ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብቃት መመዘኛ ፈተና በተሰጠባቸው ተቋሟት ለሚገኙ ሠራተኞቹ፣ አዲስ የሥራ ድልድል ይፋ ማድረጉን ዋዜማ ሰምታለች።

የብቃት መመዘኛው ፈተና ውጤትን ተከትሎ የተሰራው አዲሱ የሥራ ድልድል ይገለፃል ከተባለበት ቀን ኹለት ሳምንት ገደማ ዘግይቶ፣ በኹሉም ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ይፋ የተደረገው ከአንድ ሳምንት በፊት ነመሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቅሰዋል። በአዲሱ የሥራ ድልድል መሰረት፣ የብቃት መመዘኛ ፈተናውን ወስደው ውጤት ካመጡት ሠራተኞች መካከል፣ በምርጫቸው የተመደቡ የመኖራቸውን ያህል፣ እስካሁንም ያልተመደቡ እንዳሉ ተረድተናል።

የማለፊያ ውጤት ቢያመጡም፣ በምደባው ያልተካተቱት ሠራተኞች ያልተመደቡባቸውን ምክንያቶች፣ የትምህርት ዝግጅታቸው ከመረጡት የሥራ መደብ ጋር የተራራቀ መሆን፣ በፈተናው ያገኙት የማለፊያ ነጥብ እና ከዚህ ቀደም በየስድስት ወሩ ይሰጣቸው የነበረው የብቃት መመዘኛ ውጤት ተደምሮ ዝቅተኛ መሆኑ፣ አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ የላቸውም የሚሉ እና የብሔር ተዋፅዕ መጠበቅ አለበት የሚሉ እንደሆኑ የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። 

አንድ የክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ጽኅፈት ቤት ሠራተኛ ለዋዜማ ሲናገሩ፣ “ከ70 በመቶ በላይ የሆነ የማለፊያ ነጥብ ባመጣም፣ የተመደብኩት ግን ከደረጃ 12 ወደ ደረጃ 9፣ ሦስት ደረጃ ዝቅ ተደርጌ ነው” ይላሉ። ይህም ከተቀመጠው የብቃት መመዘኛ መመሪያው አሰራር ውጭ መሆኑን የገለፁልን እኚሁ ሠራተኛ፣ ለሦስት የሥራ መደብ ብወዳደርም፣ አንዱን ቅድሚያ ለሴቶች፣ ኹለተኛውን ደግሞ ክፍት መሆን አለበት፣ እንዲሁም ሦስተኛው ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት የለህም በሚሉ ምክንያቶች ተከልክያለሁ ብለውናል። ከ10 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ኖሯቸው ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ የሚጠይቅ የሥራ መደብ ላይ የተመደቡ ሠራተኞች መኖራቸውንም ጨምረው ጠቅሰውልናል። የክፍለ ከተማው ግማሽ ያህሉ ሠራተኛ ቅሬታ ቢያቀርብም፣ ለብዙዎች “አግባብነት የሌለው ቅሬታ” የሚል ምላሽ ነው እየተሰጠ ያለው ሲሉም ቅሪታቸውን አሰምተዋል። 

እኚሁ ሠራተኛ ሲቀጥሉ፣ “ከፈተናው በፊት ማለፊያ ነጥብ ያመጡ ሠራተኞች ደረጃቸው ዝቅ እንደማይደረግ፣ ባሉበት አልያም ከፍ ወዳሉ የሥራ መደቦች እንደሚመደቡ የተነገረን ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒ የተመደቡ ሠራተኞች አሉ” ሲሉ ሁኔታውን በቅሬታ ያስረዳሉ።

ይህን የብቃት መመዘኛ ፈተና ውጤት ተከትሎ፣ ተግባራዊ እንዲሆን የታዘዘው፣ አንድ ወረዳም ሆነ ክፍለ ከተማ ካሏቸው የሥራ መደቦች ውስጥ 60 በመቶውን ብቻ በራሳቸው እንዲመደቡ እና ቀሪውን 40 በመቶ ደግሞ፣ ለወረዳው ክፍለ ከተማው፣ ለክፍለ ከተማው ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች እንዲመድቡበት የወጣው አቅጣጫም ቅሬታዎች እየቀረቡበት መሆኑን ሰምተናል። 

ስለዚሁ ጉዳይ ያነሱ፣ በተለይ ጠቃሚ በሚባሉ የሥራ መደቦች ላይ የአሰራር ግልጽነት ይጎድላል የሚሉት አንድ የዋዜማ ምንጭ በበኩላቸው፣ “40 በመቶ መደቡ ክፍት መሆን አለበት በሚል ምክንያት አንድ ሠራተኛ ኹሉንም መስፈርቶች አሟልቶም፣ እነርሱ የፈለጉበት ቦታ ወስደው ይጥሉታል” ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ምክንያትም፣ ማለፊያ ውጤት አምጥተው፣ ተዛማጅ የትምህርት ዝግጅት እና አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ ኖሯቸውም የሚፈልጉትን መደብ ያላገኙ እና እስከ አሁንም ሳይመደቡ የቀሩ ሠራተኞች መኖራቸውንም ዋዜማ ሰምታለች። 

በአንጻሩ የማለፊያ ነጥብ ባያመጡም፣ ቀድሞ በመመሪያ ደረጃ ከተነገረው በተቃራኒ አንድ ደረጃ ከፍ ብለው ጥሩ የሚባል የሥራ መደብ የተሰጣቸው ሠራተኞች መኖራቸውንም ያነጋገርናቸው ሠራተኞች ገልጸዋል። እንዲሁም የማለፊያ ነጥብ ሳያመጡ ከቀሩት መካከልም፣ ምድባ ያላገኙም እንዳሉ ሠራተኞቹ ጠቅሰውልናል።  

 አራት ዓመት የሥራ ልምድ ቢኖራትም፣ ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ወደ ሚጠይቀው የሥራ መደብ  የተመደበች ሌላ ሠራተኛ በበኩሏ፣ ካሳለፍነው ሰኞ ዕለት ጀምሮ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ደረስ ቅሬታ እንድናስገባ ተፈቅዶልናል ብላናለች። 

የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎቹም፣ የሠራተኛውን የብሄር ስብጥር ይወክላሉ በሚል ከኦሮሞ፣ አማራ እና ከተለያዩ የደቡብ ክልል ብሔሮች የተወጣጡ እና በሠራተኛው የተመረጡ መሆናቸውንም ጠቅሳለች። ማለፊያ ነጥብ ካላመጡ ሠራተኞች መካከል ከክፍለ ከተማ ወደ ወረዳ ዝቅ ተደርገው የተመደቡ፣ ወዳልመረጡት ወረዳ የተዛወሩ እንዲሁም ምደባ ያልተሰጣቸው ሠራተኞች መኖራቸውንም ለዋዜማ ገልጻለች።

የወንበር፣ የስልክ፣ የትራንስፖርት የሚሉ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሲያገኙ የነበሩ የሥራ ሂደት መሪዎችም፣ የማለፊያ ውጤቱን ባለማምጣታቸው ምክንያት፣ ባለሙያ ወደተሰኘው ደረጃ ዝቅ ተደርገው የተመደቡ መኖራቸውንም ዋዜማ ተረድታለች። ሠራተኞቹ የፈተና ወረቀታችንን ለማየት ቅሬታ ብናቀርብም፣ ያቀረባችሁት ቅሬታ አግባብነት የሌለው ነው በሚል ከተማ አሰተዳደሩም ሆነ ፈተናው በቀዳሚነት ያወጣው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቅሬታችንን  ውድቅ አድርጎብናል ሲሉም ክሳቸውን አሰምተዋል።

በአዲሱ የሥራ መደብ ድልድል መሰረት፣ የሥራ ደረጃዎች የደሞዝ ልኬት በአዲስ የሚሰላ ወይም ባለበት የሚቀጥል መሆኑ አለመሆኑም እስከ አሁን የታወቀ ነገር አለመኖሩንም ሠራተኞቹ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት ባደረጉ ባላቸው የተወሰኑ ተቋማት ላይ፣ የመጀመሪያ ዙር ያለውን የሠራተኞች የብቃት መመዘኛ ፈተና የሰጠው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ነበር። 

ስለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጠን ዓርብ ዕለት ጥያቄ  ያቀረብንለት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ወደፊት ዝርዝር ማብራሪያ ስለምንሰጥ አሁን በተናጠል ምላሽ መስጠት ይቸግረናል ሲል መልሷል። [ዋዜማ]