Photo credit – PM Office

ዋዜማ- የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ዝቅተኛ የደሞዝ ወለልን ለመወሰን የሚያስችል የደሞዝ ቦርድ እንዲቋቋም መስማማታቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ለዋዜማ እንደገለፁት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሳበት የነበረው የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስማምተው ስራው እንዲጀመር መመሪያ ሰጥተዋል።

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢሠማኮ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሀገር አቀፍ ዝቅተኛ የደመወዝ ወልል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንድቋቋም ለሚመለከታቸው የካቢኔ አባላት ኃላፊነት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኮንፌዴሬሽኑ አመራሮች በሌሎች አንገብጋቢ የሰራተኛው ጥያቄዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም አቶ ካሳሁን ነግረውናል። ሌሎች ዝርዝር የውይይቱን ጉዳዮች አቶ ካሳሁን ከመግለጥ ተቆጥበዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን፣ ሠራተኞችን ለከባድ ችግር ባጋለጠው የኑሮ ውድነትና የሠራተኛ ደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ዙሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩን በአካል ለማናገር በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘ ቀደም ሲል መግለጡ ይታወሳል።

ኮንፌደሬሽኑ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓም የአለም የላብ አደሮች ቀንን አስታኮ በሰላማዊ ሰልፍ የሰራተኛውን ጥያቄ ለማቅረብ ሙከራ አድርጎ ሰላማዊ ሰልፉ ፈቃድ በመከልከሉ ሳይሳካለት ቀርቶ ነበር።

ረቡዕ የተደረገው ውይይት የሠራተኛውን ጥያቄዎች ለመመለስና መብቶች ለማስከበር ወደፊት መሠራት ያለባቸው አጠቃላይ ጉዳዮች የተመከረበት መሆኑ ካሳሁን ጠቁመዋል።

ከአጀንዳዎች ሁሉ አንገብጋቢ የነበረው ኢሠመኮ በተደጋጋሚ ሲያነሳው የነበረው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መኖር አለበት የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ የደመወዝ ቦርድ መሆኑን ካሳሁን ተናግረዋል።

በሠራተኛ አዋጅ  ላይ የሠራተኛ እና ሲቪክ ማኅበራትን ያካተተ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን ቦርድ እንደሚቋቋም ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ቦርዱን የማቋቋም ሥራ በአዋጅ ቢደነገግም እስካሁን ቦርዱ አልተቋቋመም። ቦርዱ በጥናት ላይ ተመስርቶ ዝቅተኛ የሠራተኛ ደመወዝን የመወሰን ሥልጣን አለው።

ቦርዱን በማቋቋም ሥራ ላይ ጉልህ ተሳትፎ የሚኖራቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ፍትሕ ሚኒስቴር ሲሆኑ፣ በውይይቱ ላይ የሁለቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።

የቦርዱን ማቋቋሚያ መመሪያ እንዲሰሩ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤት ሥራ እንደተሰጣቸው ካሳሁን ጠቁመዋል።

በተከሰተው የኑሮ ውድነት እየተፈተነ ለሚገኘው ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የኅብረተሰብ ክፍል፣ መንግሥት መርዳት የሚችልበትን ሁኔታ ሁሉ እንደሚመቻች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል መግባታቸውን ካሳሁን ተናግረዋል።

በዝቅተኛ ደመወዝ ተካፋዮች ላይ የተከሰተውን የኑሮ ጫና ለማቃለልና በዘላቂነት ችግሩን ለማሻሻል፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን ለመወጣት መግባባት ላይ መደረሱም ተመልክቷል።

ኢንዱስትሪ የፓርኮችን ጨምሮ በርካታ የግል ተቀጣሪዎች ለሠራተኛቻቸው የሚከፍሉት ደመወዝ፣ መሰረታዊ ሕይወት ለመግፋት እንኳን የማይበቃ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

የቀድሞው የሴቶች፣ ህጻናት ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በሦስት ኢንደስትሪ ፓርኮች ባደረገው ጥናት፣ ሴቶችና ወጣቶች በፓርኮቹ የሥራ  ዕድል ቢፈጠርላቸውም በወር እያገኙት ያለው ዝቅተኛ ክፍያ 750 ብር መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከምትጠቀምባቸው መንገዶች መካከል ርካሽ የሰው ኃይል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ  ነው። ይህ ሁኔታ የኢንቨስትመንት ስበት ማስታወቂያዎች ላይ ጭምር  ለኢንቨስተሮች እንደ ዕድል ይጠቀሳል። [ዋዜማ]