FILE


ዋዜማ- በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሱዳን ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው የኩርሙክ ወርቅ ፕሮጀክት በማሊና አይቮሪ ኮስት ካሉ ሌሎች የወርቅ ማዕድን ይዞታዎች ጋር ተዳምሮ ለቻይናው ዝጅን ኩባንያ በ4 ቢሊየን ዶላር ሊሸጥ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች።

ያለፉትን አመታት የግብፅ እጅ የነበረበትና የህዳሴው ግድብ አቅራቢያ በመገኘቱ ስጋት የፈጠረው ፕሮጀክት ወደ ቻይናው ኩባንያ መሸጋገሩ ለስጋቱ እልባት እንደሚሰጠው ይታመናል።


ከፍተኛ የወርቅ ክምችት እንዳለበት በሚታመነውና ከአሶሳ እስከ ሱዳን ድንበር በተንሰራፋው የመቶ ኪሎሜትሮች የኩርሙክ ወርቅ ፕሮጀክትን እስካሁን ይዞ ያስተዳድር የነበረው አላይድ ጎልድ ኩባንያ ፕሮጀክቱን ለቻይናው ዝጅን ኩባንያ ለማስተላለፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የአለማቀፍ ፋይናንስ ገበያ ዘገባዎች አመልክተዋል።

አላይድ ጎልድ በማሊና አይቮሪኮስት ካሉት ይዞታዎች የኢትዮጵያው ኩርሙክ በመጠኑ ከሌሎቹ ከፍ ያለና ሃያ አንድ ሺህ ቶን የተረጋገጠ ክምችት እንዳለው ይታመናል።


ይህ የወርቅ ፕሮጀክት ለአስር ዓመታት ያህል የግብጹ አስኮም ሆልዲንግስ ኩባንያ ይዞት የነበረ ሲሆን አስኮም የግብጽ ወታደራዊ የንግድ ተቋማት ቃላ ሆልዲንግስ አንዱ አካል ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የወርቅ ፕሮጀክቱ ከህዳሴው ግድብ ጋር ባለው መቀራረብ ሳቢያ የግብፁ አስኮም ለቆ እንዲወጣ መደረጉን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ያስረዳሉ።


ይሁንና አስኮም ግልፅ ባልሆነ መንገድ የፕሮጀክቱን ባለቤትነት ራሱ በእጅ አዙር ለሚቆጣጠረው ለአላይድ ጎልድ አስተላለፈ። የግብፁ አስኮም በአላይድ ጎልድ ውስጥ ድርሻ ያለው ሲሆን አሁን ከሽያጩ ዳጎስ ያለ ገንዘን እንደሚያገኝ ተሰምቷል።


የአላይድ ጎልድን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የሚመሩት አድራሻቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት አቶ ብሩክ ወርቁ(Brox Worku)ና የቀድሞው የሕወሓት ታጋይ አቶ ሙልጌታ ኃይለማርያም ናቸው። ይህን ፕሮጀክት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባይደግፈውም በፌደራሉ መንግስት ይሁንታና ግፊት አላይድ ጎልድ እስካሁን በይዞታው ላይ ቆይቷል።


ከፕሮጀክቱ በይፋ ወርቅ ማውጣት ባይጀመርም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለስልጣናት ግን ከአካባቢው በድብቅ ወርቅ እየወጣ ወደሌሎች ሀገራት እንደሚሻገር እንደሚያውቁ ይናገራሉ።


ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከአምስት ወራት በፊት ይህን ፕሮጀክት ሲጎበኙ ፕሮጀክቱ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ ጠቅሰው “ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት” ሲሉ ጠርተውታል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አላይድ ጎልድ ይፋ እንዳደረገው አሁን ፕሮጀክቱን ከቻይና መንግስት ጋር ቁርኝት ላለው ዝጅን ኩባንያ በ4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለመሸጥ ተስማምቷል። ዝጅን ኩባንያ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ፒንግ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው ከሚባሉት የቻይና ኩባንያዎች አንዱ ነው።


በአፍሪቃ የካናዳ ኩባንያዎች በማዕድን ዘርፍ ላይ በስፋት ተሰማርተው የሚገኙ ቢሆንም በአለማቀፉ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥና እየገጠማቸውን በመጣው የፋይናንስ ዕጥረት ከቻይና ኩባንያዎች ጋር አንድም በሽርክና ወደ መስራት ሲሸጋገሩ ሌላም ጊዜ ፕሮጀክቱን ለቻይና በመሸጥ ከገበያው ሲወጡ ታይተዋል።[ዋዜማ]