• አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ተጀምሯል

ዋዜማ- የህዳሴውን ግድብ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ዕልባት ይሰጣል የሚል ተስፋ የተጣለበት ድርድር በካይሮ እየተካሄደ ነው።
ድርድሩ በተባበሩት አረብ ዔምሬትስ አደራዳሪነት የተጀመረው ጥረት የመጨረሻ ምዕራፍ ነው። በአፍሪቃ ህብረት የተጀመረው ጥረት ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ባለፈው ወር የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች በአራት ወራት ድርድሩን ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን አስታወቀው ነበር።

ድርድሩ ትላንት እሁድ የተጀመረ ሲሆን ዛሬ ሰኞ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ይጠበቃል።

ድርድሩ በተባበሩት አረብ ዔምሬትስ አደራዳሪነት በሚስጥር ሲካሄድ የነበረው ድርድር አካል ነው። ድርድሩ በይፋ እንዲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ባለፈው ወር መስማማታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። 

በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት ይካሄድ የነበረው ጥረት ከተቋረጠ ሁለት ዓመት ያህል ሆኖታል። ሱዳን ግብፅና ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ህብረትን የድርድር ማዕቀፍ መተዋቸውን በይፋ አላሳወቁም። 

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአሜሪካ አደራዳሪነት በዋሽንግተን በተጠራው ድርድር ተካፍሎ የእጅ ጥምዘዛ ሲበረታበት ድርድሩን ማቋረጡ ይታወሳል። ከዚያ ወዲህ በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

እስካሁን በተባበሩት አረብ ዔምሬትስ አደራዳሪነት ከ28 በላይ ድርድሮችና ውይይቶች መካሄዳቸውን ዋዜማ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል። 

በዚህ ድርድር የተደራዳሪ ቡድኑን እንዲመሩ የተደረጉት ከሁለት ዓመት በፊት በምስጢር ውይይቱ መጀመር ወቅት የቡድኑ መሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ናቸው። 

የውሀና ኤነርጂ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ያሉት ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) የራሳቸው የድርድር ቡድን አዋቅረው መንቀሳቀስ የጀመሩ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ወደ ካይሮ ሊጓዙ አልቻሉም።የኢትዮጵያን ድንበር የሚሻገሩ የውሀ ሀብቶችን በተመለከተ የመደራደር ሀላፊነት የውሀ ሚኒስትሩ ነው።

በድርድሩ የኢትዮጵያ ልኡካን ትኩረት በአባይ ተፋሰስ የወደፊት የጋራ የልማት ትብብር ሲሆን በግብጽ በኩል ግን የህዳሴው ግድብ ሙሌት እና አስገዳጅ ስምምነት ነው።

በተያያዘ ዜና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጀመሩን ዋዜማ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች። 

የህዳሴው ግድብ አራተኛው ክረምት የውሀ ሙሌት በነሀሴ እና መስከረም እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዚህ ቀደም ተናግረዋል። 

የህዳሴው ግድብ የአራተኛው ክረምት ውሀ ሙሌት እንደጀመረ እና የውሀ ሙሌቱም በሰከንድ 1200 ሜትር ኪዩብ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በኢትዮጵያ መንግስት እቅድ መሰረት በዚህኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ከ10.8 እስከ 11 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንዲይዝ ታቅዷል።

መጀመርያ የውሀው ፍሰት የታሰበውን የውሀ መጠን ለማስገኘቱ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የውሀ ፍሰቱ መሻሻል የታየበት ሲሆን አሁን ውሀ እየያዘበት ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ ከሁለት እስከ ሶስት ሳምንት የተፈለገውን ያክል ውሀ ሊይዝ እንደሚችል ጠንካራ ግምቶች እንዳሉ ዋዜማ ከባለሙያዎች መረዳት ችላለች።

የህዳሴው ግድብ ባለፉት ሶስት ክረምቶች በጥቅሉ እስከ 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ይዟል።በግንባታ ደረጃም የግድቡ መካከለኛው ክፍል ከባህር ጠለል በላይ 620 ሜትር ወይንም 120 ሜትር የኮንክሪት ግንባታ ተጀምሯል። [ዋዜማ]

To reach Wazema editors, please write to wazemaradio@gmail.com