ዋዜማ- በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው 21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌሲቲቫል ላይ እንዲቀርብ የተመረጠ የሩሲያ ፊልም ለህዝብ እንዳይታይ ከዩክሬይን መንግስት ለፌስቲቫሉ አዘጋጆችና ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ተረድታለች።

21 ዓመታትን ያስቆጠረው የፊልም ፌሲቲቫል የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ፊልሞችን ለበርካታ አመታት ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን በየዓመቱ ከተለያዩ የውጪ የፊልም ፌስቲቫል አዘጋጆች ጋር ይተባበራል። በዚህ አመትም ከሩሲያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር “የሩሲያ ፊልሞች ሳምንት” በማለት የተለያዩ የሩሲያ ፊልሞችን ለተመልካች እያቀረበ ይገኛል።
ይህን የሩሲያ ፊልሞች ተሳትፎ የተመለከተው የዩክሬይን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል የሩሲያ ፊልሞች እንዳይታዩ በተለይም የሩሲያ ተዋናይ ብላድሚር ማሽኮቭ የሚታይበት ፊልም ለዕይታ እንዳይቀርብ አፅንኦት ሰጥቶ አስጠንቅቋል።

የዩክሬይን ኤምባሲ ለኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ግልባጭ አድርጎ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ብላድሚር ማሽኮቭ ሩሲያ በዩክሬይን ላይ “ከፍታዋለች” የተባለውን ጦርነት ደግፏል ፣ በአውሮፓውያኑም ከተሳትፎ የተከለከለ ባለሙያ ነው ስትል ወንጅላለች።


የፌስቲቫሉ አዘጋጆች በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ለዋዜማ ተናግረዋል። የዋዜማ ሪፖርተር የተመለከተችው የፌስቲቫሉ መርሃ ግብር እንደሚያሳየው የሩሲያም ሆነ የሀገር ውስጥ ፊልሞች በተያዘላቸው ዕቅድ እየቀረቡ መሆኑን ተረድታለች።


21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሀሙስ ህዳር 10፣ የሩስያ ልዑካንና አምባሳደሮች በተገኙበት የፊልም እይታና ውይይት እንደሚያከናውን ተገንዝበናል። በተጨማሪም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ፣ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው አዲስ ቴአትር እና ሲኒማ ኮምፕሌክስ፣ በአእምሮ ውስንነት ዙሪያ የሚቀርበውን ፊልም ተከትሎ የቀድሞው አፈጉባዔ አባዱላ ገመዳ በሚገኙበት መሰናዶ ተዘጋጅቷል፡፡
21 ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል “50 ፊልሞች በ50ብር” በሚል ርዕስ ከኅዳር 6 እስከ 13 ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የህፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ እየተካሄደ ይገኛል። [ዋዜማ]