‹‹ሃምባሃምባ! – ሃገራችንን ለእኛው ተዉልን!››

JOHANNESBURG, SOUTH AFRICA – JUNE 5 , 2026 Gaty Images

ዋዜማ- አብርሃም (ስሙ የተቀየረ) በደቡብ አፍሪካ መዲና ጆሃንስበርግ እምብርት በሚገኘውና በአካባቢው ቋንቋ ‹‹Spaza Shop›› እየተባለ በሚጠራው የችርቻሮ መደብሩ ውስጥ ሆኖ ደንበኞቹን ያስተናግዳል። በየእለቱ በቻለው አቅም ገቢ እያገኘ፣ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ እየከፈለ፣ ለአካባቢው ተወላጆችም የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ ልክ እንደ አብርሃም፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለዓመታት በደቡብ አፍሪካ የራሳቸውን ህይወትም ሆነ የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ መለወጥ የቻሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ 

ነገር ግን አብርሃም፤ ከሱቁ ተሻግሮ የሚታየው የጎዳና ላይ ትዕይንትና የሚሰማው የዛቻ ድምፅ ሰላሙን ነስቶታል። የህልውናው ጉዳይ አደጋ ላይ ከመውደቁ ባሻገር ለዓመታት ያፈራው ሃብት ንብረት በአንድ ጀምበር እንደ ጉም የመበተን አደጋ ተደቅኖበታል፡፡  

በስደተኞችዘንድየተፈራውሰኔ 30
ቀናት በገፉ ቁጥር በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የልብ ትርታ እየጨመረ፣ ባሉበት ሁሉ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ የፈረንጆቹ ሰኔ 30 እየተቃረበ ሲመጣ ድባቡ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። በማንኛውም ሰዓት ንብረታቸው እንደሚዘረፍ ወይም ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ያስባሉ፡፡ 

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደገለጹት፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በስደተኞች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችና ዘመቻዎች መነሻቸው ‹‹ህገ-ወጥ ስደተኞችን እናስወጣለን›› የሚል ቢሆንም፤ አሁን ላይ ሁኔታው ተቀይሯል። ህጋዊ ሰነድ ያላቸው፣ ለበርካታ ዓመታት በአገሪቱ የኖሩ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ዜግነትና መታወቂያ ያላቸውን ጭምር ያካተተ ሆኗል።

አየለ (ስሙ የተቀየረ) ነዋሪነቱን ያደረገው በሃገሪቱ ‹‹ክዋዙሉ ናታል›› የተባለው እና የ ‹‹ዙሉ›› ጎሳ አባላት በብዛት የሚኖሩበት ግዛት ውስጥ ነው፡፡ ችግሩ ከ 15 አመታት በፊት ጀምሮ ይታይ የነበረ ቢሆንም፤ ካለፉት 5 አመታት ወዲህ ግን ስደተኞችን ኢላማ የማድረግ እንቅስቃሴዎች መባባሳቸውን ያስረዳል፡፡
‹‹ለዚህ ደግሞ ዋነኛውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት የደቡብ አፍሪካ የውስጥ ጉዳዮች ተቋም እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፤ ቀኑ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር የጸጥታ አካላት በየመንገዱና ህጋዊ ስደተኞችንም ጭምር እያስቆሙ፣ ትንኮሳና ማዋከብ እያደረሱባቸው ነው›› የሚለው አየለ፤ በተለይም የመንግስት ተቋማቱ የመኖሪያ ፍቃድ በወቅቱ ባለማደስ ጭምር ጫና እንደሚያደርጉ ነግሮናል፡፡
‹‹በሆነ አጋጣሚ መንገድ ላይ ሲያገኙን ህጋዊ ብትሆኑ ባትሆኑ ግድ አይሰጠንም፤ ሃገራችን ውስጥ ልናያችሁ አንፈልግም፤ ወደ ራሳችሁ ሀገር ሂዱና ችግራችሁን ፍቱ ይሉናል›› በማለት  ሁኔታውን አብራርቷል፡፡

አየለ የሚኖርበት ይኸው ‹‹ክዋዙሉ ናታል›› ግዛት ከሃገሪቱ 9 ገዛቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የስደተኞች እጣ ፈንታ እጅጉን አስጊ ከሚባልባቸው ግዛቶች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
ስደተኞቹ ሁኔታውን ሲያስረዱ፤ ‹‹ህጋዊ ወረቀት ኖረህም፣ አልኖረህም፤ከየት አመጣኸው? ገዝተኸው ነው እንጂ እንዴት ልታገኝ ቻልክ?›› የሚሉ ጥያቄዎች በቀረቡላቸው ቁጥር ፍርሃቱ እያየለባቸው መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

‹‹ሃምባ! ሃምባ! ውጡልን!››
ማርች ኤንድ ማርች (M & M) እንዲሁም ‹‹ኦፕሬሽን ዶዱሉ›› የተባሉት ስደተኞችን የማስወጣት ንቅናቄዎች በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። የንግድ ማዕከል በሆነችው ‹‹ጋውቴንግ›› ግዛትም ሆነ ስደተኞች በስፋት በሚንቀሳቀሱባት ‹‹የክዋዙሉ ናታል›› ግዛቶች ውስጥ ኢትዮጵያውንን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡  

‹‹በየመንገዱ ‹‹ሃምባ! ሃምባ! – ሂዱ ውጡ!  እያሉን ነው ያሉት። ማንኛውም ሰው መጥቶ ቤትህን ወይም ሱቅህን ለቀህ ውጣ ሊልህ ይችላል። ምንም ዓይነት ዋስትና የለንም፤ በማንኛውም ሰዓት ልንገደል ወይም ንብረታችንን ተነጥቀን ልንባረር እንደምንችል እያሰብን ስጋት ውስጥ ነው የምንኖረው›› በማለት ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

የዘመቻው መነሻ ምክንያት

ስደተኞችን ከሃገሪቱ የማስወጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ቡድኖች፤ ስደተኞች እንዲወጡ የሚፈልጉበት ዋነኛ ምክንያት፤ በዋነኛነት ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች የሃገሪቱን ዜጎች የስራ እድል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ተቆጣጥረዋል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸው ነው፡፡

‹‹የደቡብ አፍሪካውያንን የስራ እድል ይነጥቃሉ፤ የእኛ ልጆች ቦታ አጥተዋል፤ ለልጆቻችን አደንዛዥ እጽ የሚሸጡትም እነሱ ናቸው›› በማለት በስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ ወቀሳ እንደሚያቀርቡም ሰምተናል፡፡

የጥቃቱኢላማዎችበስደተኞችአንደበትበአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ትናንሽ ንግዶችን በአብዛኛው የተቆጣጠሩት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ዋዜማ ያነጋገራቻቸው ስደተኞች ተናግረዋል፡፡ ይህም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ‹‹የስራ እድል እና ኢኮኖሚውን ተቆጣጠሩብን›› የሚል ቅሬታን መፍጠሩን የሚገልጹት እነዚሁ ስደተኞች፤ ከዚህ ቀደምም የማላዊ ዜጎችን በተመሳሳይ መልኩ ከሃገር እንዲወጡ ከላይ በተጠቀሱት ቡድኖች በኩል ሰፊ ዘመቻ መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡  

 በስደተኞቹ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና፤ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአንድ ጎሳ አባላት ወይም ተራ ቡድኖች የሚመራ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የአሁኑ ተቃውሞ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሃብቶች የሚደገፍ የተደራጀ ንቅናቄ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 በፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ለምርጫ ድምፅ ማግኛነት ታቅዶ በይፋ የሚደገፍ የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑንም አክለዋል፡፡ 

ስደተኞች ላይ ጥቃት ለመፈጸም፣ ንብረት ለመዝረፍ እና ጨርሶ ለማስወጣት እየተንቀሳቀሱ ያሉት ቡድኖች፤ የትራንስፖርት፣ ዕለታዊ አበልና የተለያዩ ወጪዎች ተመድቦላቸው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ የገለጹልን ኢትዮጲያውያኑ ስደተኞች፤ በሃገሪቱ በቆዩባቸው በርካታ አመታት ሰልፎችና የስራ ማቆም አድማዎች ቢደረጉም፤ በዚህ ደረጃ   የተደራጀና ድጋፍ የሚደረግለት ዘመቻ ግን አጋጥሞ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡

ነዋሪነቱን በ‹‹ሶዌቶ›› ያደረገው ሌላኛው ኢትዮጲያዊ በበኩሉ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሆንክ ወይም አልሆንክ ግድ አይሰጣቸውም። ስደተኛ በተባለ የውጪ ዜጋ ላይ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ህጋዊም ሆነ ህገወጥ የውጪ ዜጋ ለቅቆ እንዲወጣ ነው ፍላጎታቸው፡፡ ሰው ለማጥፋት እና ለዘረፋ የተዘጋጁ ቡድኖችም አሉ፤ ባለፉት ጊዜያት ከተፈጸሙት ጥቃቶች አንጻር ምን ሊደርስብን እንደሚችል ማሰብ በራሱ ይከብዳል›› በማለት ሁኔታውን አብራርቷል፡፡ በተለይ ዙሉዎች በሚበዙበት አካባቢና በከተማ ዳርቻ መንደሮች (Townships) ውስጥ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡  

በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ዘጠኙም ግዛቶች ያለው ሁኔታ እንደየ ቦታው ቢለያይም ፤  ስጋቱ በሁሉም አካባቢዎች መኖሩን ጠቅሷል፡፡

 ‹‹የኢትዮጲያ መንግስት በራሱ ጉዳይ ተጠምዷል››

የኢትዮጵያ መንግስት ከወራት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ጥቃት እንዲጣራ እንዲሁም ነገሮች እንዲረግቡ ለማድረግ ወደ ዲፕሎማቲክ ቡድኑን ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚልክ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል አሳውቆ ነበር፡፡ ስደተኞቹም ይህንኑ መረጃ ሲሰሙ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን በመንግስት ደረጃ የተደረገላቸው ነገር እንደሌለ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ የውስጥ ጉዳይ ተወጥሮ ያለ መንግስት ነው ብዬ ነው የማስበው›› የሚለው አብርሃም፤ የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት መንግስትታት የጥንቃቄ መልእክት ከማስተላለፍ ባለፈ ዜጎቻቸውን በብዛት እያስወጡ እና ከለላ እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን የጥንቃቄ መልእክት ከማስተላለፍ ውጪ ምንም አላደረገልንም›› ሲል ወቅሷል፡፡

የደቡብ አፍሪካ  መንግስት ግን በመጪው ሰኔ 30 ቀን ፤ 2026 ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመከላከል እንዲቻል፤ 600 ሚሊየን ራንድ መድቦ የጸጥታ ሃይሎችን ማሰማራታቸውን የሚገልጹት ስደተኞቹ፤ የኢትዮጲያ መንግስት ዝምታ እንዳሳዘናቸው ገልጸውልናል፡፡

 የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በደቡብ አፍሪካ  

በተለያዩ የውጪ ሃገራት ውስጥ መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ፈጥኖ እንደሚደርስ ቢታመንም፤ የደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ 

ስደተኞቹ በአሁኑ ወቅት ኮሚኒቲው መረጃ ከመቀበልና ከአካባቢው ታችኛዎቹ የመንግስት መዋቅሮች ጋር ከመነጋገር እና ግንዛቤ ከመስጠት የዘለለ ስራ አለመሰራቱን ጠቅሰው፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤‹‹የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አለ እንዴ እስከሚባል ድረስ ነው፤ ስብስቡ አለ ምንም ጥቅም የላቸውም፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እርስ በርስ በብሄር እና በሃይማኖት የተከፋፈለ ስለሆነ ምንም እየጠቀሙን አይደለም›› በማለት ስለ ሁኔታው ተናግረዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሃገሪቱ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉበት አዝማሚያ መኖሩን በመጥቀስ፤ በሃገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ ከቀናት በፊት ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በጆሃንስበርግ፣ በደርባንና በተለያዩ የከተማ ዳርቻ መንደሮች በሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ላይ የታጠቁ ቡድኖች በፈጸሙት ተከታታይ ጥቃት በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ንብረታቸው የተዘረፈ እና የወደመባቸውም በርካታ ናቸው፡፡  

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ፣ ጥቃቶቹን ለማጣራትና ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚልክ ማሳወቁ ይታወሳል። [ዋዜማ]