ዋዜማ- በትግራይ ክልል በፈንጂ ማስወገድ እና የማኅበረሰብ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ግብረሰናይ ደርጅቶች ሥራ በማቆማቸው በፈንጂ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን ዋዜማ ሠምታለች፡፡
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አበርገለ ወረዳ የጭላ ከተማ ጥቅምት 17 ቀን፤ 2019 ዓ.ም በፈንጂ ምክንያት በደረሰ አደጋ አራት ህፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሰዎች መሞታቸውን የግብረሰናይ ድርጅት ሠራተኞች እና ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
በአደጋው 6 ሰዎች ወዲያውኑ ህወይታቸውን ሲያጡ፤ አራቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ዓብይ ዓዲ ጠቅላላ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡
ፍንዳታው ከፍተኛ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሠዎች ማንነት ለመለየት አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን እና በፍንዳታው የቆሰሉት ሠዎች የሕክምና እርዳታ ቢደረግላቸውም በሕይወት መትረፍ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ፍንዳታው የተከሰተው የአበርገለ ወረዳ መቀመጫ ከሆነችው የጭላ ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወታደራዊ ሠፈር ከወደመ የጦር መሳሪያ የተረፈ ብረታ ብረት ለሽያጭ ወደ ከተማ በተወሰደበት ወቅት መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ከሟቾቹ መካከል የሆኑ ግለሰቦች ብረቶቹን ለመሸጥ በአህያ ጭነው ወደ ከተማ መውሰዳቸውን እና በድንገት ወድቆ በመፈንዳቱ፤ ሞት ማስከተሉን አስረድተዋል፡፡
ከሞት ጋር ትንቅንቅ
በ2013 ዓ.ም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተደጋጋሚ በሚከሰት ፍንዳታ የሰዎች ህይወት መጥፋቱን በወረዳው የግብረሰናይ ድርጅቶች አስተባባሪ በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሰሩ የቆዩ ምንጮች ነግረውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፌደራል መንግሥት እና በህወሃት ኃይሎች ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎም፤ ግብረሰናይ ድርጅቶች ሠዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቦታ ላይ የተገኘን ፈንጂ የማስወገድ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማቆማቸው ችግሩ አሳሰቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ወረዳው ያለፈውን የ2018 ዓ.ም ክረምት ጨምሮ በተደጋጋሚ በድርቅ በመጠቃቱ አንዳንድ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ከጦርነት የተራረፉ ብረቶችን ሸጠው ራሳቸውን ለመደጎም እንደሚሞክሩ ጠቁመው፤ በኪሎ እሰከ 30 ብር ድረስ ብረት ለመሸጥ በማሰብ ሙሉ በሙሉ ያልፈነዱ እና በከፊል የፈነዱ ተተኳሾችን ጭምር በተለምዷዊ መንገድ በእሳት በማቃጠል ለማፈንዳት በሚደረጉ ሙከራዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች በርካቶች መሆናቸው አስረድተዋል፡፡
በድርቅ የተጠቃው ማኅበረሰብ በማወቅም ባለማወቅም ያልፈነዱ ተተኳሾችን ጭምር እንደሚሰበስብ ጠቅሰው፤ ብረቶቹን ለማግኘት የመሽቀዳደም ሁኔታ እንደሚስተዋልም ነግረውናል፡፡
የማኅበረሰቡ ራሱን ለአደጋ አጋልጦ የመስጠት ድፍረት የተፈጠረው ከግንዛቤ እጥረት ባሻገር፤ ድርቁ ያስከተለው ችግር ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ግለሰቦች ያልፈነዱ ተተኳሾችን በመኖሪያ ቤታቸው ማከማቸታቸው ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ለብረታ ብረት ሽያጭ የተሰበሰቡ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ያልፈነዱ ተተኳሾችን፤ የግብረሰናይ ድርጅቶች ተከታትለው ከሠዎች በተከለለ ቦታ ያስወግዱ ነበር ብለዋል፡፡
ሥራ ማቋረጥ
መስከረም 13 ቀን፤ 2019 ዓ.ም በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት ግብረሰናይ ድርጅቶች ሥራ ለማቆም ተገደዋል፡፡ በጦርነት ወቅት ፈንጂ የማስወገድ ሥራ የመሥራት ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የፈንጂ አደጋዎችን በመከላከል ላይ የሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲሰማሩ ፈቃድ የሚሰጠው የመከላከያ ሠራዊት ሲሆን፤ ከአደጋው አሳሳቢነት አንጻር የአደጋ ጊዜ ሥራ ለመስራት ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
ድርጅቶቹ በአደጋ ጊዜ ሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለመከላከያ ሠራዊት ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው ምንጭ፤ ምንም እንኳን መረጃውን እስከሠጡን ስዓት ድረስ፣ ጥያቄ ያቀረቡ ድርጅቶች ፈቃድ ባይሰጣቸውም ሙሉ ዝግጅት አድርገው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት ተጨማሪ የፈንጂ ቅሪት በየአካባቢው መኖሩ፤ በንጹኃን ዜጎች ላይ በተለይም በሕፃናትና ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከባድ አደጋ መደቀኑን ግብረሰናይ ድርጅቶቹ ገምግመዋል።
ከፍንዳታ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለመከላከል በተለይም ተረፈ ፈንጂዎችን በመሰብሰብ የገቢ ማስገኛ ሥራን አማራጭ ያደረጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመታደግ አፋጣኝ የአደጋ ጊዜ ሥራ እንደሚያስፈልግ ድርጅቶቹ ይገልጻሉ፡፡
በግጭቱ መቀጠል ለግብረሰናይ ድርጅቶቹ የአደጋ ጊዜ ሥራ ፈቃድ የማይሰጥ ከሆነ፣ መንግሥት የማስጠንቀቂያ መልዕክት እና የግንዛቤ መስጫ መረጃዎችን በራዲዮ እና በቴሌቪዝን ጭምር ማስነገር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የአደጋ ጊዜ መረጃዎችን በመሰብሰብ የተቀናጀ የፈንጂ ማስወገድ ምላሾችን መስጠት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በሰብዓዊ እርዳታ መደገፍ ሰዎች አደገኛ የተባሉ የፈንጂ ቅሪቶችን እንደ ተራ ብረት ለመሰብሰብ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀነስ ይረዳል ብለው እንደሚያምኑም ነግረውናል። ባለሥልጣናት በድርቅ ጫና ውስጥ ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ፣ በፈንጂ ቅሪቶች የሚጠፋውን የሰው ሕወይወት መታደግ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ሲሉም አክለዋል፡፡ [ዋዜማ]
