ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ38ኛ ቀን ውሎው በሥራ ቡድን ደረጃ የጸደቁ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን ለምክክሩ ጠቅላላ ጉባኤ አቅርቧል። ኮሚሽኑ እከተለዋለሁ ሲል ይፋ ያደረገው የምክክር ውሳኔ አሰጣጥ መመሪያ፤  ለጠቅላላ ጉባኤው የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች በ”ጭብጨባ” እንደሚጸድቁ የሚጠቁም ሲሆን፤ “ጠንካራ ተቃውሞ” የሚገጥማቸው ጉዳዮች ደግሞ እንደማይጸድቁ አስቀምጧል። መሰል ውሳኔ የሚተላለፍባቸው የምክክር ሂደቶች ምልአተ ጉባኤ ተሟልቶ ሊከናወኑ እንደሚገባም በመመሪያው የተደነገገ ሲሆን፤ ምልአተ ጉባኤ ተሟልቷል የሚባለው ደግሞ ከአጠቃላይ ተመካካሪዎች መካከል 75 በመቶው ሲገኙ ነው።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስካሁን ትክክለኛውን የተመካካሪዎች ቁጥር ያላሳወቀ ሲሆን፤ ነሐሴ 15 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም ምልአተ ጉባኤ መሟላቱ ሳይረጋገጥ የተካሄደ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። በዚሁ ጉባኤ በስምንቱም አጀንዳዎች ዙሪያ የተመካከሩ የሥራ ቡድኖች ያጠናቀሯቸውና በጋራ ማረጋገጫ ቡድን እንዲደራጁ የተደረጉት ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል። ከአንጀዳ ምክረ ሀሳቦች በተጨማሪም፤ ኮሚሽኑ በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ጉዳይ “እንዲያሸማግል” በሚል ያቋቋመው ኮሚቴ ያዘጋጀው ምክረ ሀሳብም ለጉባኤው ቀርቧል።

ባለስልጣናትን ያቀፈው የሽምግልና ኮሚቴ

የክልሎች ፕሬዝዳንቶች፣ የሁለቱ ከተሞች ከንቲባዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች ተወካዮች፣ የወጣቶች ተወካዮችና ሌሎች አካላትን ማቀፉ የተነገረለት የሽምግልናኮሚቴ፤ በከተሞች አጀንዳ ዙሪያ ከጥቃቅን ቡድን ጀምሮ የተካሄደውን የምክክር ሂደት ተመልክቶ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ በኮሚሽኑ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ይህ ኮሚቴ ነሐሴ 14 እና 15 ተመካክሮ ያዘጋጀውን ምክረ ሀሳብ ለኮሚሽኑ ማቅረቡን የገለጡልን ምንጮች፤ ምክረ ሀሳቡ ለጠቅላላ ጉባኤው እንደሚቀርብ መነገሩ ግን ተቃውሞ ያጋጠመው ጉዳይ ሆኗል።

በጠቅላላ ጉባኤው ምን ተፈጠረ?

የሥራ ቡድኖች በተወካዮቻቸው በኩል ተመካክረው ያጸደቋቸውን ምክረ ሀሳቦች ለጠቅላላ ጉባኤው ከቀን 10 ሰዓት ጀምሮ እንዲያነቡ መደረጉን ተከትሎ፤ ለሥራ ቡድኖች በተሰጠው የቁጥር ቅደም ተከተል መሠረት ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል። በሰባተኛነት ከቀረበው የፌደራል ከተሞች አጀንዳ ምክረ ሀሳብ በኋላ፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) የሽምግልና ኮሚቴው ለኮሚሽኑ ያስረከበውን ምክረ ሀሳብ ለተመካካሪዎች ለማንበብ ወደ መድረክ መውጣታቸውን የነገሩን ምንጮች፤ የሽምግልና ሂደቱ ተቀባይነት የለውም የሚል ቅሬታ አቅርበው የነበሩ የአማራ ክልል ተወካዮች ከጉባኤው አዳራሽ መውጣታቸውን ነግረውናል። ኮሚሽነር ዮናስ የተመካካሪዎችን ከአዳራሽ መውጣት ቢመለከቱም ምክረ ሀሳቡን ማንበባቸውን የሰማን ሲሆን፤ የቀረበውን ምክረ ሀሳብ አንብበው ሲጨርሱም ከአዳራሽ የወጡ ተመካካሪዎችን አስመልክቶ ንግግር አለማድረጋቸውን ተረድተናል።

ኮሚቴው ያቀረበው ምክረ ሀሳብ

የተለያዩ አካላትን ያካተተው የሽምግልና ኮሚቴ በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ዙሪያ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ በዋናነት፤ በአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ጉዳይ መሆኑን ሰምተናል። በአጀንዳው የቃላት አጠቃቀም ዙሪያ ተጠሪ (አካል የሚለው ቀርቶ) እና ርዕሰ ከተማ (መቀመጫ የሚለው ቀርቶ) በጥቅም ላይ እንዲውሉም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ኮሚቴው በሕገ መንግስቱ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ናት የሚል ዕውቅና እንዲሰጥ ባቀረበው ምክረ ሀሳብ ደግሞ፤ እውቅና መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ያላቸውን ሁለት አማራጮች አቅርቧል። የመጀመሪያው አማራጭ “ሁሉም ክልሎች ርዕሰ ከተማቸውን መምረጥ እንደሚችሉ የሚጠቁም” ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ እንዲካተት የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ “አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ናት” የሚል ቀጥተኛ ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ እንዲካተት የሚጠይቅ መሆኑን ሰምተናል።

ኮሚቴው ያቀረበው ምክረ ሀሳብ፤ ኮሚሽኑ ከሁለቱ አማራጮች መካከል አንዱን ለይቶ እንዲያቀርብ የሚጠይቅ መሆኑን የገለጡት ኮሚሽነር ዮናስ፤ ኮሚሽናቸው ከጥቃቅን ቡድን እስከ ሥራ ቡድን ጉባኤ ድረስ የተካሄደውን የምክክር ሂደት በቃለ ጉባኤዎች፣ የድምጽ እና የምስል ክምቶች አማካኝነት ዳግም ተመልክቶ “ለሀገር ይበጃል” ያለውን አማራጭ ለይቶ እንደሚያሳውቅ መናገራቸውን ምንጮች ገልጠዋል። 

የአማራ ክልል ተወካዮች ጉዳይ

ኮሚሽኑ የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላትን ሰብስቦ የሽምግልና ኮሚቴ ለማቋቋም መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ ሂደቱ የጉባኤውን አሠራር የጣሰና የምክክር ሂደቱን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩት የአማራ ክልል ተወካዮች፤ “የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች “የገቡልንን ቃል ጥሰዋል” የሚል ተጨማሪ ቅሬታ ማሰማታቸውን ተረድተናል። ኮሚሽነሮች “በጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርበው በሥራ ቡድን ደረጃ የጸደቀው ምክረ ሀሳብ ነው” የሚል የማረጋጋጫ ቃል ለተወካዮቹ መስጠታቸውን ያስታወሱት ምንጮች፤ የሽምግልና ኮሚቴው ስለሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ ቀደም ተብሎ የተነገረ መረጃ አለመኖሩን ገልጠዋል። ኮሚቴው እንዲሁም ያቀረበው ምክረ ሀሳብ የምክክር ጉባኤውን የአሠራር ሂደት ያልተከተሉ መሆናቸውንም ተወካዮቹ መግለጣቸውን ሰምተናል።

የክልሉ ተወካዮች ከአዳራሽ መውጣትን ተከትሎ የክልሉ አመራሮች ተወካዮቹን እንዳነጋገሩ የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ በአመራሮቹ ጥረት “የተወሰኑ” ተመካካሪዎች ወደ አዳራሽ መመለሳቸውን ጠቁመዋል። ጉዳዩ ውሳኔ የተሰጠበት አለመሆኑን  የገለጡት የክልሉ አመራሮች፤ ኮሚሽኑ ለሀገር ይበጃል ያለውን ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ያላቸውን እምነት በመግለጥ ተመካካሪዎችን ለማግባባት መሞከራቸውንም ሰምተናል። በክልሉ ፕሬዝዳንት አረጋ ከበደ መሪነት ወደ ጉባኤው የተመለሱ ተመካካሪዎች የጉባኤውን ሂደት አጠናቅቀው መውጣታቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል።

የምክረ ሀሳቦች ቀጣይ ሂደት

ኮሚሽኑ ከሥራ ቡድኖች የተረከባቸውን ምክረ ሀሳቦች በራሱ መንገድ አደራጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚው አካል እና ለሌሎች የመንግስት አካላት እንደሚያቀርብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ምን አይነት ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል። 

የጉባኤው መጠናቀቅ

ሐምሌ 08 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በይፋዊ መርሃ ግብር ጅማሮውን ያደረገው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ ነሐሴ 16 ቀን ይፋዊ የማጠናቀቂያ መርሃግብሩን እንደሚያከናውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሚገኙበት መርሃግብር እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ጉባኤው፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ የተነሳ ተጽዕኖ ውስጥ የገባ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ]