ዋዜማ ራዲዮ- በፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በአፍሪቃ ጉዳይ እንዲያማክሩ በዋይት ሀውስ የደህንነትና የፀጥታ ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ የታጩትን ራልፍ አታላህ ሹመታቸው በወቅቱ መፅደቅ ባለመቻሉ መሰናበታቸው ተሰምቷል።
ኮሎኔል ራልፍ አታላህ ከአራት ወራት በፊት በትራምፕ አስተዳደር ለሹመት መታጨታቸው ተነግሯቸው ሲዘጋጁ ቢቆዩም የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት(CIA) የይሁንታ ፈቃድ(Security Clerance) ስላልሰጣቸው እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።
ለአፍሪቃ ጉዳዮች ወሳኝ የሆነውን ስልጣን እንዲይዙ የታጩት ራልፍ አታላህ በሲአይ ኤ ይሁንታ ያላገኙት ከትራምፕ የቀድሞው የፀጥታ አማካሪ ማይክል ፍሊን ጋር በነበራቸው የሰራ ግንኙነትና ወዳጅነት ሳቢያ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ተናግረዋል።
አታላህ በአፍሪቃ በሚደረጉ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴዎች በማማከርና በስልጠና ስፊ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን ለሀያ አመታት ያህል በአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ አገልግለዋል። አርባ አምስት የአፍሪቃ ሀገራትንም ጎብኝተዋል።
ራልፍ አታላህ በግል ተቋም ውስጥ የዲፕሎማሲ ማግባባት ሎቢ ስራ የሚሰሩ ሲሆን አሁንም ወደዛው ስራቸው መመለሳቸው ተነግሯል።
አዲስ የአፍሪቃ ጉዳይ ዕጩ መሰየምን በተመለከት የዋይት ሀውስ ቃል ኣአቀባይ “በቅርቡ አዲስ ስው ይመደባል ብለን አንጠብቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
ለአፍሪቃ ጉዳይ ተወካይ አለመመደቡ የትራምፕ አስተዳደር በአፍሪቃ ጉዳይ ላይ ለቀጣዮቹ ወራት ምንም አይነት አዲስ እንቅስቃሴ የማድረግ ዕቅድ እንደሌለው አመላካች መሆኑን ተንታኞች ያስረዳሉ።