- አሁን ባንኮች እያቀረቡበት ያለው ዋጋ ከጥቁር ገበያውም የበለጠ ሆኗል
ዋዜማ – በሀገር ውስጥ ያለው ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች በተለይም የግሎቹ ምንዛሪን ለሚጠይቋቸው ደንበኞች የሚያስከፍሉት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለምንዛሪው እለታዊ መሸጫ ካወጣው የዋጋ ተመን በላይ መሆኑን ዋዜማ ካደረገችው ቅኝት መረዳት ችላለች።
ለአንድ የአሜሪካ ዶላር ከግል ባንኮች እየተጠየቀ ያለው ኮሚሽንም ከ55 ብር እስከ 60 ብር መሆኑንም ከባንኮቹ እንዲሁም የተጠየቀውን ያክል ኮሚሽን ከፍለው ምርት ከውጭ ለማስመጣት ምንዛሬን ካስፈቀዱ ነጋዴዎችም መረዳት ችለናል።ይህም የአንድ የአሜሪካ ዶላር የባንኮች መሸጫ ዋጋን በድምሩ ከ110 እስከ 115 ብር አድርሶታል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከሰሞኑ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን እንዲሸጡ ያወጣው እለታዊ ዋጋ 54 ብር ከ82 ሳንቲም ነው። ምንዛሪውን የፈለገ የባንክ ደንበኛም በብሄራዊ ባንክ የተቀመጠው ዋጋ ላይ ከ55 እስከ 60 ብር ኮሚሽን መክፈል ይጠበቅበታል።
በዚህም ዋጋ ቢሆን ምንዛሬው እንደልብ እንደማይገኝ እና የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ በባንኮች ያላቸው ግለሰቦችን እና ምንዛሪውን የሚፈልጉ ደንበኞችን የባንክ ሰራተኞች እንደ ደላላ በማገናኘት ግብይቱ እንደሚፈጸምም መረዳት ችለናል። ምንዛሪ ፈላጊዎች የሚከፍሉትን ኮሚሽንም ባንኮቹ እና የምንዛሪ ተቀማጭ ያላቸው ግለሰቦች እንደሚካፈሉትም ተረድተናል።
ለውጭ ምንዛሪ እየተከፈለ ያለው ኮሚሽን ብሄራዊ ባንክ እያወጣው ካለው ዋጋ መብለጡም በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ ደረጃ መድረሱን አመላካች መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች ገልጸውልናል።
በባንኮች የሚደረገው የምንዛሬ ሽያጭም በትይዩ ወይንም በጥቁር ገበያ ካለው ጋር ተመሳሳይ እየሆነ መጥቷል። አስመጪዎች ሀገር ውስጥ በብር ክፍያ ፈጽመው ውጭ ሀገር ባሉ ሰዎች ለሚፈልጉት እቃ በውጭ ምንዛሪ ክፍያ ተፈጽሞላቸው እቃ ለማስገባትም (በተለምዶ ሀዋላ የሚባለው) ለአንድ የአሜሪካ ዶላር በተመሳሳይ 105 ብር እየከፈሉ ነው።
በዚህ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሳቢያም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይ የማያባራ የዋጋ ንረትን ሊጋፈጥ እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ነው።
የውጭ ምንዛሪን አብቃቅቶ ለመጠቀም መንግስት ለ38 አይነት ምርቶች በባንኮች የውጭ ምንዛሬ እንዳይፈቀድ ማዘዙም ዋጋውን ሊያረጋጋ አልቻለም።
የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ያደረግ የነበረውን የምንዛሪ አቅርቦት ከፈጸመ አመታት መቆጠሩም ችግሩን አባብሶታል። ከሶስት አመት በፊት ብሄራዊ ባንኩ ለግል ባንኮች ብቻ የምንዛሬ ገበያን ለማረጋጋት 100 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላርን እንደ ምንዛሪ ግኝታቸው እየመዘነ አከፋፍሎ ነበር። ሆኖም ከዛ ጊዜ በኋላ ለግል ባንኮች የቀረበ ምንዛሪ የለም።
መንግስታዊው ንግድ ባንክም ለምርት አስመጭዎች ምንዛሪን ብዙም አልፈቀደም። እነዚህ ሁኔታዎች የተጠራቀመ ችግር ፈጥረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ባለፈችበት ጦርነት እና እፈጽመዋለሁ ያለቻቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በፍጥነት አልፈጸመችም ተብሎ በመታሰቡ ከአለም ባንክ፣ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም እንዲሁም ሌሎች አበዳሪዎች ልታገኝ የነበረውን ብድር አዘግይቶባታል።
የብድር ክፍያ ጊዜዋን ለማራዘም እና ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የቡድን 20 አባል ሀገራት ካዘጋጁት ማእቀፍ ጋር የምታደርገው ድርድር ውጤትም አዝጋሚ ሆኗል። የዚህ በጀት አመት የስድስት ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም 1.7 ቢሊየን ገደማ ሆኖ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ማነሱ እጥረቱን እንዳያብሰው ያሰጋል። [ዋዜማ]