የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና ሌሎች ሹማምንት ከስልጣናቸው ይነሳሉ። ዋዜማ ራዲዮ ባለስልጣናቱ የሚነሱበት ምክንያት ምንድ ነው? በሚል የነበሩትን ሂደቶች ተመልክተናል። አንብቡት
ዋዜማ ራዲዮ- ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ካቢኒ አባላት በተለይ በታከለ ኡማ እና እንዳወቅ አብጤ መካከል የነበረው የእርስ በርስ አለመተማመንና ተደጋጋሚ መወቃቀስ የከተማው አስተዳደር የሀላፊዎች ለውጥ ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል።
በተለይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) አባሎቼ በከተማው መዋቅር ውስጥ የነበራቸውን ቦታ እንዲያጡ ተደርገዋል ብሎ ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርብ ተሰምቷል። የማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ከንቲባ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት እንዳወቅ አብጤ በመገናኛ ብዙሀን ላይ የአዴፓ አመራሮች ከላይ እስከ ታች ባለው የከተማው አስተዳደር መዋቅር እንደተገፉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው።
ዋዜማ ከታማኝ ምንጯ እንደሰማቸው ታድያ ከዚህ የአዴፓ የከተማ አስተዳዳደሩ ወኪሎች የሚያነሱትን ቅሬታ ተከትሎ ግምገማ እንዲረግ ፣ በከተማ አስተዳደሩ ያለው በተለይም በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) አባላት መካከል ከላይኛው እስከ ታችኛው የከተማው አስተዳደር መዋቅር ድረስ ያላቸው የስልጣን ክፍፍል እንዲገመገም ተወስኖ ነበር። በዚህ የግምገማ ሂደት ላይ አዴፓንና ኦዴፓን ወክለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ መገኘታቸውን ማወቅ ችለናል።
የስልጣን ክፍፍሉ ላይ በተደረገ ግምገማም ሁለት ነገሮች ተገኝተዋል።በጥቅሉ በከተማ አስተዳደሩ ያሉ የሀላፊነት ቦታዎች ሲቆጠሩ አዴፓ መጠነኛ ብልጫ እንዳለው ተለይቷል። ነገር ግን በከተማ አስተዳደሩ ቁልፍ ቦታ ተብለው በሚወሰዱ ተቋማት ውስጥ ባለ የስልጣን ክፍፍል ግን ኦዴፓ ብልጫ እንዳለው ታውቋል።በዚህም ምክንያት አዴፓ በከተማው ያለው ተጽእኖ ዝቅተኛ እንደሆነ ማሳመን ችሏል።
በሌላ በኩል በታከለ ኡማ እና እንዳወቅ አብጤ መካከል ተደጋጋሚ አለመግባባቶች እንዳሉ ሰምተናል። አቶ እንዳወቅ በየመድረኩ አቤቱታን በተደጋጋሚ የሚያቀርቡ ሰው ሆነዋልም ተብሏል።ይህም በታከለ ዘንድ በስልት የሚታገልና አማራጭ የሚያመጣ አመራር ሳይሆን በአቤቱታ የሚያምን ነው እንደሚባሉም ከምንጫችን ሰምተናል።እንዳወቅ አብሯቸው ባይሆን የታከለ ምርጫም ነበር።
በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ያለ አመራር በብሄርም ሆነ በሌላ መንገድ የሚቀርበውን ሰው መሰግሰግ ላይ ትኩረት እየተረገ ለህዝቡ የሚሰጥ አገልግሎት ላይ በፊትም ያለ መዳከም መቀጠሉ ፣ በዚህም ምክንያት በተለያዩ የከተማው መስሪያ ቤቶች ያሉ ሰራተኞች ተረጋግቶ ከመስራት ይልቅ ለቀው የመውጣት ከፍተኛ አዝማሚያን አሳይተዋል ተብሏል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ምክትል ታከለ ኡማ የከተማ አስተዳደሩ የበላይ እንደመሆናቸው እንጂ በግለሰብ ደረጃ ለነበረው ብልሽት ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብሎ እንደተለየ ለማወቅ አልቻልንም።
በግምገማው ላይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ በተገኙበት የግምገማ ስብሰባ ላይ ሁለቱ ምክትል ከንቲባዎቹ እና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች ” እናንተ የከተማውን ነዋሪ አቀረርቦ ለመምራት አትሆኑም ” በሚል አይነት ንግግር ውረፋ ደርሶባቸዋል።
በዚህም ሳቢያ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና እንዳወቅ አብጤ እንዲሁም የከተማው የአዴፓ እና የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች ጸጋ አራጌ እና ተስፋዬ በልጅጌ ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል። የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ አወቀ ሀይለማርያምም ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ከተወሰነባቸው ውስጥ ናቸው።
የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ምክትል ከንቲባና የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊው ሰለሞን ኪዳኔ የዚህ ውሳኔ አካል ይሁኑ አይሁኑ ግን ዋዜማ ራዲዮ ማረጋገጥ አልቻለችም። የተነሱት አመራሮችም ለትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ሊሄዱ ይችላሉ ተብለናል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከተነሳ የቁልፍ ስልጣን ክፍፍል ኢ- ፍትሀዊነት ውጭ ፣ የከተማው ነዋሪ ላልሆኑ ግለሰቦች በገፍ መታወቂያ መስጠት ፣ በስመ ተፈናቃይ አርሶ አደር የጋራ መኖርያ ቤቶችን በመጠቃቀም ለመስጠት የመፈለግ አዝማሚ በከፍተኛ የፌዴራል መንግስት አካላት ጭምር ሊታወቅ እንደቻለ ተረድተናል። እነዚህ ጉዳዮች እንደ ተጨማሪ ታዩ እንጂ ዋና መገማገሚያ እንዳልነበሩ የዋዜማ ምንጮች ገልጸውልናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መልካም ግንኙነት የላቸውም ፣ እንዲነሱ የመወሰኑም ምክንያት ይኸው ነው የሚሉ አስተያየቶች ተሰምተዋል።ለምንጫችን በዚህ ላይ ላነሳንላቸው ጥያቄ የሰጡን ምላሽ ; ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከንቲባ አሿሿም ላይ ተዘዋዋሪ ስልጣን ያላቸው ቢሆንም የአሁኑ ውሳኔ ግን በታከለና አብይ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በተነሱ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ላይ ነው ብለውናል።
ታከለ ኡማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሀላፊነት ሲመጡ ለሳቸው ሲባል የከተማው ቻርተር ተሻሽሎ በመሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ከዚህም ከዚያም ሲሰማባቸው ቢቆይም የሰሯቸው መልካም የስራ ጅምሮች እንዳሏቸው ግን ይታወቃል። ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ የመስጠት ፍጥነት እንዲጨምር አድርገዋል። በቅርቡ ብዙዎች በመልካም የሚያነሱላቸው ደግሞ ለከተማው ተማሪዎች ደብተርና ዩኒፎርም በነጻ እንዲሰጥ የማስተባበር ስራ መስራታቸው አስመስግኗቸዋል። በተለይ ለ300 ሺህ ተማሪዎች የዘወትር ምሳና ቁርስ ምገባ እንዲጀመር ማድረጋቸውም በጉልህ የሚጠቀስላቸው ነው።የዚህ የምገባ መርሀ ግብር ተቋማዊነትና ዘላቂነቱ ላይ ጥያቄ ቢነሳም የዚህ አመት ምገባ ግን አስተማማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ከምንጫችን ተረጋግጦልናል። በከተማው አዳዲስ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲጀመሩና የተጀመሩትም እንዲፋጠኑ ጥረዋል ።
ታከለ ኡማን የሚተኩ ሶስት እጩዎችም መቅረባቸውንም ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች ። የገቢዎች ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ ካሳሁን ጎፌ ፣ የአዳማው ከንቲባ አሰግድ ጌታቸው ታከለን ለመተካት በእጩነት ቀርበዋል። ማን የመጨረሻ ተመራጭ እንደሆነ ግን እስካሁን ስለመለየቱ አልሰማንም። ለገቢዎች ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ ሰፊ ግምት ቢሰጥም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሀላፊነት በመስራትና ከተማውን በተሻለ ሁኔታ በመገንዘብ የማይታሙት አሁን የአዳማ ከንቲባ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት አሰግድ ጌታቸውም የታከለ ምትክ የመሆናቸው እድል ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ነገር ግን ተተኪዎቹ በሙሉ የኦዴፓ ሰዎች በመሆናቸው ፤ ለታከለ ኡማ በተስተካከለው ቻርተርም ስልጣን የሚይዙም በመሆኑ አሁንም የስልጣን ጊዜያቸው ከውዝግብ አያመልጥም። [ዋዜማ ራዲዮ]