ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ለከፍተኛ ችግርና ኪሳራ የዳረጉት የቀድሞና የአሁን አመራሮች ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት የተዘጋጀው ሰነድ ከሁለት ዓመታት በኋላም አስታዋሽ አላገኘም። ለወንጀል ክስ የተዘጋጀው ሰነድ ሆን ተብሎ ተድበስብሶ እንዲቀር መደረጉንም ዋዜማ ራዲዮ ከተለያዩ ምንጮች መረዳት ችላለች።

በቀድሞና የአሁን የባንኩ አመራሮች ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት ሰነድ የተዘጋጀው በ2010 አ.ም የአጣሪ ቡድን ተቋቁሙ ከባንኩ የብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተሰሩ የህግ ጥሰቶች ላይ ማጣራት ከተደረገ በሁዋላ ነው።     

የልማት ባንኩ እስከ 20 ቢሊየን ብር ድረስ የተበላሸ ብድር ተከማችቶበት እንደነበር የሚታወስ ነው።የዚህ ከፍተኛ የተበላሸ ብድር መከማቸት ዋናው ምክንያትም ለተለያዩ ኩባንያዎች ብድር የሰጠበት መንገድ ከፍተኛ የተጠያቂነት ችግር የነበረበት እንደሆነ ዋዜማ ራዲዮ ለወንጀል ክስና ለዲሲፕሊን ቅጣት ከተዘጋጀው ሰነድ መመልከት ችላለች።

የተዘጋጀው ሰነድ 80 ተበዳሪዎችን እና ብድሩ ሲሰጥ የታዩ የህግ ጥሰቶችን ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳትፈው የነበሩ አመራሮችንና ሙያተኞች ስም ዝርዝር ፣ የእያንዳንዳቸው አመራሮችና ሙያተኞች በእያንዳንዱ የህግ ጥሰት በተስተዋለበት ብድር ውስጥ የነበራቸው ሚናም በዝርዝር ተቀምጦበታል ። ዋዜማ ራዲዮ ከፍተኛ የብድር አሰጣጥ ብልሽት ችግር ከታየባቸው የተበዳሪዎች መረጃዎች ውስጥ የተወሰኑትን ተመልክታለች።     

ለኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተሰጠው ብድር ላይ የታየው ከፍተኛ ችግርና በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ

ይህ ኩባንያ በጥቅሉ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ብድር ወስዶ ሳይከፍል የፋብሪካው ባለቤቶች ከሀገር ወጥተዋል።ለዚህ ኩባንያ ባልተገባ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እንዲሰጥ ያደረጉ የልማት ባንኩ 34 የቀድሞ እና የአሁን አመራሮች እንዲሁም ሙያተኞች በወንጀል እንዲጠየቁ በሚል የፈጸሙት ዝርዝር የህግ ጥሰቶች ተቀምጠዋል።የባንኩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባህረ ፣ የብድር አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትና አሁን ብርሀን ባንክ ውስጥ በሀላፊነት ያሉት ታደሰ ሀጢያ ፣ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ፣ አቶ ደረጀ አውግቸው ፣ አቶ ጌድዮን መኮንን ፣አቶ ጸጋዬ ንጉሴ እና አቶ አክሊሉ ደስታ ለኤልሲ አዲስ በተሰጠ ብድር በተፈጸመ የህግ ጥሰት ውስጥ እጃቸው አለበት ከተባሉትና በወንጀል ይጠየቁ ከተባሉት 34 ግለሰቦች ውስጥ ይገኙበታል።     

ስማቸው ለኤልሲ አዲስ በተሰጠ ብድር የህግ ጥሰት ውስጥ የተጠቀሱ ግለሰቦች ኩባንያው ከቱርክ ነቅሎ ያመጣቸው ማሽኖች ግምታቸውን ማሰራት ሲኖርባቸው ሳያሰሩ በደፈናው ማሽኖቹ የተበዳሪው መዋጮ እንዲሆን ፈቅደዋል ፣ ለቱርኩ ኤሌሲ አዲስ ልዩ የስራ ማስኬጃ በድምሩ 252 ሚሊየን ብር ብድር ሲፈቀድ የልማት ባንኩ የብድር አጽዳቂ ኮሚቴ ማጽደቅ ሲገባው አቶ ታደሰ ሀጢያና አቶ ኢሳያስ ባህረ ብቻ ተመካክረው ብድሩን ፈቅደዋል ይላል ሰነዱ። ይህም ብቻ ሳይሆን ለኩባንያው ብድር እንዲራዘም ሲደረግበት የነበረበት መንገድም ህግን የጣሰ መሆኑን ተረድተናል ።

እንዲሁም በሌላ ጊዜ ለተመሳሳይ ኩባንያ 95 ሚሊየን ብር የስራ ማስኬጃ ብድርን ከመመሪያ ውጭ በውስጥ ማስታወሻ ሲሰጥም ከ34ቱ ውስጥ የተጠቀሱት ግለሰቦች እንደተሳተፉም ሰነዱ ይገልጻል። ኤልሲ አዲስ የተሰኘው ኩባንያ ለሚሰራው ኢንቨስትመንት ከራሱ የሚያዋጣውን ገንዘብን በስራ ላይ ማዋሉ ሲረጋገጥ የልማት ባንኩ ብድር እንዲለቀቅለት ቢጠበቅም ኩባንያው የራሱን መዋጮ ላይ ማዋሉ ሳይረጋገጥ የባንኩ ብድር እንዲለቀቅለትም ተደርጓል ተብሏል። ለቱርኩ ኤልሲ አዲስ በተሰጠ ብድር ላይ ከተገለጸው ውጭ በ34 ቱም ግለሰቦች የተፈጸመው በርካታ ህግ ጥሰቶችና የየግለሰቦቹ ተሳትፎ ተገልጾ  በወንጀል እንዲጠየቁም የተዘጋጀው ሰነድ መክሯል። ሆኖም እስካሁን የተጠየቀ የለም።     

አምብሮሲያ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የማርና ሰም ማምረቻ ፕሮጀክት

28 ግለሰቦች ለዚህ ኩባንያ ከተሰጠ የህግ ጥሰት ያለበት ብድር ጋር ስማቸው የተያያዘ ሲሆን አቶ ኢሳያስ ባህረና አቶ ታደሰ ሀጢያ እዚህም ጋር ስማቸው ተጠቅሷል።አቶ ወንደሰን ተሾመ ፣ አቶ በድሉ አሰፋ ፣ አቶ ዮሀንስ በላቸው ፣ አቶ ለገሰ ከበደ ፣ አቶ ደርቤ መንገሻና አቶ ገዛኸኝ ምትኬ የተባሉ ግለሰቦችም አምብሮሲያ የተሰኘው ኩባንያ ካገኘው ብድር የህግ ጥሰት ጋር በተያያዘ የወንጀል ተጠያቂት እንዲሆኑ ተመላክቶ ነበር።     ኩባንያው 61 ሚሊየን ብር ለስራ ማስኬጃ ብድር ሲሰጠው በሁለት አመት ሊመልሰው ሲገባ በህገ ወጥ መንገድ መመለሻው በሰባት አመት እንዲሆንለት ሲደረግ ከ28ቱ ግለሰቦች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው እንዳሉ ተገልጿል።

እንዲሁም ለዚህ ኩባንያ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ተጨማሪ ብድር ሲፈቀድለት የራሱን መዋጮ መጠየቅ ሲገባው አንድም ጊዜ እንዲጠየቅ አልተደረገም። በሌላ በኩል ለአምብሮሲዮ ኩባንያ ለተለያዩ ግብአቶች ብድር ይለቀቅ እንጂ ገንዘቡ የተባለው ግብአት ላይ ባለመዋሉም ከዚህ የህግ ጥሰት ጋር ስማቸው የተያያዙ ግለሰቦች በወንጀል እንዲጠየቁም ተወስኖ እንደነበር የተመለከትነው ሰነድ ያሳያል።     

የአይካ አዲስን ጨምሮ የ80 የህግ ጥሰት የተፈጸመባቸው የብርድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ ያላቸው የቀድሞና አሁንም ያሉ የባንኩ አመራሮችና ሙያተኞች እንደተሳትፎ መጠናቸው በወንጀል እንዲጠየቁ መረጃ ቀርቦባቸዋል። ሆኖም በልማት ባንክ ላይ ለደረሰው ጥፋት የህግ ተጠያቂነት እንዳይመጣ ሰፊ የማድበስበስ ስራ ሲሰራ እንደቆየ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

በተለይ ከሁለት አመት ወዲህ በስራ ላይ ያለው የልማት ባንኩ ቦርድ ለባንኩ ኪሳራ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች የወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ ፍላጎት እንዳለው ቢሰማም ብዙም ርቀት አልሄደም። ከልማት ባንኩ ውስጥም ይሄው ተጠያቂነት እንዳይመጣ የሚሰሩ እንዳሉም ሰምተናል። ዋዜማ ራዲዮ የተመለከተችው በባንኩ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ተመቸው የተጻፈ ምክረ ሀሳቤም የወንጀል ተጠያቂነት ቢቀር የሚል ነው። በግለሰቦቹ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲተገበር መረጃዎቹ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ተልኮ እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎችን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። ሆኖም መረጃውን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ማጣራት አልቻልንም።

መንግስትም በልማት ባንኩ ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጥፋት የህግ ተጠያቂነት እንዲመጣ ከመፈለግ አንጻር ጠንካራ አቋም ያለው አይመስልም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ልማት ባንኩ ስር ነቀል ማስተካከያ ካላደረገ ድጋፍ አይደረግለትም ብለው ነበር። ሆኖም በቅርቡ ባንኩ ላይ ስለተደረገ ተጠያቂነት ሲጠየቁ  ; ማስተካከያዎች እንዲደረጉ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ነገር ግን አቃቤ ህግን ማዘዝ እንደማይችሉ ገልጸዋል። ለባከነው የባንኩ ገንዘብ ተገቢው ተጠያቂነት ሳይመጣም ልማት ባንኩ በቅርቡ ተጨማሪ 21 ቢሊየን ብርን ለካፒታል ማሳደጊያነት እንደጸደቀለት የሚታወስ ነው።[ዋዜማ ራዲዮ]

To reach the editors, write to wazemaradio@gmail.com