ዋዜማ ራዲዮ- የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችን በድጋሚ ለማደራደር ኢትዮዽያ ጥሪ አቀረበች።
የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበርና የኢትዮዽያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችን ማደራደር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን ወደ አዲስ አበባ ጋብዘዋል።
የኪር የዲንቃ ጎሳ አባላት ግን “ኢትዮዽያ ገለልተኛ አይደለችም፣ ልታደራድረን አይገባም” ሲሉ ተቃውሞ እያሰሙ ነው። ፕሬዝዳንት ኪር ከወታደራዊ አዛዦቻቸውና ከጎሳ መሪዎች ለድርድር ወደ አዲስ አባባ እንዳይሄዱ የሚጠይቅ ተደጋጋሚ ምክር እንደደረሳቸው ከጁባ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኪርን መንግስት የሚቃወሙት የኑዌር ጎሳ ተወላጁ ሪክ ማቻር ደቡብ አፍሪቃ “ታግተው” ይገኛሉ። ባለፈው አመት ከተደረሰው ስምምነት በኋላ አዳዲስ አማፂ ቡድኖች በመፈጠራቸው አዲስ ሊደረግ የታሰበው ድርድር ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል የግጭት ባለሙያዎች ያብራራሉ። ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካወጀች ከሁለት አመት በኋላ የገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት በአለማችን አሰቃቂ ከሚባሉ ስብዓዊ ቀውሶች አንዱ ነው።