ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከ39 ቀናት ቆይታ በኋላ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ. ም ተጠናቋል። በስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ ምክክር ያደረገው ጉባኤው፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት ይፋዊ የመዝጊያ መርሃግብር የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከባድ የቤት ሥራ ጥሎ አልፏል።  በስምንቱም አጀንዳዎች ዙሪያ በተመካካሪዎች የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የማስረከብ ኃላፊነት ያለበት ኮሚሽኑ፤ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሁለት ወራት የሥራ ጊዜ ቀርቶታል።

ከጠቅላላ ጉባኤ እስከ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት

ነሐሴ 15 ቀን ከተከናወነውና በፌደራል ከተሞች (የአዲስ አበባ) ጉዳይ የተነሳ ውዝግብ ካስከተለው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለሰዓታት በብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት ባልደረቦች ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ምንጮች ነግረውናል።  የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በኮሚሽኑ የተቋቋመው “የሽምግልና ኮሚቴ” በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ዙሪያ አቅርቦታል ያሉትን “የሽምግልና ምክረ ሀሳብ” ለማንበብ ወደ መደ  መድረክ ሲወጡ፤ አማራ ክልልን የወከሉና ሌሎች ተመካካሪዎች ከጉባኤው አዳራሽ መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ተመካካሪዎች አዳራሹን ለቀው ሲወጡ የነበረውን ሁነት የቀረጹ የካሜራ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የመገና ኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለሰዓታት በደህንነት ባልደረቦች ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር የገለጡት ምንጫችን፤ ስብሰባውን ጥለው የወጡ ተመካካሪዎችን የሚያሳየውን ምስል እንዲያጠፉ መጠየቃቸውን ነግረውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ሁሉንም  የምክክር ሂደቶች ቀርጾ ለኮሚሽኑ ለማስረከብ በገባው ውል መሠረት የቀረጻ ሥራዎችን ሲያከናወን መቆየቱን የገለጡልን ምንጮች፤ ለሰዓታት በቁጥጥር ስር ከቆዩት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ውስጥም የኢዜአ ባልደረቦች እንደሚገኙበት ሰምተናል። ከኢዜአ በተጨማሪም የኮሚሽኑ የካሜራ ባለሙያ በደህንነቶች ቁጥጥር ሥር መቆየቱን ተረድተናል። ምንም እንኳን ባለሙያዎቹ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም፤ ጠቅላላ ጉባኤውን ለቅቀው የወጡ ተመካካሪዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ን ስለማጥፋት አለማጥፋታቸው ማረጋገጥ አልቻልንም። መሰል ሁኔታዎች የምክክር ሂደት አካል መሆናቸውን የጠቀሱ የኮሚሽኑ ባልደረቦች ምስሎቹ እንዳይጠፉ ሲጠይቁ እንደነበርም አረጋግጠናል።

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ጉዳይ ምን ሊወስን ይችላል የሚለው ጉዳይ መልስ ባላገኘበትና በርካታ ተመካካሪዎች በሥራ ቡድን ደረጃ የጸደቀው ምክረ ሀሳብ የሽምግልና ኮሚቴው  ባቀረበው ምክረ ሀሳብ ሊተካ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው በገለጡበት ዕለት የተካሄደው የማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓት፤ ተመካካሪዎች ስለ ምክረ ሀሳቦች ቀጣይ እጣ ፈንታ በቂ መረጃ ያላገኙበት መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። በአዲስ አበባ ጉዳይ ግልጽ መረጃ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ተመካካሪዎች ትክክለኛ መረጃ የሚሰጠን አካል ማግኘት አልቻልንም ማለታቸውንም ሰምተናል።

የተመካካሪዎች የሰላም ጥሪ

ነሐሴ 15 ቀን በተካሄደው የምክክሩ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በሰላም ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ በተመካከሩ ተመካካሪዎች ሀስብ አመንጪነት የተዘጋጀ የሰላም ጥሪ ተነቧል። በዚህ የሰላም ጥሪ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ወገኖች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ፤ መንግስትም ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጥሪ ቀርቧል። በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከልም፤ መንግስት ለታጣቂ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥሪ እንዲያቀርብ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

በምክረ ሀሳቡ የክትትል ሥርዓት እንዲዘረጋና፤ ወደ ሰላም የሚመጡ ታጣቂዎች ስልጠና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ተጠይቋል። የሚፈረሙ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ለህዝብ ግልጽ እንዲደረጉና ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶች ክትትል እንዲደረግላቸው የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብም በሥራ ቡድኑ ቀርቧል።

የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ መንግስት ምቹ ሁኔታ እና ጊዜ እንዲያመቻች የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ይሁንና በሰላም ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ ተዘጋጅተው የጸደቁት ምክረ ሀሳቦች፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለማቆም የሚያስችል ጥልቀት የላቸውም በሚል መተቸታቸውን ሰምተናል።

የኮሚሽኑ እጣ ፋንታ

በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ሥራ የጀመረው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ለሁለት ያህል ጊዜያት የሥራ ዘመኑ እንደተራዘመለት የሚታወስ ሲሆን፤ ከየካቲት 14 ቀንን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ወራት ያህል የተራዘመለት የሥራ  ጊዜ ጥቅምት 14 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ድረስ ምክረ ሀሳቦችን አደራጅቶችና ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉበትን ሰነድ አዘጋጅቶ  ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ ይችላል ወይ ስንል የጠየቅናቸው የኮሚሽኑ ምንጮቻችን፤ በቀሪ ጊዜያት ሥራውን ማጠናቀቅ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኮሚሽኑ ቀሪ ሥራ ትልቅ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን የገለጡት ምንጫችን፤ ምክረ ሀሳቦችን ለባለድርሻ አካላት ከማስረከብ ባለፈ ሌሎች ቀሪ ሥራዎች ከመኖራቸው ጋር በተያያዘ የኮሚሽኑ ቀሪ የሥራ ጊዜ በቂ እንደማይሆን ነግረውናል። በዚህም ኮሚሽኑ በሌሎች ኮሚሽነሮች ለተጨማሪ ጊዜያት እንዲሠራ ሊደረግ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ሰምተናል። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 መሠረት፤ መንግስት ከምክክሩ የተገኙ ምክረ ሀሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችለው  ግልጽ እና ተጨባጭ  ዕቅድ እንዲያዘጋጅ ማገዝ እንዲሁም የምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊነት የሚከታተል ሥርዓት መዘርጋት ለኮሚሽኑ የተሰጡ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ናቸው።

ኮሚሽኑ እነዚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው የጠቆሙት ምንጫችን፤ አሁን በሥራ ላይ ካሉት ኮሚሽነሮች መካከል አብዛኞቹ ለተጨማሪ ጊዜያት በኃላፊነት ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላቸው ነግረውናል።  ይህንን መሰረት በማድረግም ለኮሚሽኑ ሌሎች ኮሚሽነሮችን በመሾም ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ማድረግ አንዱ አማራጭ መሆኑን ሰምተናል።

ኮሚሽኑ የስልጣን ማሻሻያዎች እና የስም ለውጥ ተደርጎለት የምክክር ሂደቱን ቀሪ ሥራዎች እንዲያጠናቅቅ የሚደረግበት ዕድል መኖሩንም የሰማን ሲሆን፤ በተለያዩ ደረጃዎች የሚረጉ ምክክሮች እንዲቀጥሉ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን ተረድተናል። በቀጣዩ መስከረም ወር ሥራውን የሚጀምረው ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀዳሚነት ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መካከል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጣ ፈንታ አንዱ እንደሚሆንም  ይጠበቃል። [ዋዜማ]