ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያልተመለሰለትን ብድር ለማስመለስ የ170 እርሻ አልሚ ተበዳሪዎቹን የብድር ማስያዣ በሀራጅ ለመሸጥ ቢወስንም ውሳኔውን ማስፈጸም አልቻለም።

  ልማት ባንኩ የካቲት 28 ቀን 2011አ.ም ነበር በባንኩ ምክትል ፕሬዚዳን አቶ ተሾመ አለማየሁ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ ፣ በዝናብ የሚለሙ እርሻዎች የብድር ሁኔታቸው መልካም ባለመሆኑ ፣ የባንኩንም ያልተመለሰ ብድር ከፍ ስላደረጉት 170ዎቹ የተበደሩ የባንኩ ደንበኞች ደግሞ ብድራቸው ጤናማ ስላሆነ ማስያዣቸው በሀራጅ እንዲሸጥወስኖ ነበር። ዋዜማ ራዲዮ የዚህ ደብዳቤ ቅጅ እስከ 170 ተበዳሪዎቹ ስም ዝርዝር ደርሷታል።

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ, ልማት ባንክ መሰረታዊ ለውጥ ካላመጣ ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይደረግለት ባስጠነቁቁ ማግስት ነበር። ሆኖም የ170 እርሻ አልሚዎች የብድር ማስያዣ በሀራጅ እንዲሸጥ የደረሰውን ውሳኔ እስካሁን ለማስፈጸም ስራ አልጀመረም።ይህም ንብረታቸው ለብድር ማስያዣነት ያስያዙ ተበደሪዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለተለያዩ የመንግስት አካላት የውሳኔውን ተገቢ አለመሆን አስመልክቶ አቤቱታ በማቅረባቸው ነው ተብሏል።

  ቅሬታ አቅራቢ ተበዳሪዎቹ ባለፈው አመት በተደረሰ ውሳኔ የሰፋፊ እርሻ ልማት ስራ በኤልኒኖ ፣ በዘር አቅርቦት ፣ የመሰረተ ለማትና ሌሎች ችግሮች ያለበት መሆኑ ታምኖበት ልማት ባንኩ የብድር መመለሻ ጊዜ እንዲያራዝምላቸውና ሌሎች ማበረታቻዎች እንዲደረግላቸው ከመግባባት ተደርሶ ፣ ውሳኔውም ተፈጻሚ ሳይሆንና ገና አመትም ሳይሞላው ወደ ሀራጅ መገባት የለበትም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል።

እንደተበዳሪዎቹ ከሆነም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ170 ተበደሪዎች የብድር ማስያዣ ንብረት ላይ ሀራጅ ለማውጣት የቸኮለው ብሄራዊ ባንክ ስላስጠነቀቀ እንጂ አስቦት አይደለምም ። 170ዎቹ እርሻዎች ያሉት ብዙዎቹ ጋምቤላ ውስጥ ሲሆን ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሌሎች ክልሎች ውስጥም ያሉ ናቸው።

የባንኩ ይህ ውሳኔም ከፍተኛ ቅሬታን አስነስቷል። የእርሻ ተበዳሪዎቹ እንደሚሉት ባንኩ ብድሩን ለማስመለስ የእኛ ንብረት ላይ ብቻ ትኩረቱን ማድረጉ ተገቢ አይደለም ፣ እኛ ላይ በብሄራችን ላይ በመመስረትም ጫና ያሳድርብናል ብለዋል። ከሀገር ውስጦቹ ይልቅ የውጪ ዜጎች ባለሀብት ነን ብለው ብዙ ገንዘብ ተበድረው ጠፍተው ሳለ ትኩረቱ ግን የሀገር ውስጥ ብቻ ነውም ብለዋል ። በሌላ በኩል የባንኩን ከፍተኛ የተበላሸ ብድር ከያዙት ሀያ ተበዳሪዎች መካከል ሶስቱ ብቻ የግብርና ዘርፍ ተበዳሪዎች ናቸው። የቀሩት ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ተበድሮ መክፈል ያልቻለው አይካ አዲስና በማምረቻ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሆነው ሳለ የግብርና ዘርፍ ላይ ብቻ በዚህ ደረጃ መተኮሩም ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ባንኩ ለሰፋፊ እርሻ ከሰጠው ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ ብድር ውስጥ 23 በመቶው የተበላሸ ነው። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተለይ ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የሰጠው ግን ከዚህ በእጅጉ የላቀ ነው ። ለአምራች ኢንዱስትሪው ከሰጠው ብድር ውስጥ 72 በመቶው የተበላሸ ሆኗል። ይህ ያክል መጠን ያለው ብድር ከተበላሸባቸው ውስጥም በርከት ያሉ የውጭ ባለሀብቶች ይገኙበታል።

 ባንኩ በእርሻ አልሚዎች ላይ እወስዳለሁ ያለው ርምጃንም እንዴት ተፈጻሚ እንደሚያደርገው ገና ግልጽ አልሆነም። ልማት ባንኩ እየደረሰበት ያለ ኪሳራም ሆነ የተበላሸ ብድር ምጣኔው እስካሁን በሀገሪቱ የባንክ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

ያልተመለሰ የብድር ምጣኔውም በጥቅሉ ካበደረው 46 ቢሊየን ብር ውስጥ 51.6 በመቶውን ይዟል። ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻም ከሶስት መቶ ሚሊየን ብር በላይ ከስሯል። ልማት ባንኩ በጥናት ላይ ተመርኩዞ እርምጃ ይወስዳል ተብሎም እየተጠበቀ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣ በሁዋላም የልማት ባንኩ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ጌታሁን ናና መልቀቂያ አስገብተው አዲስ ፕሬዚዳንት ከመሾሙ ውጭ ብዙም የአመራር ለውጥ ያልታየበት ነው። [ተጨማሪ የዋዜማ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/AYfRu0Erfsk