- ለአንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 10 ብር ተጨማሪ ክፍያ ይጠየቃል
በተለያዩ ንግድ ባንኮች ለውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ከተቀመጡ ህጋዊ ክፍያዎች በተጨማሪ አሁንም ተጨማሪ ገንዘብ እየተጠየቀ እንደሆነ ዋዜማ መረዳት ችላለች።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምርትን በማስመጣት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሲጠየቁ “የለንም” በማለት ፣ በሂሳባቸው ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ካላቸው ደንበኞቻችን ጋር “እናገናኛችሁ” በሚል ግብዣ በአንድ የአሜሪካ ዶላር ከ6 እስከ 10 ብር ተጨማሪ እንድንከፍል እንጠየቃለን ብለዋል። ዋዜማ ይህ አይነቱ ክፍያ እየተጠየቀ ለመሆኑም ሁለት ባንኮች ከተፈጸሙ ክፍያዎች አይታ ማረጋገጥ ችላለች።
አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነጋዴ ለውጭ ምንዛሬ ሽያጭ መከፈል ካለበት ህጋዊ ክፍያ ውጭ የሚጠየቁ ክፍያዎችም የአንድ የአሜሪካ ዶላር ለመግዛት የሚጠየቀውን ዋጋ ከ155 እስከ 160 ብር አድርሶታል ብለውናል። እኚህ ነጋዴ ለ5000 የአሜሪካ ዶላር 780, 000 ብር (ለአንድ ዶላር 156 ብር) መክፈላቸውን ነግረውናል።
አሁን ባለው አሰራር ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላር ሲሸጡ መጀመርያ እንሸጥበታለን ብለው በማህበራዊ ድረገጻቸው ላይም ሆነ ቢሯቸው ላይ ከለጠፉት ዋጋ ውጭ ፣ የአገልግሎት 12 በመቶ ካስከፈሉ በሁዋላ ፣ ለአገልግሎት ከተከፈለው ላይ ደግሞ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ወይንም ቫት ይቆርጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ነው ለአንድ የአሜሪካ ዶላር ከ6 እስከ 10 ብር የሚጠይቁት። ይህም ክፍያ የሚጠየቀው “የውጭ ምንዛሬ ስለሌለ የውጭ ምንዛሬ ካላቸው የባንክ ደንበኞች ጋር እናገናኛቹ” በሚል ነው ብለውናል አስተያየታቸውን የሰጡን ነጋዴ።
ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምርት አስመጪነት ላይ የተሰማሩ ነጋዴ እንዲሁ ” እየሆነ ያለው ነገር ምርጫ ያሳጣን ነው ” ብለው ” ሌላ አማራጮችን እንዳንጠቀም መንግስት ፍራንኮ ቫሎታን ከልክሏል ፣ ፍራንኮ ቫሎታ የተከለከለው ደግሞ በባንኮች በቂ የውጭ ምንዛሬ መቅረብ ይችላል በሚል ነው።
ባንኮችን የውጭ ምንዛሬ በምንጠይቅበት ጊዜ ደግሞ የሚሰጠን ምላሽ በተቃራኒው ነው ” ብለውናል። “ይህ የሚያሳየውም መንግስት እንደሚለው በቂ የውጭ ምንዛሬ ንግድ ባንኮች ዘንድ የለም ፣ ካልሆነም ተጨማሪ ገንዘብ ለመጠየቅ ሰው ሰራሽ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈጠረ ነው ” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በቅርቡ ለመንግስት መገናኛ ብዙሀን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ መንግስት መተግበር ጀምሮታል ባሉት”የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን” ተከትሎ የማእከላዊ ባንኩ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከእጥፍ በላይ ማደጉን ፣ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ክምችትም ከፍተኛ ጭማሬን ማሳየቱን ገልጸው ነበር።
የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በሁዋላ በወርቅ እና ቡና በጥቂት ወራት ውስጥ ተገኝቶ የማይታወቅ በእያንዳንዳቸው ምርቶች የውጪ ንግድ አንድ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱም ተነግሯል። ካለፈው አመት ሀምሌ 22 በኋላም ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና አለም ባንክን ከመሰሉ አበዳሪዎች 1.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድርን አግኝታለች።ሆኖም የውጭ ምንዛሬ እጥረት አሁንም በስፋት ይሰማል። [ዋዜማ]