ዋዜማ- የአዲስ አበባ መስተዳድር በስሩ ለሚገኙ ከጽህፈት ቤት እስከ ወረዳ ደረጃ መዋቅር ላሉ ሰራተኞቹ የምዘና ፈተና ሊስጥ ነው። ፈተናውን ማለፍ የማይችሉ በአቅማቸው ይመደባሉ አልያም መቋቋሚያ ተከፍሏቻው ከስራ ይሰናበታሉ። ከሰሞኑ ፈተናውን የሚወስዱ ተቋማት ተለይተዋል። ሁሉም ሰራተኞች እስከ ጥር ወር ድረስ ለፈተና ይቀመጣሉ። ዝርዝሩን ዋዜማ እንደሚከተለው አስናድታዋለች። አንብቡት

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር አዲስ የመዋቅራዊ ማሻሻያ አደረጃጀት ጥናት ባደረጉ ተቋማት ለሚገኙ ኹሉም ሠራተኞቹ እና የሥራ ሂደት መሪዎቹ የብቃት መመዘኛ ፈተና ሊሰጥ በዝግጅት ላይ መሆኑን  ዋዜማ ሰምታለች። 

በመጀመሪያው ዙር የብቃት ምዘና ፈተና የሚሰጠው ለቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት፣ የሥራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ፅሕፈት ቤት፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ፅሕፈት ቤት፣ ኅብረት ሥራ ፅሕፈት ቤት እና የመሬት ልማት አስተዳደር ፅሕፈት ቤት ሲሆን፤ የብቃት ምዘናው በክፍለ ከተሞች እና በከተማው አስተዳደር ጭምር ባሉት መዋቅሮች መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። 

እነዚህ ተቋማት ቀደም ብለው አዲስ ውስጣዊ የአደረጃጀት ጥናት ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ እንደ አዲስ በተዋቀሩ የሥራ መደቦች የብቃት ፈተናውን ተፈትነው ማለፊያ ውጤት ያመጡ ሠራተኞች እና የሥራ ሂደት መሪዎች ብቻ እንደሚመደቡም ዋዜማ ሰምታለች። 

ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የአሥፈፃሚ ተቋማትም የመዋቅር ጥናታቸውን ሲጨርሱ ለሠራተኞቻቸው የብቃት መመዘኛ ፈተናው የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል። ፈተናውን ለሚወስዱት ሠራተኞች እና ባለሙያዎች የተቀመጠው የማለፊያ ውጤት 50 በመቶ ሲሆን፣ የሥራ ሂደት መሪዎች ደግሞ 60 በመቶ ማምጣት እንዳለባቸው መታዘዙን ዋዜማ ተገንዝባለች። 

ዋዜማ የተመለከተችው ለዚህ ማስፈፀሚያ የተዘጋጀው መመሪያ፣ ፈተናውን ለማያልፉ ሠራተኞች ኹለት የውሳኔ አማራጮች የቀረበ ሲሆን፤ አንደኛው አማራጭ ድልድል ከመካሄዱ በፊት አጭር ሥልጠና ወስደው ለመጨረሻ ጊዜ ፈተናውን ድጋሚ እንደሚወስዱ ይገልፃል። ሌላኛው በመመሪያው የተጠቀሰው አማራጭ፣ ማለፊያ ውጤት ያላገኙት ሠራተኞች ወደ ሌላ ተቋም ተዛውረው፣ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት እና በነበራቸው ደሞዝ እንዲመደቡ ማድረግ ወይም ቋሚ የማቋቋሚያ ድጋፍ ተደርጎላቸው ከሥራ እንዲሰናበቱ ማድረግ መሆኑ ተስተውሏል። 

ፈተናውን ማለፍ ያልቻሉ በተለይም የሥራ ሂደት መሪዎች ከነበሩበት የሥራ መደብ ዝቅ እንደሚሉ እና ማለፊያ ውጤት ሳያመጡ ባሉበት ተቋም የሚቀጥሉ ሠራተኞችም ማለፊያ ውጤት ላመጡ ሠራተኞች የሚደረገውን የደሞዝ ጭማሪ ወይም የደረጃ ዕድገት እንደማያገኙ ዋዜማ ተገንዝባለች። 

ከብቃት ምዘናው በፊትም፣ እድሜያቸው ለጡረታ የደረሱ ሠራተኞች በፍቃደኝነት የጡረታ መብታቸው እንዲከበር እንደሚደረግም ዋዜማ በተመለከተችው ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። 

የብቃት ምዘና ፈተናውን ተከትሎ ከከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች እና የክፍለ ከተማ መመሪያዎች ይልቅ የወረዳ ጽህፈት ቤቶች የበለጠ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው ሊደረግ እንደሚችልም ተመላክቷል። 

የብቃት ምዘናውን በተመለከተም፣ አዲስ የሪፎርም አደረጃጀት ጥናት ባደረጉ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ባመለከቱበት የስራ መደብ ላይ ለመወዳደር የሚያገለግሉ ሰባት የባህርያዊ እና ሰባት የቴክኒካል ብቃቶች ላይ የሚያተኩር አዲስ የፁሑፍ ፈተና እንደሚጠብቃቸውም ዋዜማ ተረድታለች።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዲገለፁ ያልፈለጉ አንድ በኮልፌ ቀራኒዮ የወረዳ 06 ባለሙያ፣ የሚሰጠውን የብቃት ምዘና ፈተና የሚያስፈጽም ኮሚቴ መዋቀሩን እና በአንዳንድ ወረዳዎችም በሰው ኃይል ፅሕፈት ቤቱ እና በሠራተኞች መካከል ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። 

ባለሙያዋ በጉዳዩ ላይ ሠራተኞች ከሰው ሃብት ፅሕፈት ቤት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፣ ዋና ዓላማው የሠራተኛውን ቁጥር በመቀነስ የሥራ ጥራትን ማምጣት እና የሠራተኞችን ኑሮ ማሻሻል ነው መባሉን ለዋዜማ ተናግረዋል። ውይይቱን ተከትሎም ሠራተኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን ለአወያዮች ማቅረባቸውን ጠቁመው፣  ፈተናውን ለሁለተኛ ጊዜ ተፈትነው ማለፍ ለማይችሉ ሠራተኞች ከሥራ እንዲቀነሱ ምክንያት ይሆናል የሚል ብርቱ ስጋት መፍጠሩንም አመልክተዋል። 

ሌላው የዋዜማ ምንጭ እና በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በባለሙያነት የሚያገለግሉ ነባር ሠራተኛ እንዳሉት ደግሞ፣ እስከ ትናንት ሐሙስ ድረስ የክፍለ ከተማው አመራሮች ከሠራተኞቹ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አለማድረጉን ጠቅሰው፣ በዚኽ የተነሳም ሠራተኛው ልንባርረ እንችላለን በሚል ከባድ ስጋት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል። 

“ከተለያዩ የትምሕርት መስኮች እንደመምጣታችን፣ በምን መልኩ ለፈተናው መዘጋጀት እንዳለብን እንኳን ባለማወቃችን ተጨንቀናል” ላሉት እነዚህ ሠራተኞች ይዘጋጃል የተባለው ፈተና፣ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጀመር እና ከጥር ወር በፊት እንደሚጠናቀቅ የጠቀሱት ምንጫችን፣ ለዚህም የአዲስ አበባ፣ የደብረ ብርሃን እና የኮተቤ እና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲዎችን ጨምሮ የብቃት ምዘና ፈተና የማዘጋጀት ልምድ ባላቸው ሌሎች ዩንቨርሲቲዎችም ፈተናው እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል። 

ከተማ አስተዳደሩ የምዘና ፈተናውን በመስጠት አዲስ የሥራ ድልድል ከማድረጉ በፊት፣ በአንዳንድ ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች የሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ቀድሞ የተጣራ ሲሆን፣ በአንዳንዶች ደግሞ ገና በመጣራት ሂደት ላይ ይገኛል። ለአብነትም ዋዜማ የተመለከተችው የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በስሩ ለሚገኙ የተለያዩ የወረዳ ጽህፈት ቤቶች ኅዳር 23/2016 ዓ.ም. በፃፈው ደብዳቤ፣ ፅሕፈት ቤቶቹ የሠራተኞቻቸውን የ8ኛ፣ የ10ኛ፣ የ12ኛ እና ከዲፕሎማ ጀምሮ ያሉ የመመረቂያ የምስክር ወረቀቶችን፣ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) ማስረጃዎችን እስከ ኅዳር 30/2106 ዓ.ም. በአስቸኳይ እንዲላክለት ጠይቋል። [ዋዜማ]

To contact Wazema Editors please write to wazemaradio@gmail.com