ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለገደብ  ከቀናት በፊት አዲስ የገንዘብ ማሻሻያ ፖሊሲ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የንግድ ባንኮች የማበደሪያ ወለድ መጠናቸውን ለመከለስ እየተሰናዱ  መሆኑን ዋዜማ ስምታለች። የማበደሪያ ወለድ መጠን መጨመር ከገበያ ተፎካካሪነት እንዳያስወጣቸው የሚሰጉት ባንኮቹ በተመሳሳይ ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸውን ላለማጣት ብልሃት እያፈላለጉ ነው። ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅራለች። 

ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር አዲስ የገንዘብ ፖሊሲን ይፋ አድርጓል። በፖሊሲው መሰረት መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ መቀነስ እና የሀገር ውስጥ ብድር ስርጭት እድገትን የሚቀንስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በምርት ላኪዎች እና ብሄራዊ ባንክ እንዲሁም በባንኮች መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ ክፍፍልን የተመለከተ ነው። 

ፖሊሲው ማእከላዊ መንግስት በአዲሱ በጀት አመት ከብሄራዊ ባንክ የሚበደረው ገንዘብ ባለፈው በጀት አመት ከተበደረው ከአንድ ሶስተኛው እንዳይበልጥ ፣ ባንኮችም ከብሄራዊ ባንክ መበደር ሲፈልጉ የሚጠየቁት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ እንዲያድግ ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ የብድር ስርጭት እድገት ከ14 በመቶ በላይ እንዳይሆን ደንግጓል። ባንኮችም የ2016 በጀት አመት የብድር እቅዳቸውን በፖሊሲው መሰረት እንዲተገብሩ ተጠይቀዋል።

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት አመት የሀገር ውስጥ ብድር ስርጭት እድገት ከ28 በመቶ በላይ ነበር። ሆኖም በአዲሱ በጀት አመት  የብድር ስርጭት እድገቱ በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ያለመ ቢሆንም፣ ንግድ ባንኮች የማበደሪያ ወለድ መጠናቸው ላይ እንዲያስቡበት እያደረጋቸው መሆኑን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። አንዳንድ ባንኮች የማበደሪያ ወለድን ለመጨመር ወይንም ሌላ ውሳኔን ለመወሰን ኮሚቴ ማቋቋማቸውንም ሰምተናል። የአንድ ባንክ ፕሬዝዳንት አመራሮቹን ሰብስቦ የብድር ወለድን ለመጨመር ብሄራዊ ባንክ የብድር ስርጭት ላይ ያወጣው ፖሊሲ ዝርዝር መመሪያ እስኪደርሳቸው እየተጠባበቁ እንደሆነ መግለጻቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

የብድር ወለድን መጨመር የሚለው ጉዳይ መነሻውም ፣ ብሄራዊ ባንክ የብድር ስርጭት እድገት ጣሪያ ላይ ገደብ መቀመጡ ባንኮች ብዛት ካለው ብድር ከሚገኝ ወለድ ያገኙት የነበረውን ትርፍ ሊቀንሰው ስለሚችል ፣ ቅናሹን በሚሰጠው የብድር መጠን ላይ ወለድን በመጨመር ለማካካስ ከማሰብ እንደሆነም ነው መረዳት የቻልነው።

ብሄራዊ ባንክ ከሰሞኑ ያወጣው የ2015 አ.ም የሶስተኛው ሩብ አመት የፋይናንስ ዘርፉን እንቅስቃሴን የሚያትተው ሪፖርት በዚህ አመት የባንኮች አማካይ የማስቀመጫ ወለድ ስምንት በመቶ የነበረ ሲሆን አማካይ የማበደሪያ ወለድ ደግሞ 14.3 በመቶ እንደነበር ይገልጻል። 

ስማቸው እና ተቋማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአንድ ባንክ ፕሬዝዳንት ለዋዜማ እንደተናገሩት የብሄራዊ ባንክ አዲሱ ፖሊሲ የብድር ስርጭቱ እድገት ላይ ከተጣለው ገደብ በተጨማሪ ንግድ ባንኮች የግምጃ ቤት ሰነድን በመግዛት የሚያገኙትንም ወለድ ሊቀንሰው ይችላል። ይህም የሚሆነው ባንኮች የሚሰጡት ብድር እድገቱ እንዲቀንስ መደረጉ ያላቸውን ተቀማጭ ሊያሳድገው ስለሚችል መንግስት በሚሸጠው የግምጃ ቤት ሰነድ ላይ የማዋል ፍላጎታቸው ከፍ ሊል ይችላል። 

በግልባጩ ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር ለሚሸጠው ግምጃ ቤት ሰነድ ከፍ ያለ ፍላጎትን የሚያገኝ ከሆነ የሚከፍለው ወለድ በፊት እንደሚከፍለው አይሆንም። ባንኮች የ90 እና 180 ቀን የግምጃ ቤት ሰነድን ከመንግስት ሲገዙ እስከ 11 በመቶ ወለድ ይታሰብላቸው ነበር። አሁን ግን ባንኮች የብድር ስርጭት እድገታቸው እንዲቀንሱ ስለተደረጉ ብዙ ገንዘባቸውን ለግምጃ ቤት ሰነድ የማዋል ፍላጎት ስለሚያድርባቸው ፤ መንግስት ደግሞ አማራጮች ስለሚኖሩት የሚከፍለው ወለድ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል። ይህም የባንኮች ትርፍ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። ለሌሎች ደንበኞች የሚሰጥ ብድር ላይ ወለድን የመጨመር ፍላጎት የመነጨውም በዚህ መልኩ የሚቀንስ ትርፍን ለማካካስ ከመፈለግ ነው ብለውናል የባንኩ ፕሬዚዳንት።

እኚሁ የባንክ ሀላፊ እንደሚሉት “እርግጥ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የገንዘብ ስርጭት ገበያው ላይ እንዳይበዛ በማድረግ የብድር እድገት እንዲቀንስ መደረጉ ባንኮች በዚህ አመት ያጋጠማቸውን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በማቃለል ከጫና ሊያላቅቃቸው ይችላል” 

ባንኮች ያጋጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቋቋም ለጊዜ ገደብ አስቀማጮች እስከ 18 በመቶ መክፈል ጀምረው ነበር። 

አሁን የወጣው የብድር ስርጭት ገደብ ተቀማጫቸውን ስለሚያሳድገው ብዙ ገንዘብ ለሚያስቀምጡላቸው ደንበኞች ከፍተኛ ወለድ መክፈል አይጠበቅባቸውም። ብሄራዊ ባንክ ባንኮች ሊበደሩት ቢፈልጉ የሚጠይቃቸው ወለድ ወደ 18 በመቶ ማደጉን ቢያሳውቅም ባንኮች ገንዘብን ፍለጋ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚያስኬዳቸው ምክንያት ላይኖር ይችላል። ምክንያቱም የብድር ስርጭት እድገታቸው ላይ ገደብ በመጣሉ የገንዘብ እጥረት ውስጥ የመግባት እድላቸው ስለሚቀንስ ነው። ስለዚህም የማበደሪያ ወለድ የመጨመሩ ሀሳብ የመጣው የብድር ስርጭት ጣሪያው ሊያመጣ የሚችለውን የትርፍ ቅናሽ በመስጋት መሆኑን ተረድተናል። 

የማበደሪያ ወለድን መጨመር ከውድድር ሊያስወጣ የሚችል እንደሆና የብድር ስርጭት ላይ ገደብ ስለተጣለ ብቻ ወለድን መጨመር ሌላ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆን ባንኮች ስጋት እንዳላቸው የባንክ ፕሬዝዳንቱ አስረድተውናል።

የብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ከኢኮኖሚ ችግር ለመውጣት ብዙ በሚጠበቅባት ሀገር የዋጋ ንረትን ከመቀነስ ባለፈ  የብድር ስርጭት ላይ ገደብ መጣሉም ሌላ ስጋት ፈጣሪ መሆኑን የሚያነሱም አሉ። [ዋዜማ]