ዋዜማ- ላለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮ ቴሌኮምን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት የመሩት ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት እንዲመሩ መሾማቸውን ተከትሎ  የተደረጉ መዋቅራዊ ለውጦች፤ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ውድድር እና የቁጥጥር ምህዳር ላይ በባለድርሻ አካላት ዘንድ የመነጋገሪያ ርእስ ከሆነ ሠንበትበት ብሏል፡፡

ፍሬህይወት በተቋሙ ውስጥ በነበሯቸው የ 8 ዓመታት ጉዞ ፤የኢትዮ ቴሌኮምን ገቢ በማሳደግ፣ የኔትወርክ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት እና አዳዲስ የዲጂታል አሠራሮችን በመዘርጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በሌላ በኩል ግን፣ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ የተሠጣቸው አዲስ የሚኒስትርነት ሹመት እና የተቋማት ተጠሪነት ለውጦች ከሕግና ከገበያ ውድድር ፍትሃዊነት አንጻር ጥያቄዎች እንዲነሱ በር ከፍተዋል፡፡

ሹመት እና የሕግ ክርክር

የቀድሞዋ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ከመስከረም 25 ቀን ፤ 2019 ዓ.ም ጀምሮ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሆኑት ፍሬሕይወት፤ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተዛወሩ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)  አማካኝነት የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል። የቀድሞው የድርጅቱ ተቀዳሚ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታሪኩ ደምሴም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተሹመዋል።

ይሁን እንጂ፤ ይህ ሹመት በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1314/2016 አንቀጽ 15 ድንጋጌ ጋር እንደሚጣረስ የሕግ ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

አዋጁ፤ ‹‹የቦርድ አባላት ለሹመት ከመታጨታቸው በፊት ላሉት ሦስት ዓመታት በቦርድ አባልነት ለሚሾሙበት በመንግሥት ባለቤትነት ከተያዘ የልማት ድርጅት ሠራተኞች ያልነበሩ፣ በመንግሥት ባለቤትነት ከተያዘው የልማት ድርጅት ጥቅሞች ጋር የሚጋጭ የገንዘብ፣ ቤተሰባዊ፣ የንብረት፣ የሙያ እና ትርጉም ያለው ግንኙነት ጨምሮ ማናቸውም የግል ጥቅም ያልነበራቸው መሆን ይኖርባቸዋል›› ይላል።

የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በቀጥታ የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ የራሳቸውን የቀድሞ ውሳኔ እና አሠራር መልሰው እንዲገመግሙ ስለሚያደርጋቸው፤ የቦርዱን ገለልተኛ የቁጥጥር ሚና ያዳክማል በሚል ሕጉ ይህንን አሠራር ይከለክላል።

በአዋጁ አንቀጽ 13 እና 14 የቦርድ እና የማኔጅመንት ኃላፊነት ልዩነት በሚለው ሥር፤ የልማት ድርጅቶች ቦርድ የስትራቴጂ እና የቁጥጥር ሥራዎችን ብቻ እንዲሠራ፣ የዕለት ተዕለት ሥራ አመራሩ ደግሞ በዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዲመራ ሕጉ ድንበር የሚያበጅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመንግሥትን የባለቤትነት ድርሻ ቢያስተዳድርም፤ የቦርድ ሹመቶች ከአዋጁ ሕጋዊ መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይኸው አዋጁን የሚጥስ አካሄድ፤ የአንድ ግለሠብ ወይም አመራር ተጽእኖን በተለያዩ ግዙፍ ተቋማት ላይ የማሳረፍ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል የሚገልጹት ባለሞያዎቹ፤በተለይም በቴሌኮም ገበያው ላይ ክርክር ሲደረግባቸው የቆዩ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ክርክሮች እልባት ባላገኙበት ሁኔታ መሠል የአሠራር መጣረስ መኖሩ፤ የቴሌኮም ገበያውን ወደ ኋላ ሊመልሠው እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ከተቀላቀሉት የኔትወርክ ኦፕሬተሮች መካከል ሳፋሪኮም አንዱ ሲሆን ፤ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የህግ ባለሞያ፤ ‹‹ሹመቱ እና አጠቃላይ አካሄዱ አዋጁን የሚጣረስ ከመሆኑም በላይ፤ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ፍሬህይወት ታምሩ የሥልጣን እርከን ከአንድ ኩባንያ በላይ ሆኖ፤ ሁሉንም የመጠቅለል አቅም ሲኖረው በአንድ ሠው ተጽእኖ ሥር አይወድቅም? የቴሌኮም ገበያውን ከተቀላቀለው ሳፋሪኮም እና ለመቀላቀል አቅደው፤ ሀሳባቸውን ከቀየሩ ኩባንያዎች ጋር የነበረው አይነት ውዝግብ አይፈጠርም ብሎ ለማሰብስ አይቸግርም? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል ይላሉ፡፡

ከሳፋሪኮም ጋር የተፈጠረው ውዝግብ

ሳፋሪኮም ከአራት አመታት በፊት የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ሲቀላቀል የራሱን የፋይበር ኔትወርክ ሙሉ በሙሉ ዘርግቶ እስከሚያጠናቅቅ ድረስ የኢትዮ ቴሌኮምን መሰረተ ልማቶች ተከራይቶ ለመጠቀም ውል የተፈራረመ ቢሆንም፤ ኢትዮ ቴሌኮም የመሰረተ ልማት ኪራይ ክፍያውን በዶላር እንዲፈጸም እና የኪራይ ዋጋው ከፍተኛ እንዲሆን ጠይቆ ነበር። ሳፋሪኮም በበኩሉ ክፍያው በኢትዮጵያ ብር እንዲሆንና የዋጋ ቅናሽ እንዲደረግለት ተከራክሯል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣንም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት የክፍያ ተመኑ እንዲቀንስና የታሪፍ ድርድሩ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል እንዲቋጭ አዝዟል።

በታህሳስ 2015 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ከፍተኛ የካሳ ክስና ውዝግብ ተነሥቶ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም በወቅቱ በሰጠው መግለጫ፣ ሳፋሪኮም በአፋር ሰመራ ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች የራሱን የፋይበር መስመር ሲዘረጋ የኢትዮ ቴሌኮምን የመሬት ሥር የኦፕቲክስ ፋይበር መስመሮች በቁፋሮ ወቅት አበላሽቷል ሲል ከሷል።

በዚህ ምክንያት በበርካታ ከተሞች የኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ገልጾ፣ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቆ ነበር።

በሌላ በኩል ሳፋሪኮም የገንዘብ ዝውውር ዲጂታል መተግበሪያውን ኤም-ፔሳ (M-PESA) በኢትዮጵያ ከተገበረ በኋላ ከኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር  ጋር ከፍተኛ የገበያ ፉክክር ውስጥ ገብቷል።

ሳፋሪኮም እና ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ በሚያዚያ ወር፤ 2018 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ፤ ኢትዮ ቴሌኮም የኤም-ፔሳ መተግበሪያን በራሱ የኢንተርኔት መስመር እና ዳታ በሚጠቀሙ ደንበኞች ዘንድ እንዳይሠራ አግዶብኛል የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።

 የዓለም ባንክ በበኩሉ፤ የቴሌኮም ገበያ ግምገማ ሪፖርት ላይ ይህንን የመተግበሪያዎች መታገድ እና መሰናክል መፈጠር አረጋግጦ፤ ገበያው ‹‹በስም ነፃ ይባላል እንጂ በተግባር ፍትሃዊ ውድድር የለበትም›› ሲል ደምድሟል።

 በቅርቡ የተደረጉ የመንግሥት መዋቅር ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ተጠሪነት ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ማድረጉ እና የቀድሞዋ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከመሾማቸው ባሻገር የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መሆናቸው ፤ መሠል ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የጥቅም ግጭቶች ሲፈጠሩ በእሳቸው አመራር ተጽእኖ ሥር ይወድቃሉ የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

 ተጠሪነት

በቅርብ ጊዜ ከተደረገው የመንግሥት መዋቅራዊ ማሻሻያ በኋላ፤ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን የመቆጣጠር እና ፍቃድ የመሥጠት ኃላፊነት ያለው የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን፤ በቀጥታ ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ እንዲሆን ተደርጓል።

ቀደም ሲል በዕቅድም ሆነ በአሠራር ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ የተቋቋመው የቁጥጥር አካል አሁን በቀጥታ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥር መግባቱ፤ እንዲሁም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሮባ የቀድሞ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ ባልደረባ መሆናቸው በገበያው ውስጥ ባለው ፉክክር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ በግል ኢንቨስትመንት ገብቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ብቸኛው ተፎካካሪ የኬንያው ሳፋሪኮም ነው። አዲሱ አደረጃጀት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም እና የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣኑን በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጥላ ሥር የሚያደርግ በመሆኑ፤ በገበያው ላይ ገለልተኛና ፍትሃዊ የውድድር ምህዳር እንዳይዛባ የዘርፉ ተዋንያን ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ይህ ዓይነቱ የመዋቅር እና የሕግ አተገባበር ሁኔታ በቀጣይ የቴሌኮም ፈቃድ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኦፕሬተሮች ውሳኔ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም ይጠቁማሉ። [ዋዜማ]