ዋዜማ- በተለያዩ የሰራ መስኮች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ፍንጭ መገኘቱን ተከትሎ፣ ብሎም የዲግሪ ወረቀት ሽያጭ እንደነበረ ከተደረሰበት በኋላ፣ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱ ባንኮች ውስጥ ያሉ ሰራተኞች የትምሕርት ማስረጃ ላይ ማጣራት እንዲደረግ አዟል።
ባንኮች የአያንዳንዱን ሠራተኛቸውን ከመጀመሪያ ዲግሪ በፊት ያለው የትምህርት ማስረጃ እንዲመረምሩና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል አረጋግጠው እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መምሪያ መስጠቱን ዋዜማ ሰምታለች፡፡
በመመሪያው መሰረት እያንዳንዱ ሠራተኛ የዲግሪ ትምህርቱን ከመጀመሩ በፊት ያለውን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ መቅረብ አለበት፡፡
ባንኮች ሠራተኞቻቸውን ወደ ዲግሪ ትምህርት የተሸጋገሩበትን፣ የ12ኛ ክፍል ሰርተፍኬት ወይም ዲፕሎማ (ደረጃ አራት) አረጋግጠው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ማለፊያ ነጥብ አስመዝግበው በቀጥታ ወደ ዲግሪ ትምህርት የገቡ የባንክ ሠራተኞች፣ ከኢትዮጵያ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ተብሏል፡፡
ሠራተኞች የሚያቀርቡት የ12ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ከአገልግሎቱ ለማግኘት በአካል ወይም በዲጂታል አማራጭ በተዘጋጀው ድረ-ገጽ መጠቀም ይችላሉ፡፡
በዲፕሎማ (ደረጃ አራት) የትምህርት ማስረጃ ዲግሪ የተማሩ ሠራተኞችም በተመሳሳይ፣ ከሚመለከታቸው የክልልና ከተማ አስተዳደር ተቋማት ማረጋገጫ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሠራተኞች ለዲግሪ ትምርት መግቢያ ያስመዘገቡት የዲፕሎማ ማስረጃ ትክክለኛነት የሚረጋገጠው ማስረጃው ከተገኘበት ክልል የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ እና ከተማ አስተዳደሮች የሥራ እና ሥልጣና ቢሮዎች ነው፡፡
ባንኮች ይህንኑ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ለሰራተኞቻቸው ማሳወቃቸውንም ዋዜማ ተረድታለች።
አንዳንድ ባንኮች ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መረጃ ላስመዘገቡ ስራተኞቻቸው ላይ ያተኮሩ ሲሆን አስከትለው የሁሉንም ሠራተኞች መረጃ የማረጋገጥ እቅድ ይዘዋል።
ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከማውረዱ በፊት አንዳንድ ባንኮች በራሳቸው ተነሳሽነት የሠራተኞቻቸውን የትምህርት ማስረጃ የማረጋገጥ ሙከራ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ አሰራራቸው፣ ከመሰረቱ ሀሰተኛ ባለ ዲግሪዎችን ለመለየት አያስችልም የሚል ትችት ቀርቦበታል።
ባንኮች ከዚህ ቀደም በራሳቸው መንገድ የሞከሩት የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ አሰራር፣ የሠራተኛ ዝርዝር ልኮ ከዩኒቨርስቲዎች ማረጋገጫ መጠየቅ ላይ የተመሰረተ ነው። በተለይ የግል ዩኒቨርሲዎች በኩል ‘ተማሪያችን ነበሩ’ ወይም ‘አልነበሩም’ የሚል ምላሽ በቂ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ መሆኑ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቁጥጥርና ክትትል አሰራሩ የፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው፣ በዲግሪ ወረቀት ሽያጭ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል። በዚሁ ምክንያት የትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በራሳቸው የዲግሪ ወረቀት አትመው መስጠት እንዳይችሉ አግዷቸዋል።
ባለሥልጣኑ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው ማጣራት በ10 ዓመት ካስመረቁት 1.1 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ከ100 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የትምህርት ማሰረጃ ያስመዘገቡ መሆናቸውን እንደደረሰበት መግለጡ ይታወሳል።
ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከተገኘባቸው ግለሰቦች መካከል ከፌደራል እሰከ ክልል የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ይገኙበታል ተብሏል ። [ዋዜማ]
