ዋዜማ- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ቀደም በክልሉ በቢሮ ደረጃ የነበሩ መዋቅሮችን በኮሚሽን፣ በኢንስቲቲዩት፣ በባለሥልጣን መስሪያ ቤት፣ በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም፣ 5 ተቋማትን በልዩ ሁኔታ ለማዋቀር ረቂቅ ሠነድ ማዘጋጀቱን ዋዜማ ሠምታለች።

ክልሉ ከዚህ ቀደም በቢሮ ደረጃ የነበሩና አሁን በኮሚሽን ደረጃ ያዋቀራቸው መስሪያ ቤቶች፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ሲሆኑ በባለሥልጣን መስሪያ ቤት ደረጃ ያዋቀራቸው ደሞ የቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን እና የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን መሆናቸውን ዋዜማ ከደረሳት ረቂቅ ሰነድ ተመልክታለች።

በአገልግሎት ደረጃ እንደ አዲስ የተዋቀሩ መስሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት ኮምኒኬሽን አገልግሎት፣ የመንግሥት ንብረት ግዢና አወጋገድ አገልግሎት፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት፣ እንዲሁም የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ሲሆኑ፣ በኢንስቲትዩት ደረጃ የተደራጁት መስሪያ ቤቶች ደሞ፣ የእርሻ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኦሮሞ ባህል ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የሕግ ጥናትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት እንዲሁም የፕላን ኢንስቲትዩት መሆናቸውን ዋዜማ ረቂቅ ሠነዱ ተረድታለች።

በልዩ ሁኔታ የተዋቀሩ ተቋማት ደሞ በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያስተዳድር መስሪያ ቤት፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኦ ቢ ኤን)፣ የአደጋ ስጋት (ቡሳ ጎኖፋ)፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ሉዓላዊ ፈንድ መሆናቸውን ዋዜማ ከሰነዱ ተመልክታለች።

ከዚህ ቀደም የነበሩና ባሉበት የሚቀጥሉ ቢሮዎች ተብለው በረቂቅ ሠነዱ የሰፈሩት፣ የትምሕርት ቢሮ፣ ጤና ቢሮ፣ የግብርና ቢሮና፣ የገቢዎች ቢሮን ጨምሮ 21 ቢሮዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ቢሮዎች በስራቸው ሌሎች ንዑስ መስሪያ ቤቶችን እንዲቆጣጠሩና እንዲያስተዳድሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ራሳቸውን ችለው እንዲቀጥሉ በተደረጉ ቢሮዎች ስር እንዲተዳደሩና እንዲቀላቀሉ ከተደረጉ በርካታ ቢሮዎች መካከል፣ በሠላም ቢሮ ስር የጸጥታ እና አሥተዳድር እንዲሁም የሚሊሺያ ጽሕፈት ቤቶች፣ በመአድን እና ኢነርጂ ቢሮ ስር የመአድን እና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ በመሬት ቢሮ ስር የልማት ተነሺዎች ኤጀንሲ፣ በኢንዱስትሪ ቢሮና የልማት ተቋማት ስር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የልማት ተቋማት፣ በፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ስር፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ እና የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲተዳደሩ በረቂቅ ሠነዱ ላይ ሰፍሯል።

በተጨማሪም በማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ስር፣ የሕጻናት፣ የአረጋዊያን፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአቅመ ደካሞች የቤት ግንባታና እድሳት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤቶች እንዲተዳደሩ፣ በስፖርትና ባሕል ቢሮ ስር፣ የባሕልና ቱሪዝም እንዲሁም የስፖርት እና ወጣቶች ጉዳዮች ቢሮ እንዲተዳደሩ መወሰኑን ሰነዱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ሦስት የክልሉ ቢሮዎች ተጨማሪ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው የሚያትተው ረቂቅ ሰነዱ የከተማ ልማት ቢሮ፣ የፕላን ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኦሮሚያ ፖሊስ መሆናቸው ዋዜማ ተረድታለች። [ዋዜማ]