ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሚያ ክልል አካል የሆነው የገላን ከተማ ልዩ አስተዳደር በአጎራባች የአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ባለው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ግልፅ የአስተዳደር ወስን ባልተበጀላቸው አካባቢዎች ለመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የመሬት ዕዳላ እያካሄደ መሆኑን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ባሉ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ ዋዜማ ራዲዮ ባደረገችው ቅኝት በኦሮምያ ክልል የገላን ከተማ አስተዳደር ለተለያዩ የከተማው መስሪያ ቤት ሰራተኞች መሬት እያደለ እንደሆነ ተመልክተናል።
ያለ ግልጽ የአስተዳደር ወሰን የኦሮምያ ክልል የሚሰጠው መሬት በአዲስ አበባ ያሉ የወረዳ አስተዳደሮችን ብዥታ ውስጥ ከቷል።
የዋዜማ ሪፖርተር በጎበኘው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስር ያለው ወረዳ 13 ውስጥ የገላን ከተማ አስተዳደር መሬቶ እየሸነሸነ እየሰጠ እንደሆነ አረጋግጠናል። መሬቱ የሚሰጠውም ወረዳ 13 ቱሉዲምቱ ኮንደሚኒየም ጀርባ ባለው ሰፈር ነው።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የወረዳው ሰራተኞች ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት የገላን ከተማ አስተዳደር መሬቱን የሚያድልበት አካባቢ ያሉ ሰፈሮች ለበርካታ አገልግሎቶች ወረዳውን እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ።
የኦሮምያ አካል የሆነው የገላን ከተማ አስተዳደር የወረዳው ወሰን ውስጥ ገብቶ ለከተማው መምህራን መኖርያ ቤት መስሪያ መሬት መስጠቱም መደናገር እንደፈጠረባቸውና ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የሆነው ወረዳ አመራር አካላትም ለዚሁ ድርጊት ዝምታን እንደመረጡ ሰራተኞቹ ነግረውናል።
የገላን ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ አካል በሆነው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሰፈሮች ውስጥ መሬትን ሲያድልም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን በካሳ እንዲነሱ በማድረግም ጭምር እንደሆነ እንዲነሱ ከተነገራቸው አርሶ አደሮች ሰምተናል።
የገላን ከተማ አስተዳደር በዚሁ አካባቢ የሰጠው መሬት እያንዳንዱ 140 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ፣ መሬቱ ከተሰጣቸው ግለሰቦች አንዳንዶቹ መሬቱን በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ፣ ሽያጩ የሚስተናገደውም በገላን ከተማ መሆኑን የዋዜማ ሪፖርተር መሬት ገዥ በመምሰል ከሻጮች መረዳት ችሏል። መሬቱም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ጀምሮ እንደቦታው አቀማመጥ ይሸጣል።
በተመሳሳይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም አካባቢ ያሉ አካባቢዎች ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ የኦሮምያ ገላን ከተማ ለክልሉ የመንግስት ሰራተኞች መሬት እየሰጠ መሆኑን ታዝበናል። ይህ አካባቢ በ2011 አ.ም የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖርያ ቤት ለባለ እድለኞች በዕጣ ሲወጣ የውዝግብ መንስዔ በመሆኑ ቤቶቹን የማስረከቡ ሂደት እንዲዘገይ ተደርጓል።
ከሶስት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ እና የኦሮምያ የአስተዳደር ወሰን መፍትሄ እንዲያገኝ ኮሚቴ የተቋቋመ ቢሆንም ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ለውይይትም ሆነ ለአደባባይ ያበቃው አማራጭ የለም።
ሌላው በኦሮምያ ክልል ይዞታ ስር ባለው ገላን ከተማ በኩል ለኦሮምያ ክልል መምህራን መሬት እየተሰጠ ያለው አካባቢ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ተብሎ በሚጠራው ገላን ኮንደሚኒየም አካባቢ ነው። በዚህ ስፍራ በገላን ከተማ የተሸነሸነው መሬት በሜቴክ ስር ያለው አቃቂ ቤዚክ ሜታል ፋብሪካ ድረስ ይዘልቃል።
ሆኖም መሬቱን ከተቀበሉት ግለሰቦች አንዳንዶቹ ለሶስተኛ ወገን ሸጠውት ቅንጡ ቤቶች እየተገነቡበት መሆኑን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል። በነዚሁ አካባቢዎች ተጠሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ስር ላለ የወረዳ ጽህፈት ቤቶች ነው።
የገላን ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]