ዋዜማ- በትግራይ ሃይሎች እና በአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) ቁጥጥር ስር ያሉት የዋግኽምራ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ምግብ እና መድሃኒቶችን ጨምሮ መሰረታዊ የሚባሉ ቁሳቁሶች እንዳይገቡ በመደረጋቸው እንዲሁም የባንክ እና ህክምና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች፡፡
ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ ወር መጀመሪያ አካባቢ በዞኑ አበርገሌ ወረዳ የትግራይ እና የአገው ታጣቂዎች በጋራ ሆነው ከመንግስት ሚሊሻዎች ጋር ባደረጉት ውጊያ፤ ከሚያዚያ 12 ቀን ፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው የነበሩት የመንግስት ሚሊሻዎች አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው፤ ላለፉት ሶስት ወራት ያክል በሁለቱ ታጣቂ ሃይሎች ስር ቆይቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በጻግብጂ ወረዳም ግንቦት 18 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ታጣቂ ሃይሎቹ ከመንግስት ሚሊሻዎች ጋር ባደረጉት ውጊያ፤ አካባቢው ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
አካባቢዎቹ በታጣቂ ሃይሎቹ ስር መሆናቸውን ተከትሎ እንደ ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎችም መሰረታዊ ቁሳቁሶች ወደ አካባቢው ከገቡ ወራት መቆጠራቸውን ለዋዜማ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴም ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ገልጸዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከ 4 እስከ 5 ሰአታት በእግር ተጉዘው የዞኑ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሰቆጣ እየገቡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ውስጥ የመንግስት ሃይሎች ሙሉ በሙሉ እንደማይገኙ በመጥቀስ፤ መሰረታዊ የሚባሉት የባንክ እና ህክምና አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ነግረውናል፡፡
መንገዱ የተዘጋበትን ምክንያት ያብራሩት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የጻግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች፤ ‹‹ሚያዚያ ወር ላይ ግጭቱ ሲፈጠር በጅድዋ እና በጠራሪ ወንዝ አካባቢ የተያዙ ከዚህ ቀደም ሸቀጣሸቀጦችን ያስገቡ የነበሩ የግል ተሸከርካሪዎች ነበሩ፤ ባለሀብቶቹ ወደ አካባቢዎቹ ሸቀጣሸቀጥ ብናስገባ ማን ኃላፊነት ይወስድልናል? ምን ዋስትና አለን? የሚል ጥያቄ እያነሱ ነው፡፡ መንግስትም እርዳታ ባስገባ ታጣቂዎቹ ሊዘርፉት ይችላሉ በሚል ምንም እያደረገልን አይደለም›› ብለዋል፡፡
አማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑት ዛታ፣ ኮረም እንዲሁም እስከ ቆቦ ባሉት አካባቢዎች፤ የህዝብም ሆነ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም፤በጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ላይ ግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ሀገር በቀልም ሆነ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ወደ አካባቢው እንዳልደረሱ አስረድተዋል፡፡
የህክምና አገልግሎት መቋረጥ
በአካባቢው ያለው የህክምና አገልግሎት በመቋረጡ፤ በተለይም ለወሊድ የተቃረቡ ነፍሰ ጡር እናቶች ከፍተኛ ደም ፈሷቸው ለህልፈት እንደሚዳረጉ ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በአምቡላንስ እጥረት ምክንያት ታማሚዎችን ከጻታ እስከ ሰቆጣ ያለውን የ40 ኪሎ ሜትር ገደማ መንገድ በቃሬዛ ተሸክመው በእግር ለመጓዝ እንደሚገደዱም ነው ያስረዱት፡፡ ይህም ከ 6 እስከ 7 ሰአታት ይወስዳል ብለዋል፡፡
‹‹ነዋሪዎች እስከ አማራአምባ እና እክመጽራዋ ከተማ ድረስ በእግር ከመጡ በኋላ ነው ወደ ሰቆጣ በመኪና መሄድ የሚችሉት፤ ከእክመጽራዋ ማዶ ያለውን ቀጠና ግን ሙሉ በሙሉ በአዴን እና ትግራይ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ስለሆነ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ አይታሰብም፤ ሁኔታው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ስለሆነ ብዙ ሰው ወደ ሰቆጣ እየሄደ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ባንኮች ከ 1 ሺህ ብር በላይ አይሰጡንም››
ከቀናት በፊት ከጻግብጂ ወረዳ ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ ተጥለለው እንደሚገኙ የነገሩን አንድ ተፈናቃይ፤ በወረዳዎቹ የባንክ አገልግሎት መቋረጡን በመጥቀስ፤ ነዋሪዎች ወደ ሰቆጣ ከተማ በእግር ተጉዘው ገንዘብ እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሞባይል ባንኪንግ ቢሰራም፤ አንዳንድ ግብይቶች በጥሬ ገንዘብ ብቻ የሚሆኑበት አጋጣሚ ስላለ እንቸገራለን፡፡ ጥሬ ገንዘብ ፍለጋ ያንን ሁሉ መንገድ በእግር ተጉዘንም፤ ባንኮቹ በቀን ከ 1 ሺህ ብር በላይ አይሰጡንም›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪም በተመሳሳይ መልኩ የጥሬ ገንዘብ ችግር መኖሩን እና ወደ ሰቆጣ ተጉዘው ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያወጡ ነግረውናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ተጥልለው የሚገኙት የተፈናቀሉ ሰዎች በተለያዩ ጎዳናዎች፣ በትምህርት ቤት እና ክፍት ቦታ ወይም ግቢ ያላቸው የመንግስት ህንጻዎች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸውልናል፡፡
ትራንስፖርት – ‹‹ዋጋ ተወደደ ማለትም ቅንጦት ሆኗል››
በአሁኑ ወቅት ጥቂት መሰረታዊ ሸቀጦችን ከሰቆጣ ተነስተው በአህያ ጭነት በድብቅ ወደ ወረዳዎቹ ለማስገባት ጥረት የሚደረግበት ሁኔታ ቢኖርም፤ መንገድ ላይ ያለው እንግልትና ዘረፋ ሌላው ፈታኝ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ከቀናት በፊትም በሁለቱ ወረዳዎች መካከል በሚገኘው ዲንቃ ቀበሌ አካባቢ ‹‹ጠራሪ ወንዝ›› አቅራቢያ በእግርና በአህያ ይጓጓዙ የነበሩ የእርዳታ እና ሸቀጣሸቀጦች በታጣቂ ሃይሎቹ እንደተዘረፉ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ከጻብታ ወደ ሰቆጣ ለመጓዝ የትራንስፖርት ዋጋ 1 ሺህ ብር ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ዋጋው ከመወደዱ ባለፈ ትራንስፖርት ማግኘት የማይታሰብ ሆኗል ብለዋል።
‹‹ከጥቂት ወራት በፊት ለአንድ ጉዞ 1 ሺህ ብር በጣም ውድ ነው ብለን እንማረር ነበር፤ አሁን ግን ዋጋ ተወደደ ብሎ ማማረርም ቅንጦት ሆኖብናል›› ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ፡፡
በአማራ ክልል መንግስት እና በአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) ታጣቂዎች መካከል የተፈረመው ስምምነት
በጥር ወር አካባቢ በአማራ ክልል መንግስት እና በአገው ሸንጎ ሃይሎች መካከል የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ እንዲመለሱ፣ አገልግሎት እንዲቀጥልና እንቅስቃሴ እንዲኖር በ2016 ዓ.ም ታህሳስ ወር ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
በወቅቱ በታጣቂ ሃይሉ በተያዙት የአበርገሌ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ፤ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እንዲሁም የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዲጀመር ሲደረግ፤በስምምነቱ መሰረት የወረዳው ፖለቲካዊ እና የፀጥታ አስተዳደር በጊዜያዊነት በታጣቂዎቹ ስር እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
በዚህ ስምምነት መሠረት አዴን ትጥቅ በመፍታት እና የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ በመመዝገብ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ትግል ብቻ ለማካሄድ የተስማማ ሲሆን፤ታጣቂ ሃይሉ ያሉትን የጦር መሳሪያዎች ለመከላከያ ሰራዊት እንዲያስረክብ፤ ይህ ሲረጋገጥ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የመልሶ ማቋቋም እና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራዎችን ያከናውናል።
ሆኖም፤ ግጭቱ በአበርገሌ ላይ ዳግም በማገርሸቱና ወረዳው በአዴን ታጣቂዎች እጅ በመውደቁ ምክንያት የተደረሰው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።
ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና የነዋሪዎች ስጋት
በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በታጣቂዎች መካከል የተከፈተ አዲስ ግጭት ባይኖርም፤ ቀደም ሲል በጅድዋ እና ጠራሪ ወንዝ አካባቢ በትግራይ እና በአዴን ሃይሎች የተያዙ የግል ተሸከርካሪዎች በመኖራቸው የደህንነት ዋስትና ማጣት ትልቅ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ሰምተናል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የመከላከያ ሃይል በ15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ ከስጋት ነጻ መሆን አልቻሉም፡፡ የጸጥታና አስተዳደር መዋቅሮች በአገው ዲሞክራሲያዊ ቁጥጥር ውስጥ ቢሆኑም፤ የትግራይ ሃይሎችም በጋራ እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹት ነዋሪዎች፤ የትግራይ ሃይሎች በአካባቢው በአጋርነት የሚንቀሳቀሱት፤ ራሳቸውን ‹‹የትግራይ ሰላም ሃይል›› ብለው የሚጠሩት ‹‹የሓራ መሬት›› ታጣቂዎች ከመከላከያ ጋር ሆነው በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ በመቆየታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከዞኑ ሁለቱ ወረዳዎች በተጨማሪ በሌሎች አማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑት የዞኑ አካባቢዎች የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የታጠቁ ሃይሎች የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ፤ በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍርሃት ውስጥ እንዳሉም አክለዋል፡፡ [ዋዜማ]
