- ሀገሪቱ በዩሮ ቦንድ የወሰድኩት ብድር እንደማንኛውም ብድር ሊራዘምልኝ ይገባል ስትል ጠይቃለች
ዋዜማ- ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2014 ከአለም ገበያ በዩሮ ቦንድ የተበደረችው የአንድ ቢሊየን ዩሮ የዋናው እዳ መክፈያ ጊዜው ሊደርስ ጥቂት ወራት በቀሩት በዚህ ጊዜ ; የመክፈያ ጊዜው ይራዘምልኝ ብላ ስለመጠየቋ ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሹሞች ዋዜማ ሰምታለች።
የኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ እዳን የመክፈል ጉዳይ አሁን ወደ ትልቅ አጀንዳነት መጥቷል። ይህም የሆነው ሀገሪቱ ዋናውን ብድር ማለትም አንድ ቢሊየን ዩሮውን በአንድ ላይ ከመክፈሏ በፊት በየጊዜው ስትከፍለው የነበረውን ወለድ መክፈሏ አጠራጣሪነቱ ከተነገረ ወዲህ ነው። ዛሬም ላይ ሀገሪቱ የዚህ የዩሮ ቦንድ ወለድ አካል የሆነውን 33 ሚሊየን ዶላር መክፈል እንዳለባት ይጠበቃል።
“ዋናው የኛ ጉዳይ ኢትዮጵያ ወለዱን 33 ሚሊየን ዶላሩን የመክፈል ያለመክፈሏ ጉዳይ ሳይሆን : የአንድ ቢሊየን ዩሮው ዋናው ብድር የመክፈያ ጊዜው ለሀገሪቱ ይራዘምላት የሚለው ነው” ብለውናል ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጫችን።
ምንጫችን አክለውም “33 ሚሊየን ዶላሩን መክፈል እንችላለን ፣ ግን አሁን እያደረግን ያለነው የዋናው ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ፣ ወለዱ እንዲቀንስ መደራደር ነው” ብለውናል።
ሆኖም ኢትዮጵያ 33 ሚሊየን ዶላር ወለዱን መክፈል ትችላለች : ልትከፍልም ትችላለች ከማለት በዘለለ በእርግጠኝነት ትከፍላለች አላሉንም።
የኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ወለድ ክፍያ ጉዳይ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል መባሉን ተከትሎም ሀገሪቱ እዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ተርታ ልትመደብ ነው የሚሉ ዘገባዎች ተበራክተዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በኩል ሀገሪቱ በዩሮ ቦንድ የወሰደችውን አንድ ቢሊየን ዩሮን ከአለም አቀፍ ተቋማት እና መንግስታት እንደ ወሰደቻቸው ብድሮች ጋር በጋራ የመክፈያ ጊዜው እንዲራዘምላት ነው።
እንደ ዩሮ ቦንድ አይነት ብድሮች ግን ከግል አበዳሪዎች የሚገኝ በመሆኑ የመክፈያ ጊዜ ይራዘምልኝ የሚል ጥያቄ እንዲሁም የመክፈያ ጊዜን የማራዘም ነገር በአለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ አለመሆኑ ይታወቃል።
ከሶስት አመት በፊትም ሀገሪቱ የእዳ ሽግሽግ ጥያቄን ለነ ፓሪስ ክለብ ስታቀርብ : የዩሮ ቦንድ መክፈያም ጊዜ እንዲራዘምላት እንደምትፈልግ ስትገልጽ በቦንዱ ባለቤቶች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ ከመፍጠሩም በዘለለ ትርፉም ቀንሶ ነበር።
ሀገሪቱ አሁን የዩሮ ቦንድ እዳዋን ከመክፈል አንጻር የገባችበት ውዝግብ ወደፊት ከብድር አንጻር የሚኖራት ታማኝነት እና ከተመሳሳይ ገበያዎች የምታገኘው ብድር መኖሩ ላይ ከባድ ጥርጣሬን የሚያሰፍን መሆኑን ባለሙያዎች ነግረውናል።
በ2006 ዓ.ም በፈረንጆቹ 2014 ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ ገበያ በዩሮ ቦንድ አንድ ቢሊየን ዩሮን ለመበደር የበቃችው ፣ የሀገራትን ብድር የመክፈል አቅም የሚለኩት እንደ ፊች ; ፑር እና ሙዲ የመሳሰሉ ተቋማት በአማካይ ቢ የተሰኘውን እና በአንጻሩም ጥሩ የተባለ ደረጃ ሰጥተዋት ነው።
አሁን ሀገሪቱ ብድሩን መክፈያዋ ጊዜ ሲደርስ እነዚሁ የሀገራትን ብድር የመክፈል አቅም የሚለኩ ተቋማት ደረጃዋን በእጅጉ አውርደው cc- ድረስ ዝቅ አድርገውታል። ያኔም ብድሩ የተወሰደው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ በማዋል ምርታማነትን አሳድጎ ብድሩንም መመለስ ይቻላል በሚል ነው።
ከዚያ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ጦርነት እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝም ታክሎበት ኢኮኖሚዋ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል።በዩሮ ቦንድ ከተበደረችው ብድር ባለፈ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታት የተበደረቻቸውን ብድሮች የመክፈሏ ነገር ችግር ውስጥ ስለገባ የብድር መክፈያ ጊዜዋ እንዲራዘምላት ከአበዳሪዎቿ ጋር ተደጋጋሚ ድርድሮችን ስታደርግ ቆይታለች።
ሆኖም ድርድሩ ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ እና ሀገሪቱ ከብድር እና እርዳታ እየተገለለች መጥታ ብድር መክፈል እያቃታት በመሆኑ የብድር መክፈያ ጊዜ ሽግሽግ ድርድሩ እስኪሳካ ጊዜያዊ የብድር መክፈያ ጊዜ የማራዘም መርሀግብር ውስጥ ተገብቷል።
ሀገሪቱ በዚህ አመት መክፈል ካላባት ብድር ውስጥ 1.5 ቢሊየን ዶላሩ እንዲራዘምላት በቻይና : በፓሪስ ክለብና ሌሎች አበዳሪዎች ተፈቅዶላታል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይህ አይነቱ አካሄድ በዩሮ ቦንዱም ላይ እንዲደገም ፍላጎታቸው መሆኑን ቢገልጹም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ያሉ ሁኔታዎች የዩሮ ቦንድ ብድሩን እጣ ፈንታ ግልጽ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሀገሪቱ ከ28 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ብድር እንዳለባት ይታወቃል። [ዋዜማ]