ዋዜማ- የኢትዮጵያ መንግስት ብርን ከስውር የገንዘብ ዝውውር (ክሪፕቶ ከረንሲ) ጥቅም ላይ እንዳይውል እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ዋዜማ ባለፉት ሳምንታት ባደረገችው ማጣራት ለመገንዘብ ችላላች።
ባለፉት ሳምንታት በዋናነት ብሔራዊ ባንክ የሚመራው ይህ ብርን ከስውር የገንዘብ ዝውውር (ክሪፕቶ ከረንሲ) የመነጠል እርምጃ አካል የሆነ በርካቶች የሚጠቀሙባቸውን የመገበያያ መተግበሪያዎች በኢትዮጵያ እንዳይሰሩ እገዳ ተደርጎባቸዋል።
በነዚህ መተግበሪያዎች በመጠቀም የሸቀጥና የአገልግሎት ግብይት የሚፈፅሙ ነጋዴዎች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት አቅራቢዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መስተጓጎል እንደገጠማቸው ነግረውናል።
የባንኩ እርምጃ ባንኩ በውጭ ምንዛሬ ትይይዩ ገበያ ላይ የያዘው ጥብቅ ቁጥጥር አካል መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል፡፡
የባንኩ እርምጃ የኢትዮጵያን ብር የክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያ ያደረጉ ተቋማትን በማግባባት፣ ለባንኮች መመሪያ በመስጠትና መተግበሪያዎች ኢትዮዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ በማድረግ ስልት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በርካታ ደንበኞችን ያፈሩ የክሪፕቶ ተቋማት በኢትዮጵያን ብር የሚደረጉ የክሪፕቶ ምንዛሬ ግብይቶችን እያቆሙ ነው፡፡ እንደ ባይናንስ (Binance)፣ ባይቢት (Bybit)፣ የቴሌግራም ዋሌት (Telegram Wallet) ያሉ ዓለም አቀፍ የክሪፕቶ መገበያያዎች፣ የኢትዮጵያን ብር ከክሪፕቶ ግብይት (Peer-to-Peer) ዝርዝር ውሰጥ ሙሉ በሙሉ አውጥተዋል።
የክሪፕቶ ግብይት በአብዛኛው የሚመራው በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ተመን በመሆኑ፣ ብሄራዊ ባንክ ለነጻ ገበያ ለተወው የውጭ ምንዛሬ ገበያ መረጋጋት እንደ ትልቅ ፈተና ወስዶታል።
ባንኩ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት በብር የሚደረጉ የክሪፕቶ (P2P) ግብይት፣ በኢትዮጵያ ያልተፈቀደ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ገልጦ ነበር። ማንኛውም በብር የሚደረጉ የክሪፕቶ ግብይቶች ያለ ባንኩ ፈቃድ ማከናወን፣ የተከለከለ መሆኑን ማሳሰቡ ይታወሳል።
በዘርፉ ላይ ልምድ ያለውና በአዲስ አበባ በመተግበሪያ አበልፃጊነት እንዲሁም ለአንድ የክሪፕቶ አገበያይ የአፍሪቃ አማካሪ ሆኖ የሚሰራና ስሙን መግለጽ ያልፈቀደ ባለሙያ ለዋዜማ እንዳሰረዳው “አሁን መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ በበቂ መረጃና ብቃት ላይ የተመሰረተ አይደለም” “የክሪፕቶ ግብይት መድረኮች በዓለማቀፍ ደረጃ ለቁጥጥር አመቺ አይደሉም”
ከሁለት ወራት በፊት ይህ ባለሙያ የተሳተፈበትና መንግስት በዘርፉ ላይ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችለው ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ያለመ ውይይት መረደጉን ያስታውሳል።
በብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሰማነው ደግሞ መንግስት የገንዘብ ማሸሽ ፣ ለወንጀል ቡድኖች ገንዘብ ለማሸጋገር ፣ ለህገወጥ ንግድና ውንብድና ክሪፕቶ ጥቅም ላይ ይውላል የሚል ስጋት ስላለው እርምጃ ለመውሰድ መነሳቱን ግን ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የአቅም ውስንነት እንዳለበት ያስረዳሉ።
የማግባባት አርምጃ
የክሪፕቶ ከረንሲ የግብይት መድረኮች ለቁጥጥር አዳጋችና በመንግሥታት የማይመሩ መሆናቸው ይታወቃል። ታዲያ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እነዚህ መንግሥታት የማያዟቸውን የክሪፕቶ ገንዘብ መገበያያዎች በቀላሉ ትዕዛዙን እንዲያከብሩ ማድረግ ችሏል።
የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት ስርአት ንግድ ባንኮችን እና እንደ ቴሌብር ያሉ የሀገር ውስጥ ገንዘብ መቀበያዎችን በመጠቀም፣ ደንበኞች እርስ በእርሳቸው በቀጥታ በኢትዮጵያን ብር እንዲገበያዩ የሚያስችል ዲጂታል ገንዘብ መገበያያ መድረክ ነው። የክሪፕቶ መገበያያ መድረኮች የሀገራትን ገንዘብ የሚጠቀሙት ከማዕከላዊ ባንኮች ፈቃድ አግኝተው ሳይሆን፣ ለደንበኞቻቸው አማራጭ ለማስፋት በራሳቸው ፍላጎት ነው።
የኢትዮጵያን ብር ይዘው ሰዎች ክሪፕቶ ዝውውር ላይ የሚጠቀሙበት የመገበያያ ገንዘብ ፣ ከአሜሪካ ዶላር ጋር አቻ ዋጋ ያለውን USDT የተባለው ክረንሲ ነው።
የመጀመሪያው የማግባቢያ ዘዴ፣ አንዳንዶቹ ተቋማት በኢትዮጵያ የክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራ ላይ ስለተሰማሩ፣ ከብሄራዊ ባንክ የደረሳቸውን ትዕዛዝ በቀጥታ ለመቀበል ተገደዋል። በኢትዮጵያ የመረጃ ቋት የሌላቸው የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት አሳላጮች ተቋማትም፣ ወደፊት ይፈጠራል የተባለውን ማዕቀፍ ተስፋ በማድረግ የባንኩን ማግባቢያ ለመቀበል መፍቀዳቸውን ተረድተናል። ለወደፊት ከመንግስት ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነትና ጥቅም አስልተው የመንግስትን ጥያቄ ተቀብለዋል።
ኹለተኛው የቁጥጥር መንገድ የኢትዮጵያ ባንኮችና ዲጂታል የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን፣ የቁጥጥር አካል ማድረግ ነው። ብሄራዊ ባንክ የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት በሚል፣ ባንኮች ከክሪፕቶ ግብይት ጋር የተያያዙ ሂሳብ ቁጥሮች በአንክሮ እንዲከታተሉ እና እንዲያግዱ መመሪያ አስተላልፏል።
ሦስተኛው የቁጥጥር አማራጭ የክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያ መተግበሪያዎች እና በይነ መረቦችን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ ማድረግ ነው። እንደ ባይናንስ ያሉ ትልልቅ የክሪፕቶ መገበያያዎች በኢትዮጵያ ኢንተርኔት እንዳይሰሩ እገዳ (IP Blocking) ገደብ ተጥሎባቸዋል።
በብዛት ኢትዮጵያ ውሰጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ የክሪፕቶ መገበያያ መድረኮች በኢትዮጵያ ኔትዎርክ እንደማይሰሩ ዋዜማ አረግጣለች። በአንጻሩ የኢንተርኔት አድራሻ ሀገር ለውጥ በማድረ (VPN) የመገበያያ መተግበሪያዎቹ ይሰራሉ።
የወጣቶች ፈተና እና አዲስ መንገድ
በርካታ ወጣቶች ክሪፕቶ ከረንሲን እንደ ውጭ ምንዛሬ ንግድ (Forex Trading)፣ በዓለም አቀፍ ዲጂታል የክፍያ አማራጭነትና በውጭ የርቀት ሥራዎች እንደ ገንዘብ መቀበያ ይጠቀሙበታል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብር አገልግሎት እንዳይሰጡ የተደረጉ የክሪፕቶ ግብይት መድረኮች፣ ለበርካታ ወጣቶች የርቀት ሥራ ክፍያ አማራጭ ሆነው ያገለግሉ ነበር። ምንም እንኳን አሁንም ከፍያቸውን በክሪፕቶ ከረንሲ መቀበል የሚችሉ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ ብር መንዝረው መጠቀም ግን አይችሉም።
የማኅበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች፣ እንደ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ሊንከድን ላሉ ድርጅቶች ክፍያ የሚፈጽሙት በክሪፕቶ ከረንሲ ነበር። የኢትዮጵያ ብር ከክሪፕቶ ገበያው መውጣቱን ተከትሎ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ማስታወቂያ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ሥራቸውን ለማቋረጥ እየተገደዱ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች።
ምንም እንኳን ብሔራዊ ባንክ የክሪፕቶ መገበያያዎች ብርን ከአማራጫቸው እንዲያስወጡ ቢያደርግም፣ አሁንም በሌላ አማራጭ ግብይቱን ለማሳለጥ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ዋዜማ ተረድታለች። አዲሱ የክሪፕቶ ግብይት በኢትዮጵያ ብር የሚካሄደው፣ ገዥ እና ሻጮችን በኮሚሽን ከፍያ በሚያገናኙ ሦስተኛ ወገን ደላሎ በኩል ነው።
በአሁኑ ወቅት ግብይቱን እያሳለጡ የሚገኙ አካላት፣ የክሪፕቶ መድረኮች ከገበያ ያስወጡትን የኢትዮጵያ ብር ከዓለም አቀፋ ዲጅታል ገበያ ሙሉ በመሉ እንዳይከስም እያደረጉ ይገኛሉ። [ዋዜማ]
