Getachew Reda- Head of Tigray regional admin

ዋዜማ ~  የኢትዬጵያ ምርጫ ቦርድ –  ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ከህወሓት የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ ፡፡

ቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ሕወሃት ከምዝገባ ያሰረዘውን “ሐይልን መሰረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ላይ መሳተፉን” መሰረት በማድረግ ነው።

ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ ውሳኔ ያሳለፈው  ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።

 ቦርድ በወቅቱ ባሳለፈው ውሳኔ የፓርቲው ሀላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ና የፓርቲው ንብረቶችም ምናልባት ፓርቲው እዳ ካለበት በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት እዳውን ለመሸፈን እንዲውል  ውሳኔ አሳልፎ ነበር ።

የተረፈ ገንዘብና ንብረት ካለም በክልሉ ለመራጮችና ለስነዜጋ ትምህርት እንዲውል የሚሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል ።

ህውሃት ከሰሞኑ ለምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ አሁን በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላማዊና በሕገ-መንግስታዊ መንገድ እንዲፈታ ተወስኖ የተኩስ አቁም እርምጃም በመወሰዱ ሳቢያ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲሰረዝ ያደረገው የቦርዱ ውሳኔ እንዲነሳለት ጠይቋል ፡፡

በፓርቲው አባላት ላይና በንብረቱም ላይ የተላለፈው ውሳኔም እንዲነሳለት ህወሃት ለ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ ጠይቋል። ይህንኑ ጥያቄ መሰረት በማድረግም ቦርዱ ትናንት ስብሰባ በማካሄድ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል ፡፡ 

 ቦርዱ “ለቀረብልኝ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ መሰረትና ድጋፍ አላገኘሁም” ብሏል። ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔም የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ድንጋጌ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንደሌለ በመግለፅ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ 

 ህጉን መሰረት አድርጎ ሊፈቅድለትና ሕጋዊ ሰውነት ሊኖረው የሚችለው፣ ህወሃት እንደገና ፓርቲ ሁኖ ለመቋቋም እንደ አዲስ ተደራጅቶና ፊርማ አሰባስቦ ጥያቄ ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል ፡፡

በተጨማሪም የፓርቲው አመራሮች በህወሐት ስም እንዲንቀሳቀሱ ያቀረቡት ጥያቄ በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት ፍቃድ ነፍጓቸዋል። ንብረቱንም በተመለከተ የቀረበው “የይመለስልኝ ጥያቄ” ፓርቲው የመሰረዙ ውጤቶች አካል በመሆኑ እንደ አዲስ ሊነሳ የሚችል   ጥያቄ አለመሆኑ አስታውሶ ከህወሐት የቀረበለት ጥያቄ ውድቅ አድርጓል ፡፡

ህወሐት ፓርቲ መሆኑን እውቅና እንዲሰጠው ከተፈለገ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎችን በአግባቡ መተግበር ይኖርበታል ብሏል። [ዋዜማ]