ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ላይ “ዕልቂትና ውድመት”  ሊያስከትል ይችላል የተባለ የኬሚካል ክምችት መኖሩን መንግስት ራሱ አስታውቆ ነበር። ይህ አደገኛ የኬሚካል ክምችት አሁንም መፍትሄ አላገኘም። ዋዜማ ለምን ችግሩን ማስወገድ አልተቻለም?  ስትል ጠይቃለች። አንብቡት

ዋዜማ – በግልና መንግስት ተቋማት ወደ አገር ውስጥ ገብተው የመጠቀሚ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከሁለት አመት በፊት ተይዞ የነበረው አቅድ የዓለም ባንክና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ሊሰጡ ቃል የገቡትን ገንዘብ ባለመልቀቃቸው ኬሚከሎቹ አሁንም አደጋ እንደደቀኑ መሆናቸውን የመንግሥት  ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡

የኬሚካል ክምችቱ የተፈጠረው ከውጪ ሀገር ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገዝተው  በወቅቱ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፉ ነው።

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ለዋዜማ እንደገለጹት የተከማቹ ኬሚካሎቹን ለማስወገድ በ 2013 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አማካኝነት ጥናት ተደርጎ ለማስወገድ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ገንዘቡን ማግኘት ባለመቻሉ ከእቅዱ ተግባራዊ መሆን አልቻለም። 

‹‹ኬሚካሉን ለማስወገድ በጀት ይፈለጋል፤ ይህን በጀት ገንዘብ ሚንስቴር እፈልጋለሁ አለ፤ ነገር ግን  ገንዘቡ አልተገኘም ጉዳዩም ባለበት ቆሟል›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

ኬሚካሉን ለማስወገድ በጀት ከመንግስት መመደብ የማይቻል በመሆኑና ይህን ገንዝብ ማግኘት የሚቻለው ከአለም ባንክ  እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ቢሆንም፤ እነዚህ ተቋማት ባለፉት ሁለት አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥሩ ባለመሆኑ ገንዘቡ ተገኝቶ ኬሚካሉ ሊወገድ አልቻለም ብለዋል፡፡

አቶ ሃጂ እንደተናገሩት በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በክምችት ላይ ያለው ኬሚካል ለማስወገድ የሚረዳውን ገንዘብ ለማግኘት በገንዘብ ሚንስቴር የኢኮኖሚክ ትብብር ሚንስቴር ዴእታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ለሚመሩት ዘርፍ መመራቱን ተናግረዋል፡፡ 

ዋዜማ ስለጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቃቸው ወ/ሮ ሰመሪታ ጉዳዩን እናጣራለን የሚል መልስ በመስጠት ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡

የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ከፈነዱ በሰዎችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባሉት የግብርናና የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ሲሆኑ ዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌትና ኦርጋኖ ክሎሪን እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የክምችቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የጠየቅናቸው ባለሙያዎች አብዛኛው ክምችት አዲስ አበባ መሆኑንና ቀላል የማይባል ክምችት በክልል ከተሞች መኖሩን ነግረውናል። የክምችቱን መጠን በአሀዝ መግለፅ ግን አደጋውን የበለጠ አስፈሪ ከማድረግ በዘለለ ሌላ አደጋ ይጋብዛል  በሚል ከማብራራት ተቆጥበዋል። 

አቶ ሃጂ ከሁለት አመት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ተከማችተው የሚገኙት ኬሚካሎች በቶሎ ካልተወገዱ አደጋቸው የከፋ ሊሆን እንደሚቸል ተናግረው ነበር፡፡

በነሃሴ 2012 ዓ.ም በመካከከለኛው ምስራቅ ውስጥ በምትገኘው ሊባኖስ – ቤይሩት ባጋጠመ የ2,700 ቶን አሞኒየም ናይትሬት የተሰኘ ከባድ የኬሚካል ክምችት ፍንዳታ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማለፉን፣ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከአስራ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ውድመት ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ተከማችተው የሚገኙ ዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌትና ኦርጋኖ ክሎሪን ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከ4.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ [ዋዜማ]