Yinager Dessie- Governor of NBE-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ውንብድና ለመቆጣጠር፣ የህገወጥ ገንዘብ ፍሰትን ለመከታተል እንዲሁም በተለያዩ የሽፋን ስሞችና የተጭበረበሩ ሰነዶች የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር ለማስቀረት ባንኮች አዲስ የባንክ መለያ መታወቂያ እንዲያዘጋጁ መታዘዛቸውን ዋዜማ ራዲዮ ስምታለች።


ሁሉም የንግድ ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት እና ሙሉ መረጃ አደራጅቶ ሊይዝ የሚችል የየባንኮቹ የራሳቸው የደንበኛ መታወቂያ ካርድ እንዲያዘጋጁ ብሄራዊ ባንክ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተረድተናል። ይህንን ለመስፈፀምም አጋዥ እንዲሆን ብሄራዊ ባንክ መመሪያ በማዘጋጀት ለባንኮች ባለፉት ቀናት እንዲደርስ ማድረጉን ዋዜማ ከባንክ ምንጮቿ ሰምታለች።


ዋዜማ ካገኘችውና ለባንኮች እንዲደርስ ከተደረገው የማስፈጸሚያ መመሪያ እንደተረዳቸው ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ አጣርቶ መረጃውን ለመቀመርና መታወቂያ ለመስጠት የ6 ወራት ግዜ ተሰጥቷቸዋል።


በቅርቡ ሁሉም ባንኮች በዚሁ መመሪያ አተገባበር ላይ ባደረጉት ስብሰባ ስራውን ለማጠናቀቅ የ6 ወር የግዜ ገደብ መቀመጡ በቂ አለመሆኑን በሀገሪቱ ግዙፍ ከሆነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወካዮች በስፋት መነሳቱን የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ።
ይህ አዲሱ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ደንበኞች ወደ ባንክ ሄደው ሂሳብ ሲከፍቱ ከሚሞሏቸውም መረጃዎች ተጨማሪ ዝርዝር የደንበኛን መረጃ ጭምር በማከል የሚዘጋጅ መሆኑን መመሪያው ጠቅሷል።


ከዚህ ቀደም ባንክች ደንበኞቻቸውን የሂሳብ ደብተር ሲከፍቱ ይጠየቁ ያልነበሩ መረጃዎች በአዲሱ አሰራር እንዲካተቱም ተደርገዋል። ለአብነት ያህል አንድ ደንበኛ የባንክ ደብተር የሚከፍትበት ምክንያትን እንዲያስረዳ የሚጠየቅ ሲሆን ከዚያም ባሻገር የእናት ስም እና ተጨማሪ የቤተሰብና የግል መረጃዎች እንዲሰፍሩ እንዲደረግም ያዛል።


ብሄራዊ ባንክ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ቀደም ሲል የግለሰቦችን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ እንደ ማመሳከሪያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው የቀበሌ መታወቂያ ቢሆንም ነገር ግን አንድ ግለሰብ በተለያዩ አካባቢዎች የነዋሪነት መታወቂያዎችን የመያዝ እድል ስላለው አስተማማኝ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ስለታመነበት ነው።


ይህ አዲሱ በብሄራዊ ባንክ በኩል እንዲተገበር መመሪያ የተላለፈበት የባንኮች ‘’የደንበኛ መታወቂያ’’ በአንድ ባንክ ውስጥ የተከፈቱ የአንድ ግለሰብን ከሁለት በላይ የባንክ ሂሳቦችን በአንድ በማጣመር ተደራራቢ የሆኑ የደንበኞችን መረጃዎች ማስቀረት አላማው እንዲሆነ ታሳቢ ተደርጓል።


በቀጣዮች ደግሞ እየታሰበ ያለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የመታወቂያ አገልግሎት (national ID) ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር በአንድ ባንክ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የሂሳብ ደብተሮችን ከማስተሳሰር ባሻገር፤ አንድ ደንበኛ በተለያዩ ባንኮች ያሉትን የሂሳብ ደብተሮች በማስተሳሰር በቀላሉ መረጃን ማደራጀት እንዲቻልም ታሰቧል።

ይህንን ሂደትንም በፍጥነት ለማጠናቀቅ ብሄራዊ ባንክ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው ዋዜማ ከብሄራዊ ባንክ ምንጮቿ የሰማችው። [ዋዜማ ራዲዮ]