ዋዜማ ራዲዮ- ብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ውክልናን በህዝብ ብዛትና በአባላት ብዛት የሚያደርገውን መተዳደሪያ ደንቡን አጽድቋል ።
ፓርቲው እያካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤው የመተዳደሪያ ደንቡንና ፕሮግራሙን እንዳጸደቀ የፓርቲው የህዝብና የአለምአቀፍ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ የገለጹ ሲሆን ሁሉም በሚገባቸው ልክ የሚወከሉበት ይሆናል ብለዋል።
በጸደቀው የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ውሳኔ ሰጭ በሆኑት የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ እንዲሁም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚወክሏቸው አባላት ብዛት በክልላቸው ህዝብና በአባላቱ ብዛት የሚወሰን ይሆናል።
በተጨማሪም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ልዩ ኮታ እንደሚኖራቸው ተገልጿል ። ከዚህ ባሻገር የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማይገለልበትና አባል ሆኖ የሚታገልበት ሁኔታ ያመቻቸ ስለመሆኑ ሃላፊው አስታውቀዋል ። ከዚህ ቀደም ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ የተካው ኢህአዴግ የውሳኔ ሰጭ አካላቱ ውስጥ የሚካተቱ አባላት ከግንባሩ አራት ብሔራዊ ድርጅቶች በእኩል መጠን የሚወከሉበት እንደነበር ይታወሳል።
ፓርቲው በዛሬ ውሎው የማዕከላዊ ኮሚቴ የስራ አስፈፃሚ እንዲሁም የቁጥጥር ስነምግባር ኮሚቴዎች አባላትን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል ።
ብልጽግና ፓርቲ በትናንትናው ዕለት ከመተዳደሪያ ደንቡ በተጨማሪ የፓርቲውን ፕሮግራም ያጸደቀ ሲሆን ፕሮግራሙ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የማህበራዊ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ፕሮግራሞች የተካተቱበት ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ዐቢይ አሕመድን በከፍተኛ ድምጽ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርጎ እንደመረጠ አስታውቋል። ደመቀ መኮንን እና አደም ፋራህ ደሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ከ1 ሺህ 600 የጉባዔው ተወካዮች መካከል ዐቢይን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርገው የመረጡት 1 ሺህ 480 ተወካዮች ናቸው። ዋዜማ ራዲዮ]