Meles Zenawi

ዋዜማ ራዲዮ- የጤፍን የባለቤትነት ጉዳይ በተመለከተ ከሰሞኑ ግር የሚያሰኙ ዘገባዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀንና በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል። የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሳይቀር የጤፍ የባለቤትነት መብት በህግ ለኢትዮጵያ ተረጋገጠ፣ ባለቤትነታችን ተመለሰ ሲሉ ዘግበዋል። መረጃው ትክክል አይደልም። የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ እንደተናገረውና እኛም ስለጉዳዩ ከሚያውቁ ጠይቀን እንደተረዳነው ነገሩ እንዲህ ነው።
ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ጤፍን ፈጭቶና አሽጎ ለገበያ የሚያቀርበው ኤንሸንት ግሬይን (Ancient Grain) የባለቤትነት ህጋዊ መብት ፓተንት ወስዶ የኛኑ ጤፍ ሲቸበችብ ከርሟል። የባለቤትነት ህጋዊ መብት ፓተንት ማውጣቱ እንኳን የታወቀው ከአራት ዓመት በፊት ነው። ቤክልስ (Bakels) የተባለ ሌላ ዳቦ ጋጋሪ ኩባን ያ ከጤፍ የተሰናዳ ዳቦ ገበያ ላይ ማቅረቡን ያስተዋውቃል። ያኔ ነው ኤንሸንት ግሬይን ህጋዊ ባለመብት እኔ ነኝ ብሎ ወደ ፍርድ ቤት የሄደው። አሁን ፍርድ ቤቱ ኤንሸንት ግሬይን የባለቤትነት ህጋዊ መብት ፓተንት የጠየቀበት “ጤፍን ፈጭቶ ፣ቀላቅሎና አቡክቶ ማዘጋጀት የሰው ልጅ በኑሮ ክህሎት የሚማረው ተራ የምግብ አዘገጃጀት እንጂ የባለቤትነት ህጋዊ መብት ፓተንት ጥበቃ የሚያስፈልገው አይደለም” ሲል ክሱን ውድቅ አድርጎ የባለቤትነት መብቱን ሽሮታል።
እርግጥ ነው የኤንሸንት ግሬይን የባለቤትነት መብት መነጠቅ ለኢትዮጵያ መልካም ዜና ነው። ቢያንስ አሁን የጤፍ የባለቤትነት ጥያቄን የሚያነሳ አካል የለም። ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ማለት አይደለም። ነገ ከነወዲያ ማናቸው አካል ተነስቶ የባለቤትነት ጥያቄን ቢያነሳ ምንም አይነት ህጋዊ ከለላ የለንም። እናም የሰሞኑ የጤፍ ባለቤትነት ት ተወሰነልን የሚለው ዘገባ የተጋነነና በበቂ መረጃ ላይ ያልተመረኮዘ ነበር። ለመሆኑ በአድባራችን በቀያችን የሚበቅለውና የኛ ብቻ የሆነው ጤፍ እንዴት በባዕዳን እጅ ገባ? ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ ምን ያልተነገረ ነገር አለ? የጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሚና ምን ነበር? ከታች የድምፅ ዘገባችን ላይ ዝርዝሩን ያገኛሉ

https://youtu.be/O8kquSy14Gs