የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበር ቤት ግንባታ መነሻ ዋጋ በካሬ ወደ 50 ሺህ ብር ከፍ መደረጉን ዋዜማ ሰምታለች ፤ ክፍያውን መቀጠል ያልቻሉ መምህራን ‹‹ገንዘቡ አይመለስላችሁም›› ተብለዋል፡፡

ዋዜማ- ከዚህ ቀደም በካሬ 35 ሺህ ብር የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበር ቤት ግንባታ መነሻ ዋጋ ፤ ወደ 50 ሺህ ብር ከፍ እንዲል መደረጉን  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በማኅበር ተደራጅተው ቤት የመገንባት ፍላጎት ያላቸውን የመንግሥት ሠራተኞች ለሚያደራጀው የከተማ አስተዳደሩ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የጻፈው ዋዜማ የተመለከተችው ደብዳቤ ያመላክታል።

የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ መኮንን ጥበቡ ቸኮል (ዶ/ር) ፊርማ ያረፈበት ይኸው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ በታህሳስ ወር፤ 2017 ዓ.ም በካሬ የተሰላው መነሻ የግንባታ ዋጋ 35 ሺህ ብር ቢሆንም፤ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም በተከለሰው የዋጋ ተመን መሠረት ወደ 50 ሺህ ብር ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተለይም መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች በማኅበር ተደራጅተው በካሬ በ35 ሺህ ብር ሂሳብ፤ የ25 በመቶ ቅድመ ክፍያ ፈጽመው ቤት እንዲገነቡ መሬት በነፃ አቅርቧል። በተጨማሪም፤ 75 በመቶ የሚሆነው ክፍያ በባንክ ብድር ለመሸፈን የሚያስችል አሠራር የዘረጋ ሲሆን፤ 6 ሺህ 194 መምህራን እያንዳንዳቸው ከ100 እስከ 110 አባላት ባሏቸው 57 ማኅበራት ተደራጅተው ከከተማ አስተዳደሩ መሬት በነፃ ተረክበዋል።

ሆኖም፤ በቀረበላቸው የግንባታ መነሻ ዋጋ መሠረት የ25 በመቶ ቅድመ ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ እንዳጋጠማቸው ለቤት ግንባታ የተደራጁ የመምህራን ማህበራት ኮሚቴዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ የ25 በመቶ ቅድመ ክፍያውን ሲፈጽሙ ተሠልቶ የቀረበላቸው የግንባታ ዋጋ በቅርቡ ከተሻሻለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ጠቅሠው፤ ጭማሪው ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አስረድተዋል።

መምህራኑ በቀረበላቸው ዋጋ መሠረት ቅድመ ከፍያውን ሲፈጽሙ፤ ያለምንም የዋጋ ጭማሪ ቤቱ ተገንብቶ እንደሚሰጣቸው በማመን እንደገቡበት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ፤ ወደ ግንባታ ሂደት ሲገቡ የገጠማቸውን የዋጋ ጭማሪ ያልጠበቁትና ከወር ገቢያቸው አንጻር አዳጋች መሆኑን ይናገራሉ።

የማኅበራቱ ቅሬታና ስጋት

የመምህራኑ ማኅበራት መጀመሪያ በቀረበላቸው አጠቃላይ የግንባታ ዋጋ ስሌት መሠረት 25 በመቶውን ቅድመ ክፍያ ሲከፍሉ፤ ከወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ ለመክፈል ስለከበዳቸው በብድር እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ክፍያውን መፈጸማቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በቅርቡ ተሻሽሎ የቀረበላቸው ‹‹የተጋነነ›› ሲሉ የጠሩት ዋጋ ያልጠበቁት እንደሆነባቸው ነግረውናል፡፡

አቅማቸውን ማእከል ባደረገ መልኩ ከስቱድዮ እስከ ባለ 3 መኝታ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ቅድመ-ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ፤ አዲሱን የዋጋ ተመን ሲያውቁ ገንዘባቸው እንዲመልስላቸው የጠየቁ መምህራን መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መነሻ ዋጋው 50 ሺህ ብር ሲሆን፤ እስከ 82 ሺህ ብር ተመን የወጣላቸው ግንባታዎች እንዳሉ ሲገነዘቡ፤ ‹‹ተጨማሪ ክፍያ የመፈጸም አቅም የለንም፤ ገንዘባችን ይመለስልን›› በማለት ከማህበሮቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ጥያቄ ያቀረቡ መምህራን ፤ ገንዘባቸውን መመለስ እንደማይቻል እንደተነገራቸው ገልጸውልናል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተጠንቶ የቀረበው ወቅታዊ የማኅበር ቤት ግንባታ ዋጋ በካሬ እስከ 82 ሺህ ብር የሚደርስ ሲሆን፤ በማኅበር የሚገነቡ ቤቶችን ንድፍ (ዲዛይን) ያወጣው ዩኒቨርሲቲው ባቀረበው የዋጋ ስሌት መሰረት እያንዳንዱ ማኅበር ግንባታ በሚያከናውንበት ቦታና የግንባታ ግብዓት የተወሰነ የዋጋ ልዩነት ቢኖረውም፤ በአመዛኙ ተቀራራቢ እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡

አብዛኞቹ በማኅበር የተደራጁ መምህራን የቀረበውን የዋጋ ጭማሪ መሰረት አድርገው ክፍያ ለመፈጸም አቅማቸው እንደማይፈቅድ በመግለጽ፤ በኮሚቴዎቻቸው በኩል ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ቢሮው በበኩሉ የዋጋ ጭማሪውን ቀድሞ በተሰላውና አዲስ ተጠንቶ በቀረበው ዋጋ መካከል ለማቀራረብ እንደሚጥሩ በቃል ደረጃ ምላሽ እንደሰጣቸው የማኅበራቱ ኮሚቴዎች ነግረውናል።

አስቀድሞ የዋጋ ተመን ከወጣ በኋላ ምክንያታዊ ያልሆነ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንደማይቀበሉ በየማኅበራቸው አቋም መያዛቸውን የገለጹት ኮሚቴዎቹ፤ በቅርቡ ተጠንቶ የቀረበላቸው ጭማሪ ያለው የግንባታ ዋጋ፤ የሪል ስቴት አልሚዎች ለመሬት እና ለግንባታ አጠቃላይ ወጪ ከሚጠይቁት ዋጋ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን በመጥቀስ፤ አግባብ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ጭማሪው የመምህራንን አቅም ያላገናዘበ መሆኑን ተከትሎ፤ ግንባታው እንዳይስተጓጎል ‹‹ስጋት አለን›› ብለዋል፡፡

በ25 በመቶ ቅድመ ክፍያ ግንባታ ያስጀመሩ አንዳንድ ማኅበራት፤ በዚሁ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ግንባታውን ማቋረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአብዛኞቹ ማኅበራት ግንባታ ገና መሠረት በማውጣት ደረጃ ላይ ሲሆን፤ የዋጋ ጭማሪው ቁርጡ ሳይታወቅ ‹‹ግንባታ አንጀምርም›› ያሉ እንዳሉም ሰምተናል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ

የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ ያቀረበው አማራጭ ላይ መነሻ ዋጋ እንጂ አጠቃላይ የግንባታ ዋጋ መወሠን እንደማይችል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ አንድ ሀላፊ ለዋዜማ ተናግረዋል። ሀላፊው እንደገለጹት፤ ቅድመ- ክፍያውን የፈጸሙ መምህራን ክፍያውን ከፈጸሙ በኋላ፤ ራሳቸው እንደሚገነቡት ሳይሆን ‹‹መንግሥት ገንብቶ ያስረክበናል›› የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ነበር፡፡

መሬት በነፃ ከማቅረብ፣ የግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር እገዛዎችን ከማድረግ፣ እንዲሁም የግንባታውን አጠቃላይ ዋጋ 75 በመቶ የባንክ ብድር ከማመቻቸት ባለፈ፤ አስተዳደሩ ዋጋ የመወሠን ሚና እንደሌለው አብራርተዋል፡፡ የግንባታ ዋጋውን የሚወስነው ማኅበራቱ የመረጡት የቤት ዲዛይን፣ የግንባታ ግብዓቶች ደረጃ፣ ቤቶቹ የሚገነቡበት ቦታ እና ሁኔታ እንዲሁም አጠቃላይ የወቅቱ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በማኅበራት ቤት ዲዛይን እና የዋጋ ጥናት አቅራቢው የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አሻሽሎ ያቀረበውን የግንባታ ዋጋ ማረጋገጫ እንዳልሰጠው የገለጹት ሀላፊው፤ ማኅበራቱ ሲደራጁ የቀረበው የግንባታ ዋጋ ዝቅተኛ መነሻ እንጂ፤ አጠቃላይ የግንባታ ወጪው የሚወሰነው ቤቱ በሚገነባበት ደረጃ መሆኑንም ነግረውናል።

ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው ያቀረበውን የዋጋ ጥናት እና ከተማ አስተዳደሩ በየሩብ ዓመቱ ከሚወጣ የግንባታ ግብዓት ዋጋ ተመን ጋር ለማጣጣም እንደሚሞከር አስረድተዋል፡፡ የግንባታ ተቋራጮች፤ በዝቅተኛ ዋጋ ውል ከተዋዋሉ በኋላ፤ ግንባታው እንዳይስተጓጎል እና ከመምህራን አቅም በላይ የተጋነነ ዋጋም እንዳይኖር ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም፤ አስተዳደሩ የግንባታውን ዋጋ የመወሠን ሚና እንደሌለው አስምረዋል፡፡

መምህራን እና የጤና ባለሞያዎች ለአመታት ሲያነሷቸው ለቆዩዋቸው የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በማሰብ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስጀመረው የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበር ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጥር 27 ቀን፤ 2018 ዓ.ም፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በለሚ ኩራ ክፍለ-ከተማ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ]