ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ ከሚሰሩበት የኢትዩ ሲሚኒቶ ፋብሪካ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በድንጋይ ማውጫ ካምፕ በስራ ላይ የነበሩና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱት 27 የፋብሪካው ሰራተኞች 18ቱ ሐሙስ ዕለት መለቀቃቸውን ዋዜማ ሰምታለች ::
ከሁለት ሳምንት በፊት በታጣቂዎች ስር የቆዩት 21 ኢትጵያውያንና 6 የሕንድ ዜጎች ሲሆኑ አሁን የተለቀቁት 18 ቱ ኢትዩጵያውያን ብቻ ናቸው።
የድርጅቱ ሰራተኛ የሆኑ 6 ሕንዶች እና 3 አስተርጓሚዎች አሁንም በታጣቂዎቹ እንደተያዙ ይገኛሉ::
ሰራተኞቹ በታገቱበት ወቅት ከታጣቂዎቹ ጋር ሰራተኞቹን ለማስለቀቅ የገንዘብ ድርድር ሲያደርጉ ነበር የተባሉ 4 የኢትዩ ሲሚንቶ ሰራተኞች ደግሞ በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
የዋዜማ ምንጮች እንደነገሩን 18ቱ ታግተው የነበሩ ሰራተኞች ሊለቀቁ የቻሉት በአካባቢው በሚገኙ ተሰሚ ሰዎች ሽምግልና ነው ::
በዕገታ ላይ ስላሉትና እና ከአጋቾቹ ጋር ሲደራደሩ ነበር ስለተባሉትና በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው የሚገኙት 4 የፋብሪካው ሰራተኞችን በተመለከተ ዋዜማ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አራርሳ መርዳሳ የእጅ ስልክ ላይ ደውላ ነበር። ታጋቾቹ ስለመፈታታቸው አልሰማሁም ላጣራ ካሉ በኋላ በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቻልንም። [ዋዜማ ራዲዮ]