Gov Forces in Moyale - Photo SM
Gov Forces in Moyale – Photo SM

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ሞያሌ ከተማ  በገሬና በቦረና ጎሳ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ አስራ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

ትናንት በተከሰተው በዚህ ግጭት አስራ ሶስት ሰው ከኦሮሚያ ቦረና ጎሳ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ከገሬ ጎሳ መገደላቸውን መረጃ እንዳላቸው በአካባቢው የሚንቀሳቀስ የረድዔት ድርጅት ሀላፊ ለዋዜማ ተናግረዋል።
የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል ያሉት ሀላፊው በአካባቢው ባለው ዉጥረትና የመገናኛ አውታር ችግር ሳቢያ ስለደረሰው ጉዳይ ያለን መረጃ ውሱን ነው ብለዋል።

በግጭቱ በረካታ ሰዎች ወደ ኬንያ መሸሻቸው እየተነገረ ነው።
የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ጣልቃ ገብተው ለማረጋጋት እየሞከሩ መሆኑንም ሀላፊው ተናግረዋል።

ግጭቱ በተፈጥሮ ሀብት ሳቢያ ይሁን በቅርቡ በተባባሰው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ፖለቲካዊ መማረር ባለው የድንበር ይገባኛል በግልፅ አልታወቀም። ይሕ ግጭት በአካባቢው ህዝብና በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች መካከል የተከሰተ እንደሆነም የሚናገሩ አሉ።

ገሬና ቦረና ጎሳዎች ለረጅም አመታት በግጦሽ መሬት በውሀና በከብት ዝርፊያ የሚፋለሙ ጎሳዎች ናቸው።
የሶማሌ የገሪ ጎሳ አባላት ከሶማሊያ (ሞቃዲሾ)  በቀላሉ በሚገኝ የጦር መሳሪያ የሀይል የበላይነቱን እየያዙ በመምጣታቸው ወደ ቦረና እየዘለቁ ጥቃት ማድረሰ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ከአስራ ሶስት አመት በፊት ለአምስት ቀናት በቆየ ግጭት ከሁለት መቶ የሚበልጡ ስዎች ተገድለዋል።
በወቅቱ በመሀል ሀገር በምርጫ ውጤት ሳቢያ ውዝግብ ውስጥ የነበረው ኢህአዴግ ግጭቱን ማስቆም ባለመሞከሩ ሳቢያ በርከት ያለ ህይወት እንዲጠፋ ሰበብ ሆኗል።