FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያውን የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ከመጋቢት 2 እስክ 4 2014 ዓ.ም ለማድረግ ፕሮግራም መያዙን ዋዜማ ሰምታለች።


የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ምክርቤት ያካቲት 16 እና 17: 2014 ዓ.ም እያካሄደ በሚገኘው ስብሰባው ከሚገነጋገርባቸው አጀንዳዎች መካከል የዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት አንዱ መሆኑን ከፓርቲው ምንጮች ለመረዳት ችለናል።


ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል የፓርቲውን ፕሮግራም ማጽደቅ አዳዲስ አመራሮች መምረጥ እንዲሁም የፓርቲውንጨየቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት አዳምጦ ውሳኔ ማሰለፍ የሚገኙበት መሆኑን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23 ቀን 2014 ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር በምርጫ ህጉ መሠረት ከ6ተኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱና የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ የተገለፀላቸው ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ መወሰኑ በምክክሩ ወቅትም ለፓርቲዎች መገለጹ ይታወሳል።


በዚህም መሰረት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ከተገለጸላቸው 26 አገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች መካከል ብልጽግና ፓርቲ ይገኝበታል። [ዋዜማ ራዲዮ]