ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ የዐረብ ኤምሬትሱ ዱባይ ፖርትስ (Dubai Ports) ና ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም የደረሱበት ስምምነት ሞቃዲሾን አስቆጥቷል። የሀገሪቱ ፓርላማም ስምምነቱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ፓርላማው ከአንድ ተቃውሞና ከአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በስተቀር በሙሉ ድምጽ ስምምነቱን ውድቅ ሲያደርግ የሦስትዮሽ ስምምነቱ የሱማሊያን ሕገ መንግስት የጣሰ፣ ዐለም ዐቀፍ ሕግን ያልተከተለ እና ለሱማሊያ ሉዓላዊነት አደጋ የሚደቅን ነው በማለት ነው፡፡ ውዝግቡም ከቀጠናው እና ከባህረ ሰላጤው ጅኦፖለቲካ ጋር የሚቆራኝ በመሆኑ የከረረ ዲፕሎማሲያዊ አተካሮ እንደሚፈጥር ተሰግቷል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያና ሱማሊያ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ተብሎም ተገምቷል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]
በርበራ ከሁለት ዐመት በፊት ለዱባዩ ወደብ ድርጅት ከተሰጠ ወዲህ የሱማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲያወግዙት ቢቆዩም ሰሞኑን ለኢትዮጵያ የተሰጠው የ19 በመቶ ድርሻ በፊርማ መጽደቁን ተከትሎ ግን ፓርላማው ስምምነቱን ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ነው ያሳለፈው፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላም የላይኛው ፓርላማ በተመሳሳይ ውድቅ ያደረገው ሲሆን አሁን የሀገሪቱ ሕግ ለመሆን የሚጠበቀው የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ፊርማ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የሱማሊያ ፓርላማ የሦስትዮሽ ስምምነቱን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ የሱማሌላንድ ፓርላማ የዛኑ ዕለት አጽድቆታል፡፡ የሱማሌላንድ ባለስልጣናት የወደብ ስምምነቱን ከኢምሬትስ ጋር የፈጸሙበት መንገድ ሚስጢራዊና ሙስናም ሊኖርበት እንደሚችል በሱማሌላንድ ውስጥ ስር የሰደደ ጥርጣሬ ቢኖርም የሞቃዲሾውን ውሳኔ ግን ፓርላማው በጥድፊያ እንዲያጸድቀው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል፡፡
ሱማሊያ “ሕገ ወጥ” በማለት ውድቅ ያደረገችው ስምምነት የበርበራውን ብቻ አይደለም፡፡ በሌላ የዱባይ ኩባንያ የተያዘውን የፑንትላንዱን ቦሳሶ ወደብ ስምምነት ጭምር እንጅ፡፡
ኢትዮጵያ ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል የጅቡቲ ወደብን በከፍተኛ ክፍያ ስትጠቀም ብተቆይም በቀይ ባህር ወደብ የአክሲዮን ድርሻ ስታገኝ ግን በርበራ የመጀመሪያዋ መሆኑ ነው፡፡ እናም ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ሀገር አንድ ትልቅ እምርታ እንደሆነ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ምክንያቱም በጅቡቲ ወደብ ተርሚናል መጨናነቅና ዋጋ ንረት ሳቢያ ለጉዳት ለተዳረገው የሀገሪቱ ወጭና ገቢ ንግድ መተንፈሻ እንደሚያገኝ ተስፋ ያተደረገው በበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ነውና፡፡ በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ከበርበራ ወደ መኻል ሀገር የሚወስደውን አውራ መንገድ የመገንባት ሃላፊነት አለበት፡፡
ስምምነቱ 51 በመቶውን ድርሻ ለዱባዩ ዐለም ዐቀፍ ወደቦች ድርጅት(Dubai Ports)፣ 30 በመቶውን ለሱማሌላንድ፣ 19 በመቶውን ደሞ ለኢትዮጵያ ነው የደለደለው፡፡ በዐለም በትልቅነቱ አራተኛ የሆነው የዱባዩ ኩባንያም ለወደቡ ማስፋፊያና ተዛማጅ ልማቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ የመደበ ሲሆን ሦስቱ ሀገሮች ወደቡን የሚስተዳድር አዲስ የጋራ ኩባንያ እንደሚያቋቁሙ ይጠበቃል፡፡ ስምምነቱ ግዙፍ የሥራና ኢንቨስትመንት ዕድል እንደሚፈጥርና መሰረተ ልማትን እንደሚያስፋፋ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ተጨማሪ አዲስ ወደብም ይገነባል፡፡
ለሁለት ዐስርት ዐመታት ከዐለም ዐቀፍ ንግድ ልውውጥና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተገልላ ለኖረችው ራስ ገዟ ሱማሌላንድ የበርበራ ወደብ የሦስትዮሽ ስምምነት የሚያስጎመጅ እና ዐይኗንም ለዐለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ እንድትከፍት እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡ የወደቡ መልማት ምጣኔ ሃብቷን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚያሳድገው ዐለም ዐቀፍ ዕውቅና ለማግኘትም ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ የዱባዩ ኩባንያም በርበራን የአፍሪካ ቀንድ የንግድና ሎጅስቲክ ማዕከል ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡
የጦርነት አዋጅ
በቅርቡ ስልጣን የተረከቡት አዲሱ የራስ ገዟ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ “የጦርነት አዋጅ” ሲሉ አውግዘውታል፡፡ ውሳኔውን ግን መንግስታቸው የጠበቀው ስለሆነ እምብዛም የተደናገጠ አይመስልም፡፡ እንደ መንግስታቸው እምነት ሱማሊያ ለሩብ ክፍለ ዘመን በሱማሌላንድ ላይ አንዳችም ሉዓላዊ ቁጥጥር ስለሌላት መንግስታቸው የገባው ስምምነት ሕጋዊ ነው፡፡ እንዲያውም “በሉዓላዊው ግዛቴ እና በገዛ ይዞታዬ ያሻኝን ባደርግ እናንተ ምን ጥልቅ አደረጋችሁ?” በማለት ነው አጸፋውን ለፕሬዝዳንት ፎርማጆ መንግስት የሰጠው፡፡ የቃላት ጦርነቱ ከወዲሁ የተጧጧፈ ሲሆን ሱማሌላንድ ራስ ገዝ ከሆነች ወዲህ የበርበራው ውዝግብ ከባዱ እንደሚሆን ነው ታዛቢዎች ከወዲሁ እያስጠነቀቁ ያሉት፡፡ የዱባዩ ወደብ ድርጅትም “ስምምነቱን የፈጸምኩት ካንድ ነጻ መንግስት ጋር ነው” በማለት ውሳኔውን አጣጥሎታል፡፡
የፎርማጆ መንግስት በውሳኔው ከሱማሌላንድ፣ ኢምሬትስና ኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌላኛዋ ራስ ገዝ ፑንትላንድ ጋር ጭምር ነው አተካራ ውስጥ የሚገባው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው P&O የተባለው የዱባይ የወደብ ኩባንያ ቦሳሶ ወደብን ለ30 ዐመት ተረክቦ እያስተዳደረ ሲሆን ለወደቡ ማስፋፊያም ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድቧል፡፡
ሱማሊያ የሞቃዲሾ ወደብን የቱርክ ኩባንያ በኮንትራት የሰጠች ሲሆን አሁን በመንግስት እጅ የሚገኘው ኪስማዩ ወደብ ብቻ ነው፡፡ ኢምሬትስ ሱማሊያ ላይ ደኅና መሰረት ካላት ቱርክ ጋር በወደብ ቅርምት እና ጦር ሰፈር ግንባታ ውድድር ውስጥ የገባች ሲሆን የቀድሞ ሱማሊያዊያን ባለስልጣናትን በአማካሪነት በመቅጠርና በረብጣ ዶላር በመደለል በአፍሪካ ቀንድ ከበባዋን አጠናክራለች፡፡
የበርበራው ውዝግብም የዕለቱለት ነው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከባህረ ሰላጤው ሀገሮች ጋር ባላቸው የጅኦፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ ላይ መንጸባረቅ የጀመረው፡፡ የሱማሌላንዱ ፕሬዝዳንት የተቃዋሚ ፓርቲውን መሪ አስከትለው የዕለቱለት ለውይይት ወደ ኢምሬትስ ያቀኑ ሲሆን የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ፎርማጆም በበነጋው የኢምሬትስ ባላንጣ ወደሆነችው የክፉ ቀን ደራሻቸው ኳታር ድጋፍ ለማግኘት ተጉዘዋል፡፡ ሱማሌላንድ እና ፑንትላንድ በባህረ ሰላጤው ቀውስ ከሱማሊያ ፌደራላዊ መንግስት በተቃራኒ ከተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስና ሳዑዲ ጎን ነው የቆሙት፡፡
እዚህ ላይ ሱማሊያ ስምምነቱን ለማሰናከል ምን ልታደርግ ትችላለች? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያላት ሱማሌላንድ ስለወደፊቱ ዕጣ ፋንታዋ ከሞቃዲሾ ጋር እንድትደራደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዐለም ዐቀፍ ግፊቱ የጠነከረባት ሲሆን የፎርማጆ መንግስትም ይህንኑ ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ነው የበርበራው ዐለም ዐቀፍ ስምምነት ተቀባይነት እንዳይኖረው የዲፕሎማሲ ዘመቻውን ያጧጧፈው፡፡
የዓረብ ሊግ ድጋፍ
ከሳምንት በፊትም ፕሬዝዳንት ፎርማጆ ስምምነቱን በመቃወም ለዐረብ ሊግ አቤት ብለው የነበረ ሲሆን ዐረብ ሊጉም ባወጣው መግለጫ በሱማሊያ የአየርና የየብስ ሉዓላዊ ግዛት ላይ መወሰን የፌደራል መንግስቱ ስልጣን መሆኑን አስምሮ ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ ያም ሆኖ ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በሊጉ ውስጥ ካላቸው ቁልፍ ሚና አንጻር ሊጉ ምን ያህል ለሱማሊያ ተስፋ ይሆናት ይሆን? የሚለው ማጠራጠሩ አልቀረም፡፡
ኢምሬትስ ከበርበራው ስምምነት ለኢትዮጵያ የአክሲዮን ድርሻ መስጠቷ የቀጠናውን ሀገሮች ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጠቅማት ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ባለድርሻ መሆኗ በስምምነቱ መሰረት ከቀጠለ ሱማሌላንድን እንደ ዐይን ብሌኗ እንድትንከባከባት የሚያደርግ ነው፡፡ ምናልባትም የኢትዮጵያ ባለድርሻ መሆን የቀጠናውን የብሄራዊ ጥቅም አሰላለፍ ስለሚያዛባው የሞቃዲሾን መንግስት ክፉኛ ሳያስቆጣ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡ ሱማሊያ በውዝግቡ ከገፋችበት ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራት የጸጥታ ትብብር ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥርባት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ጋር እንዲህ ባለ የጋራ ንብረት መቆራኘቷ ለተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ወታደራዊ ጦር ሠፈር የፈቀደውን የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስትን በተዘዋዋሪ ለመነጠልም ይጠቅማት ይሆናል፡፡
“ሱማሌላንድና ፑንትላንድ ሉዓላዊ ግዛቶቼ ስለሆኑ ዐለም ዐቀፍ ስምምነት መፈጸም አይችሉም” የሚለው የሱማሊያ የሕግ መከራከሪያ ለጊዜው ለዐለም ዐቀፍ ሕግ ባለሙያዎች ትተን ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የውስጥ ፖለቲካዊ እና ጸጥታ ውጥንቅጥ እንዲሁም በዐለም ዐቀፍ መድረክ ካላት ስም አንጻር በተግባር ሲታይ ግን ብዙ ተስፋ ያላት አይመስልም፡፡ ኢምሬትስ በበርበራ ጦር ሠፈር ጭምር እየገነባች መሆኗም የሱማሊያን የመቃወም አቅም ያዳክመዋል፡፡ በተለይ በዐረብ ሊግ ካልተደገፈች በተግባር እምብዛም ልታደርገው የምትችለው ነገር እምበዛም ነው የሚመስለው፡፡
ጅቡቲ ተቆጥታለች
የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስና የዱባዩ ወደብ ድርጅቷ አተካራ የገጠማቸው ከሱማሊያ ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ባለፈው ወር ጅቡቲ የዱራሌ ወደብ ተርሚናልን 33 በመቶ ድርሻ ካለው ከዚሁ የዱባዩ ኩባንያ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ነጥቃለች፡፡
እናም ድንገተኛው ውሳኔ ምናልባት ኢትዮጵያና የዱባዩ ወደብ ድርጅት ፊታቸውን ወደ በርበራ ማዞራቸው የፕሬዝዳንተ ኢስማዔል ጌሌን መንግስት አስከፍቶ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ከዱባዩ ኩባንያ የሚሰማው ፉከራ “በርበራን የምስራቅ አፍሪካ የወደብ፣ ኢንቨስትመንትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ዋነኛ ማዕከል አደርገዋለሁ” የሚል መሆኑ ደሞ ዋነኛው ደንበኛዋ ኢትዮጵያ ብቻ ለሆነችው ጅቡቲ ራስ ምታት መሆኑ አይቀርም፡፡
በዚህም አለ በዚያ በርበራ ወደብ የባህረ ሰላጤው እና አፍሪካ ቀንድ ሀገራ የሚያካሂዱት የጅኦፖለቲካ እና ንግድ ፉክክር አንድ ተጨማሪ መናኸሪያ ሆኗል፡፡ ስምምነቱ እንደታሰበው ተግባራዊ ከሆነ ጅቡቲ በብቸኝት ይዛው የቆየችው የወደብ የበላይነትም የሚሸረሽርና ለቀጠናው ኢንቨስትመንት፣ እና ንግድ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ የሚጫወት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ግን የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተለይም ራስ ገዟ ሱማሌላንድና ሱማሊያ ከባህረ ሰላጤውና መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጅኦፖለቲካና ርዕዮተ ዐለማዊ ውዝግብ ዋነኛ አካል ከመሆን ወጥተው የራሳቸውንና የቀጠናውን ጥቅም ማስቀደም ከቻሉ ብቻ ይሆናል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]
https://youtu.be/cs4UGpksJEo