Gonder City

ዋዜማ- የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ይቀርፋሉ ተብለው ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው ፕሮጀክቶች እንደታሰበው ስኬታማ አልሆኑም። 

የጎንደርን የውሃ ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የመገጭ ውሃ ግድብ ከታች ከመሰረቱ በኩል አፈሩ  መናዱንና የውሃ ስርገት መከሰቱን ዋዜማ ሰምታለች፡፡

በ2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ  ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ጎንደርን በጎበኙበት ጊዜ   የመገጭ ውሃ ግድብ ከስድስት ወራት በኃላ ተጠናቆ ስራ ይጀምራል ቢሉም እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡  እንደውም  ግድቡ ከስር አፈሩ መናድ መጀመሩን ዋዜማ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሃላፊዎች ሰምታለች፡፡

መገጭ ከጎንደር 20ኪሎሜትር የማይደርስ  ርቀት ላይ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነች፡፡ 2.4 ቢሊዬን ብር በመመደብና በዚህ አካባቢ የውሃና መስኖ ግድብ ለመገንባትና ለጎንደር ከተማ  1.8ሚሊዮን ሜትር ኪውብ ውሃ  ለማቅረብ ታቅዶ  በ2001ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ 13 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ውሃ ለአካባቢው ህብተረሰብ ማቅረብ ግን አልተቻለም፡፡

በአማራ ክልል የውሃ ልማት ፈንድ ፅ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ  የሆኑት አቶ አደም ወርቁ አሁን በቅርቡ በነበረ ቅኝት “የመገጭ ፕሮጀክት ከስር በኩል የመናድ አደጋ ገጥሞታል፡፡ ባለፈው አመት ሲሰራ የከረመው ግድብ በክረምት ውሃ ምክንያት ተንዷል፡፡ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብና ጊዜ ይጠይቃል” ብለዋል፡፡

ጎንደር  ከ20 አመታት በላይ በዋነኛነት ውሃ የሚያገኝው ከአንገረብ ውሃ ግድብ ነው፡፡ ይሁንና በ1994 ተጠናቆ ስራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ደለል ወደ ግድቡ ይገባል፡፡  አካባቢው የነበሩ ገበሬዎች እንዲነሱ አልተደረገም በዚህም ምክንያት ከላይኛው የመሬት ክፍል በሚከናወን  የግብርና ስራ አማካኝነት  ክረምት ሲመጣ ደለል በቀላሉ ወደ ግድቡ ይደርሳል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ከጎንደር ደባርቅ የመንገድ ስራ ሲሰራ ተጨማሪ ከፍተኛ ደለል ወደ ግድቡ በመግባቱ በሂደት ደለሉ  ከፍ እንዲል አድርጎታል  ፡፡

እንደ ባለሞያዎች ሀተታ ከመነሻው ደለል እንዳይገባ ማድረግ እንጅ ደለል መጥረግ አዋጭ አይደለም፡፡ እስከ 2013 ዓ.ም  3 ሚሊዮን ሜትር ኪውብ ደለል ተከማችቶ ነበር ፡፡

አሁን የአንገረብ ግድብ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በደለል በመሞላቱ ውሃ ለማቅረብ የሚችልበት አቅሙ እየተሟጠጠ ነው፡፡ ደለሉን ለመጥረግ ከሚደረግ ድካምና ወጪ ይልቅ አዲስ ግድብ መገንባት የተሻለ አንደሆነ ባለሞያዎች ያሳስባሉ፡፡ ይሁንና የከተማው አስተዳደር የደለል መጥረግ ስራ እያካሄደ ነው። 

አንገረብ ግድብን በተመለከተ የግድቡን ከፍታ መጨመር አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብ ቀርቧል፡፡ የግድቡን ከፍታ መጨመር ግን አዋጭ አለመሆኑንና መሰረቱ ተጨማሪ ክብደት መሸከም እንደማይችል ባለሙያዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡  

የጎንደር ከተማ ውሃና ፍሳሽ ፅ/ቤት ስራ አስኪያጅ  አቶ ወርቅነህ አያል የአንገረብ ውሀ ግድብ በ1994ዓም ሲጠናቀቅ በወቅቱ ለነበረው እስከ 300,000 ለሚደርስ ህዝብ ታቅዶ፣ ለ20ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባ ነበር ይላሉ፡፡ 

አሁን ባለው መረጃ የጎንደር ህዝብ ብዛት ከ700,000 በላይ ነው፡፡ ይህን ያህል የህዝብ ቁጥር ላለው  ከተማ ደግሞ ቢያንስ 70,000ሜትር ኪውብ ውሃ ያስፈልጋል፡፡ ማቅረብ የተቻለው ግን 13.000 ሜትር ኪውብ ነው ይህም 18 በመቶ ማለት ነው፡፡

ለጎንደር ከተማ ንፁህ ውሃ ከከርሰ ምድር ለማቅረብ በቆላድባ በ600 ሚሊዮን ብር የውሃ ፕሮጀክት የተሰራ ቢሆንም ውሃ ግን ለከተማዋ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ዋዜማ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ጥናቱ ከጅምሩ ችግሮች ነበሩበት፡፡  

ከጎንደር ውሃ አቀርቦት  ጋር በተያያዘ በተከታታይ፣ በሁሉም አማራጮች የታየው ትልቁ ክፍተት የጥናቶች ችግር ነው፡፡ የቆላ ድባ የከርሰ ምድር ውሃ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ያሳየው ውጤት በወቅቱ አጥጋቢ ነው ከተባለ በኃላ ስራው ተጠናቆ መሳብ ሲጀምር  ተጠና ወይም ተረጋጋጠ የተባለው ውሃ እንደተባለው አልተገኘም፡፡ 

ፕሮጀክቱ በተጀመረበት አመት ከታች በኩል ውሃ ሊያሰርግ እንደሚችል ባለሞያዎች ጠቁመው ነበር፡፡ ስራው ከተጀመረ አራት አመታትም በኃላ ይኸው ተመሳሳይ ሞያዊ አስተያዬቶች ቀርበዋል፡፡

የጎንደርን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል አሁን አስተዳደሩ  ጥናቶችን ቀድሞ ሊያከናውን መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች፡፡ [ዋዜማ]

የዋዜማ አዘጋጆችን በኢማይል አድራሻ wazemaradio@gmail.com ማግኘት ይችላሉ