በተመሳሳይም 25ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ከድር አብዲ እስማኤል በዕርግጥም በክሱ ላይ የተጠቀሰው ስም የእራሳቸው እንደሆነ ለችሎቱ ቢገልፁም ክሱ ሲነበብላቸው ግን በክሱ የተጠቀሱትን የወንጀል ተግባራት ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን የሌላቸው ተራ አርሶ አደር እንደሆኑ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልክ የዛሬ አመት ከሰኔ 10 ጀምሮ በተለያዩ ስብሰባዎች እና heego waaheegan በሚል በፌስቡክ ድህረ ገፅ በኦሮሞ ወታደሮች ተወረናል፣ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታችንን ለቀው መውጣት አለባቸው፣ ነዳጃችንን መሬታችንን እና ወርቃችንን በጉልበት ሊወስዱብን ነው ፣የሶማሌ ተወላጆች ዛሬ ደማችሁ ሊፈላ ይገባል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት በርካታ አብያተ ክርስትያናት መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው የተባሉ የክልሉ የቀድሞ ከፍተኛ ሀላፊዎች እና ሄጎ የተባለ ቡድን አባላት ፤ በጥቅሉ 47 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና ለ ፤35፣38፣240/2 ስር የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል ዘቃቤ ህግ ክሱን በዝርዝር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከጅምሩ አንስቶ አቃቤ ህግ በቁጥጥር ስር አውሎ ማቅረብ የቻለው የክልሉን የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀመሰድ እና የሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ሀላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ረሀማ መሀመድን ጨምሮ 7 ግለሰቦችን ብቻ ነበር፡፡

ሰኔ 7 2011 ዓም የፌደራሉ ለፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በተሰየመበት ወቅት ደግሞ አቃቤ ህግ ሌሎች 8 ተከሳሾችን አቅርቧል፡፡ ይሁን እንጂ ከቀረቡት ተከሳሾች መሀል 22ኛ ተከሳሽ የሆኑት አብዲኑር መሀመድ አህመድ የአያቴ ስም የሱፍ ነው ያሉ ሲሆን 43ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ሀኒ ሀሰን ደግሞ ስሜ ዘምዘም ሀሰን ነውሲሉ ተከራክረዋል ፡፡ እንዲሁም 46ኛ ተከሳሽ የሆኑት ሻምበል አይዲድ በደል ራጌ ምክትል ኢኒስፔክተር አይዲድ ራጌ ነኝ በማለት ክሱ በእነሱ ላይ እንዳልቀረበ ፍርድቤቱ እንዲገነዘብላቸው ተከራክረዋል፡፡

በተመሳሳይም 25ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ከድር አብዲ እስማኤል በዕርግጥም በክሱ ላይ የተጠቀሰው ስም የእራሳቸው እንደሆነ ለችሎቱ ቢገልፁም ክሱ ሲነበብላቸው ግን በክሱ የተጠቀሱትን የወንጀል ተግባራት ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን የሌላቸው ተራ አርሶ አደር እንደሆኑ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

በስም መመሳሰል በስህተት ቀርበው እንደሆነ በማስረዳትም እንዲጣራ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥበት የጠየቀ ቢሆንም በዕለቱ አቃቤ ህግ ግለሰቦቹ እዚህ በችሎት ሲቀርቡ ስማቸውን እየቀየሩ እንደሆነ እና ምስክሮች የጠቆሙት እነሱን በመሆኑ በወንጀል የምፈልገው እነዚሁኑ ግለሰቦች ነው ብሎ ነበር፡፡

ሆኖም ተከሳሾች ከችሎቱ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ስለማንነታቸው የሚገልፅ መታወቂያ እና ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን ተከትሎ ችሎቱ ተከሳሾች ስለማንነታቸው ከአቃቤ ህግ በተሸለ ማስረዳት ችለዋል ብሏል ሆኖም በወንጀል የምፈልገው እራሳቸውን ነው በማለቱ የስም ማስተካከያ አድርጎ እነዚህ ተከሳሾች ላይ የተሻሻለ ክስ እንዲያቀርብ ለዛሬ ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ዛሬ ለተሰየመው ችሎት ከድር አብዲ የተባሉትን 25ኛ ተከሳሽ እሳቸው እንዳሉት በስህተት የታሰሩ ስለመሆናቸው ስላረጋገጥኩ እንዲለቀቁ ለፌደራል ፖሊስ ነግሬያለው ብለዋል፡፡

ችሎቱም ተከሳሹ ከእስር እንዲፈቱ እና ትዕዛዙ ዛሬውኑ ተፈፃሚ እንዲሆን ሲል ተዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አቃቤ ህግ በዛሬው እለት በቀደመው ቀጠሮ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ስማችን ተሳስቷል ባሉት ሶስት ተከሳሾ ላይ ክሱን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡

በዚህም 22ኛ ተከሳሽ የሆኑት አብዲኑር መሀመድ በክሱ ከተካተቱ እና የሄጎ አመራሮች ከሆኑት ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ሀምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ ሄጎ ተነስ እናሸንፋለን በማለት ህዝቡን ለአመፅ ሲያነሳሱ እና ሲቀሰቅሱ ነበር ሲል አቃቤ ህግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ዘምዘም ሀሰን ተብሎ ስሟ የተስተካከለው ሃኒ ሐሰን ደግሞ ሀምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ላይ ለጊዜው ስማቸው በውል ተለይቶ ያልታወቁ ብዛት ያላቸው የሄጎ አባላቶችን 13ኛ ተከሳሽ ከ መሀመድ አህመድ /መሀመድ ድሬ/ ጋር በመሆን እየመሩ ይዘው በመምጣት በከተማው የሚገኘውን ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን በእሳት ሲያቃጥሉና የሄጎ አባላቶችም እንዲያቃጥሉ እንዲሁም የተለያዩ ንብረቶች እንዲዘረፉና እንዲያወድሙ ትዕዛዝ በመስጠት የተሳተፉ መሆኑን በችሎት የተነበበው ክስ ያስረዳል፡፡

እንዲሁም ም/ል ኢንስፔክተር አይዲድ ራጌ ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ በሆነ ቀን በግምት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በሶማሌ ክልል ዙሪያ ፊቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በከተማው ተነስቶ በነበረው ረብሻ ኢ/ር ናትናኤል ታምራት፤ካሳሁን ወንድሙ ፤አባይ ወልዴ ዲጎም እና ሌሎች ሁለት ስማቸው የማይታወቁትን ለይተው በመኪና ጭነው ከወሰዷቸው በኋላ አንቀው በመኪና በመጎተትና በላያቸው ላይ መኪና እንዲሄድባቸው በማድረግ በአሰቃቂ ሁኔታ ሥጋቸው ፈራርሶ እና ተቦጫጭቆ ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ በዓመፁ ውስጥ ተሳትሰዋል ሲል አቃቤ ህግ ክሱ ላይ አስረድቷል፡፡

ክሱ ለተከሳሾች በሶማለኛ አስተርጓሚ አማካኝነት እየተተረጎመ ከተነበበላቸው በኋላ ተከሳሾች ድርጊቱን ስላለማድረጋቸው እና አቃቤ ህግ ስም አስተካክሎ የሌላ ሰው ክስ እነሱ ላይ ማቅረቡ አግባብ አይደለም በማለት ቢከራከሩም ችሎቱ እንዲህ ያለው ክርክር በማስረጃ የሚለይ ነው ሲል መምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡

በቀረበባቸው ክስ ላይም የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያ ካላቸው እስከ ሰኔ 29 ድረስ በጠበቆቻቸው አማካኝነት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በዚህ ክስ ላይ ተካተው ክሳቸው ቀደሞ የተነበበላቸው አቶ አብዲ መሀመድ እና ሌሎቹ ተከሳሾች ቀደም ብለው መቃወምያ ማስገባታቸውን እና አቃቤ ህግም ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በዚህ ላይ ምርምሮ ብይን ለመስጠት ችሎቱ አስቀድሞ ለሀምሌ 11 2011 ዓም ቀጠሮ ይዟል፡፡