ዋዜማ- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አሁን ከመንግስት ጋር ጦርነት የገጠመውን የትግራይ ተዋጊ ኀይል በማደራጀት የመሪነት ሚና እንደነበራቸው ዋዜማ ከሰነድና ከጉዳዩ ጋር ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ተረድታለች።
ታደሰ በደብረፂዮን ገብረሚካዔል ከሚመራው አንጃ ጋር የመረረ ውዝግብ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ማግስት ጀምሮ በሰውር የትግራይን ታጣቂዎች መልሶ ለማደራጀትና ለዳግም ውጊያ ሲደረግ በነበረው ዝግጅት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ በክልሉ መንግስት በፀጥታ ዘርፍ ሲሰሩ የነበሩ እማኝ ለዋዜማ አስረድተዋል።
ታደሰ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በግንቦት ወር፤ 2018 ዓ.ም ከፈረሰበት ጊዜ አንስቶ በቁም እሥር ላይ መቆየታቸው ሲገለጽ፤ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊትም ጠባቂዎቻቸው እንዲቀየሩ እንዲሁም ከመኖሪያ ቤታቸው መግባትም ሆነ መውጣት እንዳይችሉ ክልከላ ተደርጎባቸው ቆይተዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች 5 የቀድሞ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮችም ከመቀለ ከተማ ውጪ ወደ አሉ አካባቢዎች ተዛውረው የቆዩ ሲሆን፤ የመንግሥት ኃይሎች ማክሠኞ፤ ጥቅምት 3 ቀን፤ 2019 ዓ.ም የአድዋ ከተማን በተቆጣጠሩ ማግሥት ግን አመራሮቹ ነጻ ወጥተዋል ተብሏል ፡፡
በጥቅምት 2015 ዓ.ም በተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 መሠረት፤ የትግራይ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የመፍታት፣ ወታደራዊ መዋቅራቸውን የማፍረስ እና አባሎቻቸውን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ሆኖም፤ ታጣቂዎቹ መሣሪያዎችን ማስረከብ እና ትጥቅ መፍታት የሚጀምሩት ከክልሉ ውጭ ያሉ እና የፌዴራል መንግሥት ያልሆኑ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኃይሎች ከክልሉ ሙሉ በሙሉ ሲወጡ እንደሆነ ተደንግጓል።
ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግም ፤ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ የመከላከያና የደህንነት የበላይነቱን የማረጋገጥ ሥራውን የሥምምነቱን መርሆዎች ተፈጻሚ ከማድረግ ጎን ለጎን እንደሚያከናወን የሚገልጽ ሲሆን፤ ህዳር 12 ቀን፤ 2017 ዓ.ም የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ የመከላከያ ሠራዊት ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የትግራይ ኃይል አዛዦች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ታዛቢ አካላት በተገኙበት የ1ኛ ዙር የትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን የማሰናበት እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የመቀላቀል መርሃ-ግብር መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ጄኔራል ታደሰ ወረደ በአደባባይ መግለጫዎቻቸው፤ ይህንን ሂደት እንደሚደግፉና ከህወሓት አመራሮች ጋር የገቡበት ውጥረትም ከሰላም ሂደቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲናገሩ ቆይተዋል። በተለይም በጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሃት ክንፍ እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ራሱን ከድርጅቱ እና ከመንግሥታዊው መዋቅር ካገለለ በኋላ የፕሬዚደንትነቱን ቦታ የተቆናጠጡት ጀነራሉ፤ ‹‹ጦርነት በቃን›› ከሚለው ንግግራቸው ጀርባ ግን በራሳቸው ፊርማ የወጣው ሰነድ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስና በታደሰ ወረደና የደብረፂዮን ገብረሚካዔል አንጃ መካከል የተናበበ አካሄድ እንደነበረ ያመለክታል።
በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. በሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተፈርሞ የወጣው «የትግራይ ፀጥታ ኃይል አባላት መብትና ተጠቃሚነት ደንብ» ሠራዊቱን ትጥቅ እንዲፈታ የሚያደርግ ሳይሆን፤ቋሚና የተደራጀ ወታደራዊ ተቋም አድርጎ የሚያጸና ደንብ ነበረ፡፡
ደንቡ ተዋጊዎች ወደ ትግሉ የተቀላቀሉበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ የከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ይሰጣል። ከጥቅምት 24 እስከ ሰኔ 21 ቀን፤ 2013 ዓ.ም. የተቀላቀለ 200 ካ/ሜ፣ ከሰኔ 22/2013 እስከ ታህሳስ 30/2014 ዓ.ም. የተቀላቀለ 175 ካ/ሜ፣ እንዲሁም ከጥር 1/2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ደንቡ መጽደቅ ጊዜ የነበረ ተዋጊ 140 ካ/ሜ የመሬት መብት ያገኛል። ይህ አሰራር የትግራይ ኃይልን እንደ መደበኛ የክልል ወይም የሀገር ሠራዊት በመቁጠር የይዞታ ዋስትና የሚሰጥ ነው።
ለሠራዊቱ አባላትና ለቤተሰቦቻቸው በየደረጃው ነፃ የሕክምና አገልግሎት ፤ ነፃ ወይም በመንግሥት የሚሸፈን የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት፤በዓመት ሁለት ጊዜ የደንብ ልብስ፣ ጫማና ካልሲ፤ በዓመት አንድ ጊዜ ቲሸርትና አንሶላ፤ በየሁለት ዓመቱ ብርድ ልብስና ምንጣፍ አቅርቦትን ያካትታል፡፡
የደንቡ አነጋጋሪ የሆነው ክፍል፤ አባላቱ እነዚህን መብቶች የሚያገኙት «የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ ዋስትና ለመሆን በተልዕኮ በመቆየት እና በማንኛውም የማይተካ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን አምነው ሲቀጥሉ» ብቻ እንደሆነ መደንገጉ ነው። ይህ ድንጋጌ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ከማስፈታት እና ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል ከሚለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር የሚቃረንና ተዋጊዎችን በወታደራዊ መስመር ውስጥ ለዘለቄታው ለማቆየት የተሰራ ስሌት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡
በትግራይ አስተዳደር የፀጥታ ዘርፍ አባል የነበሩና አሁን ከሚካሄደው ጦርነት ራሳቸውን ያገለሉ ምንጭ እንደነገሩን ታደሰ ወረደ በሚያሳዩት ተለዋዋጭ አቋምና “የመፅናት ችግር” አስቀድሞ ከጌታቸው ረዳ ጋር በኋላም ከደብረፂዎች ጋር የከረረ ውዝግብ ውስጥ ነበሩ።
ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ለማባረርና እስከ ግድያ የደረሰ እርምጃ ለመውሰድ በነበረው ሴራ ታደሰ “እጅግ በወላዋይ” አቋማቸው ከሁለቱም ሀይሎች ጋር ላለመጣላት ሲጠነቀቁ መታዘባቸውን ምንጫችን ነግረውናል። የክልሉን አስተዳደር መምራት ከጀመሩ በኋላ ግን ከደብረፂዮን አንጃ ጋር በመስማማት “የትግራይ ህልውና የሚረጋገጠው ጠንካራ ወታደራዊ ሀይል ሲገነባ ነው” በሚል በጋራ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይህንንም የወቅቱ ጊዜያዊ አስተዳደር አንዳንድ አባላትና ፌደራል መንግስቱ እንዳያውቁ በምስጢር ተይዞ እንደነበር ምንጫችን ያስታወሳሉ።
ደብረፂዮን የክልሉን መሪነት በሀይል ከያዙ በኋላ ከታደሰ ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ መሻከሩን እንደሚያውቁ ምንጫችን ነግረውናል። ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደን ባለፉት አራት ቀናት በቀጥታና በቤተሰቦቻቸው አማካይነት አግኝተን ምላሻቸውን ለመሰማት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።[ዋዜማ]
