ዋዜማ- በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ መቻሬ ሜዳ በሚባለው ቦታ በ50 ቢሊየን ብር ወጪ ቅንጡ የመኖሪያ አፓርታማን ጨምሮ የተለያዩ ማዕከላትን የያዘ አዲስ የፕሮጀክት ስራ መጀመሩን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
ይህ ፕሮጀክት በሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን የገበያ ማዕከል፣ ግዙፍ ሆቴልና አንድ ሺህ ሶስት መቶ የሚጠጉ አፓርትመንቶችና ዘመናዊ ቪላዎች የተካተቱበት ነው።
የሼህ መሐመድ አላሙዲ ንብረት በሆነው የሚድሮክ ግሩፕ ባለቤትነት የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት “መሐመድያ ሪል ስቴት ቪሌጅ” የሚባል ሲሆን ግንባታው የሚካሄደው አሁን የሚድሮክ ኩባንያዎች ባሉበት የመቻሬ ሜዳ ቦታ ላይ ነው።
በመቻሬ ሜዳ ሚድሮክ ወርቅን ጨምሮ 26 የሚድሮክ ግሩፕ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን 50 ቢሊየን ብር የሚወጣበትን መንደር ለመስራት በማሰብ 90 በመቶ የሚሆኑት ፈርሰው ግማሾቹ ግዮን ሆቴል ጎን ባለው ናኒ ህንጻ ቢሮ የተሰጣቸው ሲሆን ከፊሎቹ ጊዚያዊ ቢሮ ተዘጋጅቶላቸዋል ተብሏል።
የማዕከሉ ግንባታ አማካሪ መሰረቱን በአሜሪካ ቦስተን ያደረገው ዚአስ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ ኤንድ ኢንጂነርስ የተባለ ኩባንያ ሲሆን የግንባታው ፕላንም እንደጸደቀለት ነው የሰማነው።
በኢትዮጵያ በስፋቱ የመጀመርያ ይሆናል ተብሎ የተነገረለት ይህ የከተማ ማዕከል ግንባታ በውስጡ በርካታ የግንባታ ይዘቶች ይኖሩታል። የመኖርያ አፓርታማ ፣ ቅንጡ መኖርያዎች ፣ ቪላ ፣ ሲኒማ ቤት እና ሰፋፊ መዝናኛዎች በግንባታ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
ቤቶቹም ከተገነቡ በኋላ በኪራይ እና በሽያጭ ለገዢዎች ሊተላለፉ ይችላሉ። ቅልቅል ማለትም ለንግድ ፣ ለቢሮና መሰል አገልግሎት የሚውሉ ህንጻዎች እንዲሁም ህዝባዊ ሁነቶች የሚከናወኑባቸው ቦታዎችም በግንባታው የተካተቱ እንደሆነም ዋዜማ ራዲዮ ከሜድሮክ ግሩፕ ምንጮቿ ሰምታለች።
ተመሳሳይ አይነት መንደሮች ከዚህ ቀደም በጸሀይ ሪልስቴት እና መሰረቱን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ያደረገው ኤግል ሂልስ በአዲስ አበባ ለገሀር መጀመራቸው ይታወቃል። በለገሀር ያለው ኤግል ሂልስ በተለያየ ደረጃ የተሰሩ ቤቶችን እየሸጠ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
የዋዜማ ሪፖርተር እንደተመለከተው በ50 ቢሊየን ብር ወጭ ለሚሰራው የ “መሐመድያ ሪል ስቴት ቪሌጅ” የከተማ መንደር ግንባታ የሚያስፈልገው መሬት ጠረጋ በብዛት የተከናወነ ሲሆን በቅርቡ ዋናው ግንባታ ይጀመራል ተብሏል።
ሼህ መሐመድ አላሙዲ በሀገሪቱ እስካሁን ካደረጓቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው።
አላሙዲ በሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰቦች ዙሪያ ከተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ጋር ተያይዞ በሙስና ተጠርጥረው ከበርካታ የንጉሳውያን ቤተሰቡ አባላትና ባለሀብቶች ጋር በቅንጡ ሆቴል በቁም እስር ከቆዩ በኋላ ተለቀዋል።
ከቁም እስር ተለቀዋል ቢባልም እስካሁን በአደባባይ ሳይታዩ ቆይተዋል።
ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚድሮክ ግሩፕ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ የሚድሮክ ወርቅ አቋርጦ የነበረውን ስራውን ከፌደራሉና ከኣኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመነጋገር እንደገና ጀምሯል። [ዋዜማ]