PHOTO Credit -Addis Fortune/FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ሰሌዳቸው በአዲስ አበባ የተመዘገቡ ኮድ 1እና ኮድ 3 የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ከሐምሌ 1 2014  ዓ.ም ጀምሮ ነዳጅ መንግሥት ድጎማ በሚያደርገው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ እንደሚያገኙ ተሰምቷል ።

ዋዜማ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ባገኘችው መረጃ መሠረት የነዳጅ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጡ በታሪፍ እና በስምሪት ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ መለስተኛ፣ መካከለኛ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተሸከርካሪዎችን የሚመለከት ይሆናል፡፡

ከዚያ ባሻገር ግን ድጎማው ድጎማው የግልና የመንግስት ሰራተኞችን እንዲሁም የትምህርት ቤት  ሰርቪሶችን እንዲሁም በመተግበሪያ   አገልግሎት የሚሰጡ የመጫን አቅማቸው ከ12 ሰው በታች የሆኑ ተሽከርካሪዎችን አይመለከትም ተብሏል።

በድጎማ ስርዓቱ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ላይ የቦታና እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ (ጂ.ፒ.ኤስ) የሚገጠም ሲሆን ይህም የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ለመቆጣጠር ይረዳል።

በድጎማ ስርዓቱ የተመዘገቡ ተሸከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30/2014 ዓ.ም የግድ መቆጣጠሪያ  ጂፒኤስ  መግጠም የሚጠበቅባቸው ሲሆን  እስከ ግንቦት 30/2014 ዓ.ም የተሸከርካሪዎች መረጃ ወደ መረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የማስገባት ስራ ይሰራል ተብሏል ። 

በመሆኑም በመዲናዋ በህዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች ተደራጅተው እንዲላኩለት ቢሮው አሳስቧል ።

ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሠረት ቢሮው የተዘጋጀውን መመሪያ ተግባራዊ የሚደረገው በአዲስ አበባ ከተማና በከተማዋ በተመዘገቡ ሰሌዳዎች ብቻ ሲሆን ክልሎች በየራሳቸው በሚያወጧቸው ተመሳሳይ መመሪያዎች በየክልሉ የሚገኙ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል።

በኢትዮጵያ መንግስት ነዳጅ ከውጭ በሚገዛበት ጊዜ በድጎማ እያቀረበ መቆየቱ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከጎረቤት አገሮች አንጻር ዝቅተኛ  በመሆኑ ወደኢትዮጵያ የገባ ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደጎረቤት አገራት እንዲወጣና የአቅርቦት እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ መሸጫ ዋጋን ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ውጪ በአለም ገበያ ዋጋ ነዳጅ ገዝተው እንዲጠቀሙ ማቀዱንም በቅርቡ ይፋ አድርጓል። [ዋዜማ ራዲዮ]