካከል በቅድመ-66 የነበረው አንዱ አታካች ክርክር፣ ኢትዮጵያ ለአብዮት ደርሳለች/አልደረሰችም የሚል እንደነበር ያስታውሷል)። እነርሱ ከታመኑለት ርዕዮተ-ዓለም አኳያም፣ የአብዮተኝነት መሠረታዊው መለዮ፣ ያሉት “አብዮታዊ ሁኔታዎች” አብዮቱን ለመቀስቀስ የሚኖራቸውን ድርሻ በቅጡ መገንዘብ መሆኑን ስናክል፣ ጉድለቱ የእንቅስቃሴው መፍጠን ብቻም ሳይሆን፣ የልሂቃኑ ከሁነቶቹ የነበራቸው አእምሯዊ ተነቃይነትም ጭምር እንደነበር እንገነዘባለን፡፡

  በመጨረሻም፣ የዋልዶ ኤመርሰንን፣ ‘የዓለምን ቤተ መጻሕፍት በሙሉ አቃጥሏቸው፤ የፕላቶ ዘ ሪፐብሊክ ካለ ይበቃል’ን ለዚህ መጸሐፍ እስከመጠቀም ባንታበይም፣ አብዮቱን በቅጡ ለመረዳት ግን፣ ይህን መጸሐፍ አለማንበብ ብዙ ያጎድላል።

ዝክራችንንም፣ የሞዛምቢኩ የፍሪሊሞ ንቅናቄ  መሪ፣ ኤድዋርዶ ሞንድላኔ ባበጀልን ዘላለማዊ ሐረግ እንዝጋ– A luta continua!

  አብዮት እና አብዮተኞች ለዘላለም ይኑሩ! 

ከታች ያለውን የምስል ዘገባ እንድትመለከቱ ጋብዘናል [ዋዜማ]