ዋዜማ- የሕዳሴ ግድብ ደርድርን በተመለከተ በአራት ወራት ጊዜ ከስምምነት ለመድረስ የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች ቃል መግባታቸውን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል። በሰባት ዓመታት ስምምነት መድረስ የተሳናቸው ግብፅ ፣ኢትዮጵያና ሱዳን ላለፈው አንድ ዓመት ምንም ይፋዊ ድርድር ሳይካሄድ እንዴት በአራት ወራት ከስምምነት እንደሚደርሱ እርግጠኛ መሆን ቻሉ?  ዋዜማ በግድቡና በድርድሩ ዙሪያ ሲካሄዱ የነበሩና እየተካሄዱ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተናል

የግድቡ ግንባታ ያለበት ደረጃ

የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በዚህ አመት መጨረሻ ወር ማለትም ነሀሴ ወይንም እስከ ቀጣዩ አመት የመጀመርያ ወር መስከረም ድረስ አራተኛ ዙር ሙሌቱን እንደሚያከናውን መንግስት መግለጹ ይታወሳል። ሆኖም መንግስት አራተኛ ዙር ሙሌቱ ይከናወናል ከሚል መረጃ ውጭ የግድቡ የደርሰበትን ቁመና እና በአራተኛው ዙር ምን ያክል ውሀ ይይዛል በሚለው ላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ዋዜማ ከምንጮቿ  ከሰበሰበችው መረጃ እንደተረዳችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአራተኛው ዙር ውሀ ሙሌቱ የሚይዘው የውሀ መጠን ከ10.8 እስከ 11 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይገመታል። ይህም ግድቡ በአጠቃላይ የሚይዘውን ውሀ ከ32 እስከ 33 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ያደርገዋል። የሕዳሴው ግድብ ላለፉት ሶስት ዙር ሙሌቶች በጥቅሉ 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን ይዞ ቆይቷል። 

በ2012 አ.ም ክረምት ወራት ላይ ለመጀመርያ ጊዜ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ የያዘ ሲሆን ; በቀጣዩ የ2013 አ.ም የክረምት ወቅት ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ የግድቡን ግንባታ እንደተፈለገው ማከናወን ባለመቻሉ የተያዘው ውሀ 1.8 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነበር። ባለፈው አመት ግን ግድቡ በግንባታ አንጻር መልካም የነበረ በመሆኑ ተጨማሪ 14 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በመያዝ አጠቃላይ የውሀ መጠኑን ወደ 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ተጠግቷል።

የሕዳሴው ግድብ የጥቅጥቅ ኮንክሪት ግንባታ የመሀልኛው ክፍል ቁመቱ 120 ሜትር ወይንም 620 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ደርሷል።ሆኖም ዳር እና ዳር ያለው የግድቡ ቁመት ከመሀልኛው አንጻር የተወሰነ ሜትር ዝቅታ ስላለው ይህን ለማስተካከል ነው አራተኛውን ዙር የውሀ ሙሌት ወቅት ገፋ ማድረግ የተፈለገው። 

በ2014 አ.ም የክረምት ወቅት ሶስተኛው ዙር ሙሌት ሲከናወን የግድቡ ዋነኛ ክፍል ቁመት 100 ሜትር ወይንም ከባህር ወለል በላይ 600 ሜትር ላይ ነበር። ላለፈው አንድ አመትም ተጨማሪ የ20 ሜትር ግንባታን በማከናወን የመሀልኛውን የግድቡን ክፍል ቁመት 120 ሜትር ወይንም ከባህር ወለል በላይ 620 ሜትር ላይ ማድረስ ተችሏል።

ድርድርና ዲፕሎማሲ

የግድቡ ዲፕሎማሲ ጉዳይም ከሰሞኑ አነጋጋሪ ነገሮች ተከስተውበታል። ሱዳን ኢትዮጵያ የግድቡን ድርድር አስመልክቶ ልትሄድበት ባሰበችው መንገድ ላይ ኩርፊያ ውስጥ መግባቷን ዋዜማ መረዳት ችላለች። የኩርፊያው ምንጭም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሳምንታት በፊት የሱዳንን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት በግብጽ ከተደረገው ጉባኤ ጎን ለጎን ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር በግድቡ ዙርያ የሚደረግ ድርድርን በአራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መስማማታቸው ተገልጿል።

ሱዳን አሁን ላይ በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን እና በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ሀይሎች ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እያለች የህዳሴው ድርድር በአራት ወራት እንዲያልቅ ሁለቱ ሀገሮች መስማማታቸው ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ለእንዲህ አይነቱ ድርድር ዝግጁ ባለመሆኗ በሁለቱ ሀገራት የመገለል ስራ እንደተሰራባት ቆጥራዋለች። 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሱዳን ሰዎች ባገኟቸው አጋጣሚዎች ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት እየገለጹ እንደሆነ ዋዜማ ከዲፕሎማሲ ምንጮቿ ሰምታለች። 

ኢትዮጵያ እና ግብጽ የሕዳሴው ግድብ ድርድርን በአራት ወራት እንዴት ሊያገባድዱ እንዳቀዱ በይፋ ያስታወቁት ዝርዝር የለም። 

ከመሪዎቹ መግለጫ አንድ ቀን በኋላ ዋዜማ ላቀረበችው ጥያቄ የኢትዮጵያ የተራዳሪዎች ቡድን አባላት በግብፅና በኢትዮጵያ መሪዎች መካከል ድርድሩን በአራት ወራት ለመቋጨት ስለተደረሰው ስምምነት መረጃ እንዳልነበራቸው ነግረውናል። ባለፈው  ሳምንት በድጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ደግሞ ምንም አይነት ዝርዝር መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀውልናል። 

በሩሲያ ሶቺ ከአራት ዓመት በፊት የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች በድንገት በደረሱት ስምምነት ድርድሩ ወደ አሜሪካ ሄዶ ከሶስት ዙር ያልተሳካ ሙከራ በኋላ መቋረጡ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ተይዞ ቆይቷል። እስካሁን የተገኘ ውጤት የለም።

የአፍሪቃ ህብረት ድርድርን ለማሳካት ሙከራ ያደረጉት የወቅቱ ሊቀመንበር የነበሩት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ትሸከዲ ተጨባጭ ውጤት ላይ ሳይደረስ የሊቀመንበርነት ጊዜያቸውን ጨርሰዋል። እስከ አሁንም ከአፍሪቃ ህብረት በኩል በድርድሩ የተሳካ ነገር የለም። 

አሁን ለብዙዎች ጥያቄ የሆነው የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች በአራት ወራት ከስምምነት ለመድረስ የሚያደፋፍር ምን አማራጭ አገኙ የሚለው ነው። 

የዔምሬትስ ስውር ዲፕሎማሲ

ያለፉት ሁለት ዓመታትን የተባበሩት አረብ ዔምሬትስ የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ ለማደራደር ሙከራ ስታደርግ እንደነበረና በሚያዚያ ወር 2013 ዓም ከኢትዮጵያ የተወከለ የተደራዳሪ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በምስጢር ወደ ዱባይ ማቅናቱን ዋዜማ መረጃ አላት። 

ይህን ተከትሎ ዔምሬትስ ባደራጀችው መድረክ 28 ዙር ድርድሮችና ምክክሮች ተደርገዋል። 

በተባበሩት አረብ ዔምሬትስ የተደረጉት ድርድሮች ይዘት በሶስቱም ሀገራት በከፍተኛ ሚስጥር እንዲያዝ የተደረገ ቢሆንም ግን ሂደቱ ብዙም ስኬት የተመዘገበበት አይደለም። እንደውም በኢትዮጵያ በኩል ድርድሩን በኮሞሮስ ሊቀመንበርነት እየተመራ ወዳለው የአፍሪካ ህብረት የመመለስ ፍላጎት አለ። 

ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ግንባታን እያከናወነች እና ውሀም እየያዘች በመሆኑ ግብጽ እና ሱዳን እንደበፊቱ የግድቡ ቁመት እና የውሀ መጠን ላይ መደራደር አዋጭ ባለመሆኑ ፣ ኢትዮጵያ ውሀ ስትሞላ አስገዳጅ ስምምነቶችን እንድትፈርም እና ግድቡ በረጅም ጊዜ ስራውን ሲያከናውን በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ድርቅ ቢያጋጥም ውሀ እንድትለቅ የሚያስችል አስገዳጅ ስምምነት ማስር ዋና ግባቸው ሆኗል።

ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ጥቅሟን የሚነካ እና አስተማማኝ ባልሆነ የውሀ ፍሰት ላይ አስገዳጅ ስምምነትን መፈረም ተገቢ አይደለም የሚል አቋም ይዛለች። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ በአራት ወራት እናሳካዋለን የሚሉት ስምምነት መሰረቱ የአፍሪቃ ህብረት ድርድር ይሁን የተባበሩት ዓረብ ዔምሬትስ አልያም አዲስ ስምምነት ይፋ አላደረጉም። [ዋዜማ]

To reach Wazema editors please write via wazemaradio@gmail.com