Demeke Mekonen- DPM and Foreign Minister

ዋዜማ ራዲዮ- ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ ካደረገችው የመሬት ወረራ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ለተሰየመው የህወሃት ቡድን መቀመጫ በመሆን እያገለገለች ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከሰሰ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮነን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተቋማቸውን የ9ኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም አቅርበዋል፡፡

አቶ ደመቀ በሪፖርታቸው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ህዝብ ከሱዳን ህዝብ ጋር ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በጣም የተሳሰረ ቢሆንም ሁለቱ አገራት በሚጋሩት የወሰን የይገባኛል ጥያቄ አለመግባባት መኖሩን አመልክተዋል።፡፡

ይሁን እንጅ ችግሩን ለመፍታት የተዘረጋ የጋራ መስመር ቢኖርም የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሰሜኑ ጦርነት ፊቱን ባዞረበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ በመውረር የአካባቢውን ማህረሰብ በማፈናቀል ሃብት ንብረት በመውረርና በማውደም ከፍተኛ ጫና እያደረሰች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ይህ የሱዳን ወረራ አደገኛ ውጤት ሊያሰከትል ስለሚችል ኢትዮጵያ ለሰላማዊ መፍትሄ በሯን ከፍታ እየጠበቀች መሆኗን አቶ ደመቀ ለምክርቤቱ አስረድተዋል፡፡

የድንበር ወረራው አልበቃ ብሎ በስደተኛ ስም የገቡ የህወሃት አሸባሪ ቡድን አካላት መቀመጫቸውን በሱዳን  አድርገው በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ በመሆኑም ይህ  ለጠላት መቀመጫ መሆን በራሱ እንደመውጋት ይቆጠራል ብለዋል ፡፡

በተመሳሳይ አቶ ደመቀ በሪፖርታቸው በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው አካባቢ ባሉ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ተመልካች ሆና ልትቀጥል አይገባም፣ ሚናችን ወሳኝ መሆን አለበት ያሉት ሲሆን ለዚህም ሚንስቴሩ መርህ አስቀምጦ በአመታዊ በዕቅዱና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጅ  ጉዳዮች ውስጥ አካቶ በትኩረት እየተከታተለና እየሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቀጠናው ባሉ እንቅስቃሴዎች ሁነኛ ተዋናኝና ተሳታፊ መሆን ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ በተለይም በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው የቀይ ባህር ፎረም ኢትዮጵያን ያገለለና በመሆኑ ሀገራችን ጉዳዩን በትኩረት እየሰራችበት እንዳለች አስረድተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]