Amhara IDP’s -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ኑሯቸው የተናጋ 11.6 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የነፍስ አድን ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ዋዜማ ከክልሉ መንግስት የግምገማ ሪፖርት መረዳት ችላለች። 

በክልሉ 2.3 ሚሊየን ወገኖች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ሲሆኑ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ደግሞ 9.3 ሚሊየን ያህል ናቸው።

በድምሩ 11.6 ሚሊየን ሰዎች ምግብ ፣ መድሃኒት ፣ የህፃናት አልሚ ምግብና የጤና አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል። 

የክልሉ አደጋ ስራ አመራር ከዓለም የምግብ ፕሮግራም(WFP) ፣ ከቀይ መስቀል፣ ከአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት እንዲሁም ከክልሉ ባለሀብቶች ጋር ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት ይገልፃል። 

የዕርዳታ አቅርቦቱ ከችግሩ አንፃር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ አሰቀድሞ ርብርብ መደረግ እንዳለበት የረድዔት ድርጅቶች እያሳሰቡ ነው። 

ከ2010ዓ/ም ጀምሮ በተፈጠረ ግጭት ተፈናቅለው በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኙ ከ290,000 በላይ ተፈናቃዬች በቅርቡ ዕርዳታው በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበልን አይደለም በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በክልሉ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ከ11.6 ሚሊዬን በላይ ዜጎች በመንግስት ችግሩ የከፋ መሆኑ ታምኖበት የተለዩ አካባቢዎች

  • ከ3 ሚሊዬን በላይ ደቡብ ወሎ፣ 
  • ከ2 ሚሊዬን በላይ በሰሜን ወሎ፣
  • ከ1ሚሊዬን በላይ በሰሜን ሽዋ ፣ 
  • ከ1.5 ሚሊዬን በላይ በደቡብ ጎንደር ፣ 
  • ከ800 ሽህ በላይ በዋግኸምራ ብሔረሰብ፣ 
  • ከ500 ሽህ በላይ በኦሮሞ ብሔረሰብ የሚገኙ ናቸው።

የትራንስፖርት አቅርቦት ዝቅተኛ መሆንና ከለጋሾች በኩል ችግሩን የሚመጥን ድጋፍ አለመገኘቱ ሁኔታውን አሳሳቢ እንዳደረገውም የክልሉ ምንጮች ይገልፃሉ።

በቀጣዩ አንድ ወር ሰፊ ርብርብ ካልተደረገ በክልሉ እጅግ አስከፊ ስብዓዊ ቀውስ ይከሰታል ብለው እንደሚሰጉ የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]