ዋዜማ ራዲዮ- ከቅርብ ግዜ ወዲህ በትግራይ ክልል ርእሰ መዲና በመቀሌ የመሬትና የመኖሪያ ቤት ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት እየናረ መምጣቱን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። በከተማይቱ ያነጋገርናቸው በድለላ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ አከራዮችና ነዋሪዎች እንደነገሩን የመሬትና የመኖሪያ ቤት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ንሯል። ባለፈው አንድ አመት የመኖሪያ ቤት ግዥ ፍላጎትና የተከራዮች ቁጥር ከሌላው ጊዜ ላቅ ብሎ መታየቱን በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ነግረውናል።

ለአብነት ያህል 200 ካሬ ሜትር ህጋዊ ካርታ ያለው ቦታ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር እስክ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር እየተሸጠ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ይህ የዋጋ ሁኔታ በተለይም በከተማዋ ከሚገኙት ክፍለተሞች መካከል አንዱ በሆነው ሓወልቲ ውስጥ ዓዲሽም ዱሑን አካባቢ ፍላጎቱ ከፍ ብሎ እንደሚታይም ነው ምንጮቻችን የሚናገሩት፡፡

የመቀሌ የመሬት የዋጋ ንረት በኣአንዳንድ አዲስ አበባ አካባቢ ካሉ አካባቢዎች የሚወደደር ሆኗል። ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ ባደረግነው ስሌት የመሬት ዋጋ 25 እስከ 30 በመቶ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ከ19 እስከ 22 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
በመቀሌ የመኖሪያ ቤት ኪራይም ከዕለት ዕለት እየናረ መምጣቱንና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ከከተማዋ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ለመኖር እየተገደዱ መሆኑን የዋዜማ ዘጋቢ ተመክታለች።

በአካባቢው ያለው የመኖሪያ ቤት እና የመሬት ሽያጭ ማስተወቂያዎች በማህበራዊ ድህረ ገጾች ሳይቀር የተጧጧፈ ሲሆን ዝግጅት ክፍላችንም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ማስታወቂያዎችን በስፋት ለመቃኘት ሞክሯል፡፡ የቦታውን መገኛ አድራሻ እና የቦታውን መጠን እንዲሁም የዋጋ ሁኔታ በግልፅ የተገለጸባቸውና ለፌስቡክ የተከፈለባቸው(Sponsored) የትግርኛ ቓንቃ ማስታወቂዎች በማህበራዊ ድህረ ገጾች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡

ከከተማዋ ወጣ ባሉ ደብሪን በመሳሰሉ አዳዲስ አካባቢዎች ጭምር የመኖሪያ ቤት እና የቦታ ግብይቱ ተመሳሳይ ገጽታ እንዳለው ኑሮአቸውን በከተማዋ ያደረጉ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡