በኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ ከተካሄደ ሃያ ዓመታት ሊደፍን ነው። ብሄርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ላላት ኢትዮጵያ የህዝብ ቆጠራ ሌላው የፍልሚያ ሜዳ ነው። ቆጠራ እንዳይደረግ የሚፈልጉ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸውም ምስጢር አይደለም።ከአምስት ዓመት በፊት ብዙ ወጪ ከወጣበት በኋላ የታቀደው ቆጠራ ተሰርዟል። አበዳሪ ተቋማት ቆጠራ አካሂዱ የሚል አጀንዳ ይዘው መጥተዋል። በጉዳዩ ላይ ዋዜማ ያሰናዳችውን ዝርዝር ዘገባ አንብቡት
ዋዜማ- ኢትዮጵያ በ 10 ዓመት አንዴ መካሄድ የሚገባውን ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ካካሄደች ሁለት አስርት ዓመታት ሊሞላት ጥቂት ጊዜያት ብቻ ቀርተዋታል። በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እውን መሆን ያልቻለውና በተደጋጋሚ የተራዘመው 4ኛው አገራዊ ቆጠራ፣ አሁንም የሚካሄድበት ትክክለኛ ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሚወሰን ድረስ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጲያ ስታትስቲክስ ማሻሻያ አዋጅን ያጸደቀ ሲሆን፤ የአዋጁ መጽደቅ የመረጃ አሰባሰብ እና ስርጭት እንዲሁም እርስ በርስ የሚጋጩ መረጃዎችን በማስቀረት ሂደት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው ተብሏል፡፡ በተሻሻለው አዋጅ ውስጥ ከተካተቱት ልዩ ድንጋጌዎች መካከል፤ ከመንግስት ምደባ፣ ከአገልግሎትና ስልጠና ክፍያዎች፣ እንዲሁም ከልማት አጋሮች ከሚገኙ ድጋፎች የተደራጀ ሆኖ በመንግስት የበጀት አስተዳደር ሕግ እንዲመራ፤ ክልሎች የራሳቸውን የስታትስቲክስ ህግ ማውጣት ቢችሉም፤ ድንጋጌዎቹ ከዚህ አዋጅ መሠረታዊ መርሆዎች ጋር የተጣጣሙ ወይም ይበልጥ ጥብቅ የሆኑ ደረጃዎችን የያዙ እንዲሆኑ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም፤ በነባሩ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 442/1997 እና የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/14 (አንቀጽ 28/1/ወ እና አንቀጽ 56) ዲጂታል አሰራርን አያካትቱም በሚል ሙሉ በሙሉ ተሽረዋል።
አዋጁ ቆጠራው በምን ያህል ዓመት ልዩነት ወይም በየትኛው ወርና ቀን መካሄድ እንዳለበት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ (ለምሳሌ በየ10 ዓመቱ የሚል ቀጥተኛ አሃዝ) የለም። ይልቁንም ስለ ቆጠራ ጊዜና ዝግጅት በዘረዘረው የአዋጁ ክፍል፤ ቆጠራ የሚካሄደው ወሰኑ በውል በታወቀ ቦታ እና ‹‹በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ›› ብቻ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የህዝብና ቤት ቆጠራ ስራዎች የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 449/97 መሠረት የሚመሩ በመሆናቸው፤ የጊዜ ሰሌዳው በዚያው በልዩ ህጉ በሚቋቋመው ኮሚሽን እንደሚወሰን ነው የሚገልጸው፡፡
ከደርግ መንግስት ጀምሮ የተካሄዱት ቆጠራዎች
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ሶስት ሃገር አቀፍ የህዝብ እና ቤት ቆጠራዎችን አካሂዳለች። የመጀመሪያው የህዝብ ቆጠራ የተካሄደው በ1976 ዓ.ም በደርግ ስርአት ወቅት ነበር። በወቅቱ ቆጠራው የሀገሪቱን የህዝብ ቁጥር 81 በመቶ ብቻ ያካተተ ሲሆን፥ አጠቃላይ የህዝብ ብዛትም 34 ነጥብ 5 ሚሊዮን አካባቢ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱ ሀገሪቱ በ14 ክፍላተ ሀገራት ፣ በሁለት የአስተዳደር አካባቢዎች (አዲስ አበባ እና ዓሰብ)፣ በ101 hአውራጃዎች፣ በ604 ወረዳዎች እና በ819 የከተማ ማዕከላት ተከፋፍላ ነበር። ሆኖም ግን ከጸጥታ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ቆጠራው ሊሸፍን የቻለው 85 አውራጃዎችን፣ 441 ወረዳዎችን እና 668 የከተማ ማዕከላትን ብቻ ነበር።
ቆጠራው ለምን ያህል ጊዜያት ታቅዶ ሳይሳካ ቀረ?
ኢትዮጵያ በየአስር ዓመቱ መካሄድ ያለበትን የህዝብና ቤት ቆጠራ በተለያዩ ጊዜያት ለማካሄድ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፤ ሂደቱ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
የመጀመሪያው ዕቅድ በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 103 መሰረት በ1999 ዓ.ም ከተካሄደው 3ኛው ቆጠራ ከአስር ዓመት በኋላ ሊካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ በወቅቱ በሃገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ለውጥ ሽግግርና አለመረጋጋት ሳቢያ ሳይካሄድ ቀርቷል።
ሁለተኛው ዕቅድ በህዳር 2011 ዓ.ም ነበር፡፡ የጊዜ ሰሌዳው ተሻሽሎ ለህዳር ወር 2011 ዓ.ም እንዲካሄድ ቢወሰንም፤ የዝግጅት ስራዎች ባለመጠናቀቃቸውና በወቅቱ በነበሩ የጸጥታ ስጋቶች ምክንያት ለተጨማሪ ወራት ተራዝሟል።
ሶስተኛው ዕቅድ ቆጠራው ሚያዝያ 2011 ዓ.ም እንዲካሄድ ነበር፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ቆጠራው ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት እንደሚከናወን ይፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም፤ በወቅቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረጉት የጋራ ስብሰባ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም በሚል ቆጠራው ለ3ኛ ጊዜ እንዲራዘም ወስነዋል።
አራተኛው ዕቅድ በ2012 ዓ.ም ነበር፡፡ የጸጥታው ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ተሻሽሎ ሂደቱን ለመጀመር በተሞከረበት ወቅት፤ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መከሰቱ የቤት ለቤት የመረጃ ማሰባሰብ ስራውን ሙሉ በሙሉ በማስተጓጎሉ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ቆጠራው እስካሁን ያልተካሄደበት ዋነኛ ምክንያቶች
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ግንቦት 7 ቀን፤ 2015 ዓ.ም ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፤ ቆጠራው ሳይካሄድ የቀረባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤
ሂደቱ በተለይም፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት እንዲሁም በሃገሪቱ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ተቋርጦ ቆይቷል ብለዋል።
በተጨማሪም፤ አዳዲስ የክልል አደረጃጀቶች እና በክልሎች መካከል ያሉ የወሰን አለመግባባቶች ሂደቱን ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረጉት ጠቅሰው፤ እስከ 2018 ዓ.ም ባሉት 3 አመታት ውስጥ እንደሚካሄድ ተናግረው ነበር፡፡ ይሁንና በ2018 ዓ.ም ተሰናባቹ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስታትስቲክስ ማሻሻያ አዋጁን ከማጽደቅ ውጪ ቆጠራውን ለማካሄድ ቀን አልቆረጠም፡፡
22 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው ታብሌቶች የት ገቡ?
በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም የወጡት መረጃዎች እንደሚያመለከቱት፤ ኢትዮጵያ 4ኛውን ሀገር አቀፍ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ዝግጅት አድርጋ ነበር። በወቅቱ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለቆጠራው አላማ ብቻ የሚውሉ 180 ሺህ ታብሌቶች በአለም አቀፍ ጨረታ መገዛታቸውን በመጥቀስ፤ አስተማማኝነታቸው በ3 ዙር የሙከራ ሂደት ማረጋገጡንም ገልጾ ነበር፡፡
እያንዳንዱ ታብሌት በመለያ ቁጥር በዋናው የመረጃ ቋት የተመዘገበ ሲሆን፤ በላያቸው ላይ የቆጠራ ካርታ፣ የካርታ መግለጫ፣ ቦታ ጠቋሚ እና የመጠይቅ ቅፆች ተጭነውባቸው ዝግጁ መሆናቸው እንዲሁም ቴክኖሎጂው ለቆጠራው ዓላማ ብቻ የተሰራ በመሆኑ ለግላዊ መረጃ መጠቀም እንደማይቻል መግለጹም ይታወሳል፡፡
በቆጠራው ወቅት የሚሰበሰበው መረጃ ከየአካባቢው ወደ ማዕከል የሚተላለፈው ከየትኛውም የሰርቨር መስመር ንክኪ ውጪ በሆነ ልዩ ‹‹የቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ›› (VPN) አማካኝነት ሲሆን፤ ለዚህም ኢትዮ ቴሌኮም 37 ሺህ ልዩ ሲም ካርዶችን አዘጋጅቻለሁ ብሎ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የፈሰሰበት የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ዝግጅት ተጠናቆ የመጋቢት 2011 ዓ.ም የቆጣሪዎች ስልጠና ሊጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ቆጠራው በፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል። ይሁንና ለዚሁ ስራ ተብለው የተገዙት ታብሌቶች አሁን የት ናቸው? የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ከማነጋገሩም ባሻገር፤ ‹‹ታብሌቶቹ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎች ለግል ጥቅም እንዲያውሉት ተሰጥተዋል›› የሚለው መረጃ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
ሁኔታውን አስመልክቶ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የመንግስት ሃላፊዎች ግን፤ ታብሌቶቹ ከቆጠራው መስተጓጎል በኋላ ከማእከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ወጥተው ወደ ሌላ የመንግስት አካል መዛወራቸውን በመጥቀስ፤ መረጃው ትክክል አይደለም ብለውናል፡፡
‹‹የታብሌቶቹ ቴክኖሎጂ ለቆጠራ አላማ ብቻ ከቻይና የመጣ አንድሮይድ 2 ቴክኖሎጂ ነው፤ ከአንድሮይድ 12 በተሻገረበት ዘመን እነዚያን ታብሌቶች አሻሽሎ ለሌላ ስራ ማዋል አይቻልም፤ የሚታደስ ነገርም የላቸውም፤ ስለዚህ በግለሰቦች እጅ ናቸው ማለት አይቻልም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እነዚህ ንብረቶች ለአንድ ዓመት ተኩል የቆጠራ ስራ ተብለው የተገዙ በመሆናቸው፤ ስራው ሲቋረጥ የንብረቱ ባለቤት የሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር ወይም በስሩ ያለው የመንግስት ንብረትና ግዢ አገልግሎት ንብረቱን ተረክቧል። ሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱ ንብረቶቹን ምን እንዳደረጋቸው የሚያውቀው ራሱ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡
በወቅቱ ወጪ የተደረገው የገንዘብ መጠን
ዋዜማ ካሰባሰበችው በወቅቱ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች መሠረት ለቆጠራው ተብለው ለተገዙት 180 ሺህ ታብሌቶች እና 126 ሺህ የሃይል ቋቶች (Power Bank) ግዢ ብቻ ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ (በወቅቱ የምንዛሪ ተመን ከ800 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ) ወጪ ተደርጓል። ይህ ግዢ የተፈጸመው በዓለም አቀፍ ጨረታ አማካኝነት ከቻይና ኩባንያዎች ነበር።
ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ፣ ለሰው ኃይል ስልጠና፣ ለህትመት፣ ለሎጅስቲክስ እና ለቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት የተመደበው ጠቅላላ በጀት ወደ 120 ሚሊየን ዶላር (ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ) ይጠጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል፡፡
ይህ በጀት ከኢትዮጵያ መንግስት በተጨማሪ እንደ የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ (UNFPA) እና የእንግሊዙ አለማቀፍ የልማት ተቋም (DFID) ባሉ የልማት አጋሮች በተገኙ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎች የተሸፈነ ነበር።
የአለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ ግምገማ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ባወጣው 4ኛው የፋይናንስ ግምገማ ሪፖርት፤ ኢትዮጲያ የምታካሂዳቸውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በአግባቡ ለመምራትና ስኬታማነታቸውን ለመለካት የህዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ አስፈላጊ ስለመሆኑ ምክረ-ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የአለም ባንክ ግምገማ መሰረት፤ የግብር አቅምን ለማሳደግ ፣ የወጪ ንግድን ለማጎልበት እንዲሁም የማህበራዊ ድህንነት ድጋፎችን ለትክክለኛው የኅብረተሰብ ክፍል ለማድረስ ወቅታዊና ትክክለኛ ሃገር አቀፍ የህዝብ ቁጥራዊ መረጃዎች በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆናቸው ይጠቁማል፡፡
‹‹የቆጠራው ቀን በፓርላማው እስከሚወሰን እየጠበቅን ነው››
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች እንዳሉት፤ የቆጠራ ሂደቱ በበሽታ ወረርሽኝ፣ በጦርነት እና ተያያዥ ፖለቲካዊ ሁነቶች ሳቢያ ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡ የህዝብና ቤት ቆጠራን በቀጥታ የሚያስፈጽመው የማእከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሚና ቴክኒካዊ ድጋፍ መስጠት በመሆኑ ቆጠራው መቼ ይካሄዳል ለሚለው ጥያቄ ተቋሙ በቀጥታ መወሰን እንደማይችል ነግረውናል፡፡
‹‹መቼ እንደሚካሄድና እንዴት እንደሚከናወን የሚወስነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራውና የክልል ፕሬዝዳንቶች በአባልነት የሚገኙበት ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሚሆነው የቆጠራ ኮሚሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ናቸው፤ ፓርላማው መመሪያ ሲያወርድና ቀን ሲቆርጥ ብቻ ነው ወደ ቆጠራ የምንገባው›› ብለዋል፡፡
‹‹የህዝብ ቁጥር የፖለቲካ ሚዛን ማስጠበቂያ ነው›› ተንታኞች
በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 103 መሰረት ፤ የህዝብ ቆጠራው በየ10 ዓመቱ መደረግ ያለበት ዋና ዓላማ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎችን የሀብት ክፍፍልና የፌዴራል በጀትን ለመወሰን እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ወረዳዎችን ድንበር ለማሻሻል ወቅታዊ የህዝብ ቁጥር መረጃ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
በመንግስት በኩል ከተጠቀሱት እንቅፋቶች በተቃራኒ መልኩ፤ ለክልሎች በየአመቱ የሚመደበው አመታዊ በጀት በህዝብ ቁጥር ላይ የተመሰረተ መሆኑን፤ አለመረጋጋት እና መፈናቀል በተንሰራፋበት በዚህ ወቅት ቆጠራ ቢካሄድ፤ ሌላ መልክ ያለው የጥቅም ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ምናልባትም፤ በክልሎች መካከል የሚኖረው የሃብት ክፍፍል ሽሚያ ሌላ ሃገራዊ ቀውስ ሊቀሰቅስ የሚችል በመሆኑ ሂደቱን ማዘግየት እንደ ጊዜ መግዣ ሊወሰድ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
በተጨማሪም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች፤ የሚደለደሉት በህዝብ ቁጥር ላይ ተመስርተው በሚከለሉ የምርጫ ክልሎች ነው፡፡ ባለፉት 18 አመታት በግጭት እና መፈናቀል፣ በአስተዳደራዊ መዋቅር ለውጥ እንዲሁም በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የህዝብ አሰፋፈርና ስብጥር ለውጥ መኖሩን የሚገልጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ተንታኞች፤ የአዲስ አበባን ሁኔታ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ቆጠራ ከተካሄደ የፓርላማ መቀመጫዎች ስብጥር መለወጡ አይቀሬ ነው፤ ይህ ደግሞ አሁን ላይ በፓርላማው ውስጥ ከፍተኛ ይዞታ ያላቸውን የተወሰኑ አካባቢዎች የውክልና የበላይነት ሊለውጥ ይችላል፤ በዚህ ረገድ የፖለቲካ ስልጣን ሚዛኑ እንዳይናጋ በመስጋት ቆጠራውን የማዘግየት ፍላጎት ሊኖር ይችላል›› በማለት አብራርተዋል፡፡
